Get Mystery Box with random crypto!

ሰላም! ዛሬ ትንሽ ስለጡረታ! ኢትዮጵያ አዳዲስ የጡረታ አዋጆች ማውጣቷን ሰምተዋል? ይኸውልዎ! • | የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት

ሰላም!
ዛሬ ትንሽ ስለጡረታ!
ኢትዮጵያ አዳዲስ የጡረታ አዋጆች ማውጣቷን ሰምተዋል? ይኸውልዎ!
• የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 እና ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 907/2007 በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014፤
• የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 እና ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 908/2007 ደግሞ በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014
ተሽረዋል፤ ተተክተዋል።
እነዚህ ህጎች ለወደፊት በሰፊው የምንመለስባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዛሬ በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 ስለአገልግሎት ዘመን የተደነገገውን በጨረፍታ እናጋራዎ!
የአገልግሎት ዘመን አቆጣጠር
1/ የመንግሥት ሠራተኛ የአገልግሎት ዘመን መቆጠር የሚጀምረው በመንግሥት ሰራተኝነት ከተቀጠረበት ወይም ከተመደበበት ቀን አንስቶ ሲሆን በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አቅድ ሽፋን ባለው ድርጅት የፈፀመው የአገልግሎት ዘመን በሙሉ ተዳምሮ ይታሰብለታል፤
2/ የሚከተሉት አገልግሎቶች ታሳቢ ይደረጉለታል፥-
ሀ) ከጡረታ መውጫ ዕድሜ በኋላ አገልግሎቱ በሕግ መሠረት ተራዝሞለት በሥራ ላይ እንዲቆይ የተደረገበት ጊዜ፤
ለ) የጡረታ መውጫ ዕድሜው በመድረሱ የጡረታ አበል ከተወሰነለት በኋላ በመንግሥት ውሳኔ ወደ ሥራ ተመልሶ አገልግሎት የሰጠበት ጊዜ፤
ሐ) የደመወዝ ክፍያ ሳይቋረጥ በማናቸውም ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ የቆየበት ጊዜ፤
መ) በየወሩ ደመወዝ እየተከፈለው ሙሉ ጊዜውን በማናቸውም የመንግሥት አካል ወይም በሠራተኛ ማህበር በተመራጭነት አገልግሎት የሰጠበት ጊዜ፤
ሠ) በመንግሥት መሥሪያ ቤት በጊዜያዊነት አገልግሎት የሰጠበት ጊዜ፤
ረ) በመንግሥት ትዕዛዝ መንግሥት ከ50 በመቶ በታች የካፒታል ድርሻ በያዘበት ድርጅት በማገልገል ያሳለፈው ጊዜ፤
ሰ) በመንግሥት ውሳኔ በዓለም አቀፍ ድርጅት በማገልገል ያሳለፈው ጊዜ፤
ሸ) ከጡረታ መውጫ ዕድሜ በኋላ በምክር፟ቤት አባልነት አገልግሎት የሰጠበት ጊዜ፤
ቀ)የአገልግሎት ወይም የጤና ጉድለት ዳረጎት ተከፍሎት ከተሰናበተ በሗላ የወሰደውን ዳረጎት መልሶ እንደገና በመንግሥት ሠራተኛነት የተቀጠረ ወይም የተመደበ ሰራተኛ የቀድሞ አገልግሎት ይታሰብለታል፤
በ) ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም በፊት የጡረታ መዋጮ ተመላሽ ተደርጎለት የወሰደውን የጡረታ መዋጮ ከባንክ የማስቀመጫ ወለድ ጋር መልሶ እንደገና በመንግሥት ሠራተኛነት የተቀጠረ ወይም የተመደበ ሰራተኛ የቀድሞ አገልግሎቱ ይታሰብለታል፤
3/ ከፊደል ተራ (ሐ) እስከ (ሸ) የተመለከተው ጊዜ በአገልግሎት ዘመንነት ሊታሰብ የሚችለው ሠራተኛው ወይም ተመራጩ መክፈል ያለበትን የጡረታ መዋጮ የአሠሪውን ድርሻ ጨምሮ ራሱ የከፈለ ወይም እንዲከፈልለት ያደረገ እንደሆነ ነው፤
4/ የሚከተሉት አገልግሎቶች ታሳቢ አይደረጉለትም፡-
ሀ) አገልግሎቱ በሕጉ መሠረት ካልተራዘመ በስተቀር የጡረታ መውጫ ዕድሜው ከደረሰበት ከሚቀጥለው ወር አንስቶ የሚሰጠው አገልግሎት፤
ለ) ኢትዮጵያ ተዋዋይ ወገን የሆነችበት ማናቸውም የዓለም አቀፍ ስምምነት እንደተጠበቀ ሆኖ በሕጋዊ ፈቃድ የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ የመንግስት ሠራተኛ የኢትዮጵያን ዜግነት ከማግኘቱ በፊት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም በጡረታ አቅድ በተሸፈነ የግል ድርጅት የሰጠው አገልግሎት፤

ሰኔ 02 ቀን 2014 ኣ.ም
ፋሲካ አጌና (የህግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ)