2022-07-11 09:09:54
በሚዳሰሱ ሞዴሎች ሐጅና ኡምራን ማስተማር እንዴት ይታያል? ከቅርብ, አመታት ወዲህ የሐጅ አፈፃፀም ስርአትን ለህፃናት በማስተማር አላማ የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ተበራክተዋል። የአዘጋጆቹ ሀሳብ መልካም ቢሆንም በሸሪዓ እንዴት ይታያል የሚለውን ማጥናት ተገቢ ይሆናል። ከዚህ አንፃር የፕሮግራሞቹ አዘጋጆች ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው እንዲያጤኑት ጥሪዬን አቀርባለው።
ይህ የማስተማሪያ ዘዴ በተለያዩ ሀገራት የተተገበረ በመሆኑ ብይኑን በተመለከተ ኡለማዎች ትኩረት ሰጥተው ውይይትና ምክክር አድርገውበታል። ምንም እንኳ አላማውን በመመልከት ይቻላል ያሉ አንዳንድ ኡለማዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ኡለማዎች እና የፈትዋና የምርምር ተቋማት ግን እንደማይፈቀድና ተገቢም እንዳልሆነ ገልፀዋል።
የዓለም የፊቅህ ሊቃውንት ምክር ቤት (መጅመዕ አልፊቅህ አልኢስላሚ) በሒጅራ አቆጣጠር ከሻዕባን 5/1412 እ.ኤ.አ በ 8/2/1992 ጀምሮ ባደረገው አስራ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤው የካዕባ ሞዴል በመስራት ልጆችን ማስተማርን በተመለከተ ተወያይቶ ባሳለፈው ውሳኔ (ይህ ተግባር ክልክል ወደሆኑ ክፉ ነገሮች ሊያዳርስ ስለሚችል መከልከልና በር መዝጋት ዋጂብ መሆኑን) አፅንቷል።
[ቀራራት አልመጅመዕ ገፅ 285]
እንደዚሁ የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴም (ካዕባ፣ መቃሙ ኢብራሂም፣ ጀመራት እና መሰል ቦታዎችን በሚዳሰስ ሞዴል በመስራት የሐጅና ዑምራ ክንዋኔዎችን ማስተማር አየፈቀድም) ካሉ በኋላ ምክንያቶችን ሲጠቅሱ፤ ሞዴሎቹን ማላቅ ወይም ማዋረድን የመሳሰሉ መጥፎ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። ገላጭ የሆኑ ፅሁፎችን በማብራራት ለሰፊው ህዝብ በቂ በሆነ መልኩ ማስተማር ስለሚቻል ሞዴል መስራት አስፈላጊ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
[ፈታዋለጅናህ 14/11]
ታላቁ አሊም ሸይኽ ኢብኑ ኡሰይሚንም በዚህ መልኩ ማስተማር የማይገባና የማይፈቀድ እንደሆነ በመግለፅ በምትኩ ቦርድ ላይ የካዕባን ስእል በመሳል ጠዋፍ እንደሚደረግ ማስተማር እንደሚቻል ተናግረዋል። በሞዴል ማሳየት በቀልብ ውስጥ ለኢባዳው ያለንን ቦታ በማሳጣት እንቅስቃሴ ብቻ ያደርገዋል ብለዋል።
[መጅሙዕ ፈታዋ ቅፅ 24 ገፅ 91]
በሞዴል ማስተማር ይቻላል ያሉ አንዳንድ ኡለማዎችም ቢሆን የዚህ አይነቱ ትምህርት በኢስላማዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር (ዊዛራ) ክትትል ሊፈፀም እንደሚገባ ከመጠቆማቸው ጋር ሞዴሎቹ እውነተኛውን የካዕባና የሐጅ ክንውን ቦታዎችን በጣም የማስመሰል ስራ እንዳይሰራ ከልክለዋል። እንደውም ሞዴሎቹ ትንንሽ ሆነው በአካባቢውና በያንዳንዱ ሞዴል ላይ መማሪያ መሆኑ እንዲገለፅበት፣ እንደ ኢባዳ ሳይሆን እንደ ትምህርት መማሪያ ብቻ መሆኑ ተደጋግሞ እንዲነገርና የሞዴሎቹን ክብር ከመንካት መጠንቀቅና ሌሎች መስፈርቶችን አስቀምጠዋል።
የእነዚህ ፕሮግራሞች አላማ የኢባዳው ፍቅር በልጆች ልቦና እንዲያድር ማድረግ እንጂ በዚህ እድሜ የሐጅ አፈፃፀም ህግጋትን የማወቃቸው አስፈላጊነት ጎልቶ አይመስለኝም። የሚዳሰሱ ሞዴሎችን በመገንባት ማስተማር የኡለማዎችን ትችት ያስተናገደና ቢያንስ በሸሪዓ ስለመፈቀዱ አጠራጣሪ የሆነ የማስተማሪያ መንገድ ነው። የሚያጠራጥርን ነገር በመተው ታዘናልና አዘጋጆች ሌሎች የማስተማሪያ መንገዶችን ቢጠቀሙ የተሻለ ይሆናል። ለምሳሌ ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ባመጣቸው እንደ 3D፣ ፓወር ፖይንትና እና ሞሽን ግራፊክስ በመጠቀም ማስተማር ይቻላል። ከዚህም በተሻለ በተቀረፀ እውነተኛ የሐጅ አፈፃፀም ቪድዮ ማስተማር ቀላል ነው። ወላሁ አዕለም
{إِنۡ أُرِیدُ إِلَّا ٱلۡإِصۡلَـٰحَ مَا ٱسۡتَطَعۡتُۚ وَمَا تَوۡفِیقِیۤ إِلَّا بِٱللَّهِۚ عَلَیۡهِ تَوَكَّلۡتُ وَإِلَیۡهِ أُنِیب}
በተቻለኝ ያክል ማበጀትን እንጂ አልሻም። (ለደግ ሥራ) መገጠሜም በአላህ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ በእርሱ ላይ ተመካሁ፡፡ ወደ እርሱም እመለሳለሁ» አላቸው፡፡
[Surah Hûd: 88]
ሐምሌ 3/2014»
: አቡ ጁነይድ ሳላሕ አሕመድ
1.8K viewsabdul@ziz Nur, edited 06:09