Get Mystery Box with random crypto!

ከፍቅር ወደ አፍቃሪነት.......2 ምንጭ ፦ ነፃነት (ኦሾ) ተርጓሚ ፦ ዘላለም ንጉሴ መፈለግ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ከፍቅር ወደ አፍቃሪነት.......2

ምንጭ ፦ ነፃነት (ኦሾ)
ተርጓሚ ፦ ዘላለም ንጉሴ

መፈለግ (መውደድ) ከሰዎች ታላላቅ ፍላጎቶች አንዱ ነው:: ስለዚህ ፍቅር ህልውናን ይዞ ይኖራል። የሰው ልጆች እስካሉ ድረስ የፍቅርን ያህል ትልቅ ነገር አያገኙም፡፡ በምድር ላይ የሚገኝ ግን የምድር ያልሆነ ነገር ነው:: በፀሐይ ፊት እንደንስር የምትበሩበት ክንፍ ይሰጣችኋል።

ያለ ፍቅር አክናፋት አይኖሯችሁም፡፡ እጅጉን አስፈላጊ የመንፈስ ምግብና ተፈላጊ ነገር ከመሆኑ የተነሳ በዙሪያው ችግሮች ይከቡታል፡፡ ፍቅረኛህ ወይንም ፍቅረኛሽን ነገር የራስህ /ሽ/ ማድረግ ትፈልጋላችሁ ዛሬ ውብ ነገር አሳልፋችኋል፣ ለነገ ደግሞ ትጨነቃላችሁ፡፡ ስለዚህ ትዳር ይመጣል። ፍቅረኛችን ነገ እንዳትከዳን ስለምንፈራ በማህበረሰብና በሕግ ፊት ውል እንፈርማለን። ፍፁም አስቀያሚና ዘግናኝ ነገር ነው:: ፍቅርን ወደ ውል መለወጥ፣ ህግን ከፍቅር ማስቀደም ማለት፣ ማህበረሰብን ከራስህ ህልውና ማስቀደም ማለት ነው፡፡ የፍርድ ቤቶችን የጦር ሠራዊቱን፣ የፖሊሲንና የዳኞችን ከለላ በመሻት ጥምረታችሁን የተረጋገጠ ለማድረግ መጣር ማለት ነው:: ነገ ጠዋት ማንም አያውቅም፡፡ ፍቅር እንደነፋስ ሽውታ ሆኖ ይመጣል። ድጋሚ ታገኘው ይሆናል፣ ፈጽሞ ላይመጣም ይችላል። ሳይመጣ ከቀረ በህግና በትዳር የተነሳ ብቻ፣ በማህበረሰብ ክብር ከመጨነቅ የተነሳ ብቻ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉት ጥንዶች ሕይወት ሁሉ ማለት ይቻላል፣ ወደ ወሲብ ንግድ ይለወጣል።

ከፍቅር በስተቀር በሌላ በማንኛውም ምክንያት፣ ለደህንነት ወይንም የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ተብሎ ከማትወዳት ሴት ጋር መኖር፣ ከማታውቂው ወንድ ጋር መኖር ኑሯችሁን የወሲብ ንግድ ያደርገዋል፡ የወሲብ ንግድ ከዓለም ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ እፈልጋለሁ፡፡ ኃይማኖቶች ሁሉ የወሲብ ንግድ መኖር የለበትም ይላሉ፡፡ የሰው ልጅ አይረቤነት የሚታየው ይህን በመሳሰሉ ሁኔታዎች ላይ ነው።

ከእምነት ማጣት ውስጥ ፍቅርን የሚያበለጽግና የሚያሳድግ ምንም ነገር የለም፡፡ ከነአካቴው ያጠፋዋል። አፍቅር ግን ሁለተኛ አታጥፋው፡፡ ፍቅር ትክክለኛ የሚሆነው ነፃነትን ሲያጎናፅፍ ብቻ ነው::

ቅድመ ሁኔታው ይህ ይሁን። እውነተኛ ፍቅር የሚባለው የሌላውን ሰው ነፃነት የማይጋፋ ከሆነ ነው:: የሌላውን ሰው የግል ኑሮና ማንነቱን ያከብራል፡፡ ዳሩ ግን በዓለም ዙሪያ የምናያቸው ፍቅረኞች ጥረት ግን ምንም ነገር የግል መሆን የለበትም የሚል ነው፣ ሁሉም ምስጢሮች ሊነገራቸው ይገባል። ግላዊነትን ይጠላሉ፣ ይፈራሉ፡፡ አንዳቸው የሌላቸውን ማንነት ያጠፋሉ፣ ይህን በማድረጋቸውም ሕይወታቸው ርካታና ደስታ የተሞላበት አንደሚሆን ያስባሉ፡፡ ሰቀቀናቸው እለት እለት እየጨመረ ይመጣል::

አፍቃሪ ሁን፤ እውነተኛ ሆነ ማንኛውም ነገርም ዘወትር እንደሚለዋወጥ አስታውስ፡፡ ትክክለኛ ፍቅር ዘለዓለም ይኖራል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ተቀብለህ ሊሆን ይችላል። ትክክለኛ ጽጌሬዳ አበባ ዘለዓለም አትኖርም፡፡ ህያው ፍጥረት እንኳን አንድ ቀን መሞት ይኖርበታል። ሕልውና የማያቋርጥ ለውጥ ነው፡፡ ፍቅር ዘለዓለም ይኖራል የሚለው ሀሳብ እውነት ቢሆን ኖሮ  ፍቅር አንድ ቀን ቢጠፋ የምንደርስበት ምክንያታዊ ድምዳሜ፣ እውነተኛ ፍቅር አልነበረም የሚል ይሆናል፡፡

እውነተኛ ፍቅር በድንገት የሚይዝህ አንተ ስለጣርክ አይደለም:: በቃ ተፈጥሮ ስጦታ ነች:: ሲመጣ ግን አንድ ቀን እንዳመጣጡ ይሄዳል ብለህ ብትጨነቅ ኖሮ ከነአካቴው ባልተቀበልከው ነበር፡፡ ግን የሚያስጨንቅ ነገር የለም:: ምክንያቱም አንድ አበባ ሲከስም ሌላ አበባ ይፈነዳል።

ካልሆነ ግን ብዙም ሳትቆይ የሞተና የረገፈ አበባ ላይ ሙጥኝ ብለህ ትቀራለህ፡፡ እውነታውም ይኸው ነው። ሰዎች በአንድ ወቅት ህያው የነበረ የሞት ፍቅርን የሙጥኝ ብለው ይታያሉ:: አሁን ወደ ትዝታና ስቃይ ተለውጧል፡፡ ለክብርና ለህግ ካለህ ጭንቀት የተነሳም ታስረህ ትቀራለህ።

ካርል ማርክስ ለዚህ ትክክለኛውን ሀሳብ አቅርቧል፣ ይህም በኮሚኒውዝም ስርዓት ውስጥ ምንም አይነት ትዳር አይኖርም፡፡ ሩሲያ ውስጥ አብዮቱ ከፈነዳ በኋላም፣ በመጀመሪያዎቹ አራት አምስት ዓመታት ውስጥ ፍቅርን ነፃነት ለማድረግ ሞክረዋል። ግን የካርል ማርክስ ጽንሰ ሀሳብ ወደ ተግባር ሲለወጥ ችግር ተፈጠረ ምክንያቱም ትዳር ከሌለ ቤተሰብ ይጠፋል፡፡ ቤተስብ ከጠፋ ደግሞ የማህበረሰቡና የህዝቡ /ሀገር/ የጀርባ አጥንትና መሠረት ነው፡፡ ቤተሰብ ከጠፋ ሀገርም መጥፋቱ አይቀርም፡፡
ከአብዮቱ እውን መሆን ከአምስት ዓመታት በኋላ የሩሲያ ኮሚውኒስት ፓርቲ ይህን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ለወጠው። ትዳር ዳግመኛ ድጋፍን አገኘ፡፡ ፍቺ ተፈቅዶ ግን መፋታት እጅግ ከባድ ሆነ፡፡ ምክንያቱም ቤተሰቡ እንዳለ መቆየት ይችላል የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከርም ይረዳል:: ያለ ሀገር ፖለቲከኞችም ሆኑ መንግሥት ሊኖር አይችልም። ትዳር የመጣው የግል ንብረት ከሚለው ሀሳብ ጋር ተያየዞ ነው የሚለውን የማርክስን ሀሳብ አላነሱም፡፡ ምክንያቱም የግል ንብረት ሲጠፋ ትዳርም አንድ ላይ ይጠፋል:: ከዚያ በኋላ አልተነጋገሩበትም፡፡

ዓለም ወደ ብዙ አካላት እንድትከፋፈል አልፈልግም። ነፃ ግለሰቦች በራሱ ጊዜ በሚቀጣጠል ፍቅር ውስጥ፣ በፀጥታና በደስታ የሚኖሩባት አንድ ዓለም እንድትፈጠር እፈልጋለሁ፡፡ ገነትን እዚሁ መፍጠር እንችላለን፡፡ ገነትን ለመፍጠር የሚያስፈልገን እምቅ ሀይል ሁሉ ቢኖረንም እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡ በተቃራኒው ግን ብዙ እንቅፋቶችን እየፈጠርን እንገኛለን።

እኔ የፍቅር ተፃራሪ አይደለሁም፡፡ ፍቅርን እጅግ እደግፈዋለሁ፡፡ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን ሙሉ አብረው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መለያየት አለባችሁ ማለት ሳይሆን፣ ይህን አብሮ መኖር የሚመሠረተው ፍቅር ላይ ብቻ መሆንና የሌላውን ግላዊ ሕይወትና ነፍስ በማይነካ ነፃነቱን በሚጠብቅ ሁኔታ መሆን አለበት፡፡ ይህ የሌላው ሰው ክብር ነው።

አፍቃሪ መሆን ትችላለህ፣ ፍቅር መሆን ትችላለህ:: አፍቃሪ ብቻ ከሆንክ ፍቅርን ራሱን ብቻ ከሆንክ፣ ፍቅር ወደ ጥላቻ የሚለወጥበትን ምንም ዓይነት እድል አትሰጠውም፡፡ ተስፋ የምትጥልበት ነገር ስለማይኖር ድንገተኛ ነገር ሊረብሽህ አይችልም፡፡ ስለፍቅር የምንናገረው ግን በመንፈሳዊ ክስተትነቱ እንጂ ከስነ-ተፈጥሮ አንፃር አይደለም፡፡ ስነ ፍጥረት ሴሰኝነትን እንጂ ፍቅር አይደለም፡፡ የስነ-ፍጥረት ዓላማ ዘርን መተካት ሲሆን፣ የፍቅር ሀሳብ ስነ-ተፈጥሯዊ ብቻ ነው፡፡ ሰው ተራክቦ ከፈፀመ በኋላ ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሃያ አራት ሰዓታት ፍቅረኛው እንደማትፈልገው ይሰማዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከእድሜ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እድሜህ እየገፋ ሲሄድ ጊዜው አርባ ስምንት ሰአት፣ ወደ ሰባ ሁለት ሰአት... እያለ ይቀጥላል።

@Zephilosophy
@Zephilosophy