Get Mystery Box with random crypto!

ከፍቅር ወደ አፍቃሪነት...........1 ምንጭ ፦ ነፃነት (ኦሾ) ተርጓሚ ፦ ዘላለም ንጉሴ ፍ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ከፍቅር ወደ አፍቃሪነት...........1

ምንጭ ፦ ነፃነት (ኦሾ)
ተርጓሚ ፦ ዘላለም ንጉሴ

ፍቅር  ሁለት ፍፁም የተለያዩ እንደውም ሙሉ ለሙሉ ተቃራኒ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ አንዱ ትርጉም ፍቅር በፍቅር ግንኙነት መልኩ ሲገለጽ እና ሌላው ደግም ፍቅር በራሱ ህልውና ይዞ ሲገኝ ነው:: ፍቅር ወደ ፍቅር ግንኙነት በሚለወጥበት ወቅት ባርነት ይሆናል:: ምክንያቱም የምንጠብቃቸውና የሚጠበቁብን ነገሮች እንዲሁም መረበሽ እና ፍርሀትን ይፈጥሩብናል፡፡ ከሁለቱም ወገንም እኔ እበልጥ ስሜት ይመጣል፡፡ የኃይል እሽቅድምድም ይሆናል:: የፍቅር ግንኙነት ትክክል አይደለም:: ፍቅር ህልውና ይዞ ሲገኝ ግን ሙሉ በሙሉ የተለየ ነገር ይሆናል፣ ስታፈቅር ከፍቅር ሌላ የፍቅር ግንኙነት እየፈጠርክ አይደለም ማለት ነው:: ፍቅርህ እንደ አበቦች ጥዑም መዓዛ ይሆናል። የፍቅር ግንኙነት አይፈጠር፣ ይህን አድርግ፣ ባህሪህ እንዲህ ይሁን አይልህም:: ከአንተ ምንም አይፈልግም። ያካፍላል። በማካፈሉም ምንም ሽልማት አይፈልግም፡፡ ማካፈሉ በራሱ ሽልማት ነው፡፡

ፍቅር ለአንተ እንደ አበቦች መዓዛ በሚሆንበት ጊዜ ታላቅ ውበት ይኖረዋል ከሰብዓዊነት በላይ የመጠቀ መለኮታዊ ነገር ይኖረዋል፡፡

ፍቅር ብቻውን ከመጣብህ ምንም ልታደርገው አትችልም፡፡ በማንኛውም ሰው ላይ አሳርን አያመጣም አንተም በማንኛውም ሰው እንድትታሰር አይፈቅድም፡፡

ግን ከልጅነት አንስቶ የፍቅር ግንኙነቶችን የመፍጠር ልምድ አለህ፡፡ ከማታውቀው ወንድ ጋር የአባትና የልጅ ግንኙነት ትፈጥራለህ:: አባትህ መሆኑን በፍፁም ርግጠኛ ልትሆን አትችልም፡፡

አንድ የሰዎችን መዳፎች በመመልከት ዕጣ ፈንታቸውን ስለሚተነብይ ሰው የሰማሁት ታሪክ አለ። በእጅ መዳፍ ንባብና በአስትሮሎጂ በመሳሰሉት እንዲሁም በእግዚአብሔርም የማያምን አንድ ወጣት ወደዚሁ ሰው ይሄድና፣ ሳይንስህ ትክክል ከሆነ እጄን አንብብና አባቴ የት እንደሚገኝ ንገረኝ አለው።»

አዋቂውም መዳፉን ተመልክቶ እንዲህ አለው «አባትህ አሳ እያጠመደ ነው፡፡» ወጣቱ ኢአማኒ ሳቀ፡፡ «እኔ የምለው ይህንኑ ነው፣ የማይረባ ሥራ ነው:: አባቴ ከሞተ ሶስት ዓመት ሆኖታል፤ ዛሬ እንዴት አሳ ለማጥመድ ይሄዳል።>>

አዋቂውም ሲመልስ፣ «ይህ እኔን አያገባኝም፤ እውነቱ ግን ያ የሞተው ሰው አባትህ ያለመሆኑ ነው፡፡ ትክክለኛ አባትህ አሳ እያጠመደ ነው፡፡ ወደ እናትህ ሂድና ጠይቃት፡፡ ታማኝና እውነተኛ ከሆነች የሞተው ሰው አባትህ እንዳልሆነ ትነግርሀለች። አንተ ግን አባትህ ነው ስለተባልክ ከእሱ ጋር የአባትና የልጅ ፍቅር ግንኙነት ፈጥረሀል፡፡

ሕይወታችሁ በሙሉ በብዙ ዓይነት ግንኙነቶች የተሞላ ነው:: ይህ መሰል ግንኙነቶች ደግሞ እውነትም ይሁን ሀሰተኛ፣ እጅግ ውስብስብ የሆነ ስነልቦናዊ ባርነትን ይፈጥራል። ወይ ሌላውን ባርያ ታደርጋለህ፡፡ ወይንም ራስህ ባርያ ትሆናለህ::

ሌላው መታወስ ያለበት ነጥብ ደግም ራስህን ባርያ ሳታደርግ ሌላውን ሰው ባርያ ማድረግ አትችልም፡፡ ባርነት ባለሁለት ሶስት ሰይፍ ነው፡፡ አንደኛው የበለጠ ጠንካራ፣ ሌላው የበለጠ ደካማ ሊሆን ይችላል፤ ግን በሁሉም የፍቅር ግንኙነቶች ውስጥ አንደኛው አሳሪ ሌላው ታሳሪ ይሆናል። ከእሱ አንፃር ሲመለከተው እሱ አሳሪው አንተ ደግሞ ታሳሪ ትሆናለህ። የሰው ልጅ ይህን በመሰለ ሀዘንና ሰቆቃ የመኖሩ ዋነኛ ሀቅና ምክንያት መካከል አንዱ ይኸው ነው፡፡

ጥላቻ ደግሞ ከፍቅርህ የጠነከረ ግንኙነት ይፈጥራል ምክንያቱም ፍቅርህ ከአንገት በላይ ነው:: ጥላቻህ እጅግ ጥልቅ ነው:: ጥላቻህን የወረስከው ከእነስሳዊነት ባህሪህ ነው:: ፍቅርህ ለመጪው ሕይወትህ ያለህ ብቸኛ እምቅ ኃይልህ ነው:: እውን የሆነ ክስተት ሳይሆን ወደፊት ፍሬ የሚያፈራ ዘር ነው:: ጥላቻህ ግን ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ የሚገኝ፣ እጅግ የጎለመሰ፣ ያለፈው የብዙ ሺህ ዓመት ታሪክህ ህያው ቅርፅ ነው፡፡ የሚያድግበት ጊዜና ቦታ የነበረው:: ለውጡ መከሰት የሚጀምረው ግን በሰው ልጆች ላይ ነው::

ግን ማንንም እኔን ከመጥላት ማገድ አልችልም ስለዚህ ማንም ሰው እንዲያፈቅረኝ ማድረግ አልችልም:: ልገልፀው የምችለው ነገር ቢኖር ጥላቻም ሆነ ፍቅር የግንኙነት መልክ በሚይዝበት ጊዜ ንፅሕናውን እንደሚያጣ ብቻ
ነው፡፡

ፍቅርህን ህልውናህ አድርገው፡፡ ፍቅር
እንዲይዝህ ሳይሆን አፍቃሪ እንድትሆን ጣር፡ ፍቅር ባሪያህ ነው። ለአንተ ፍቅር የህልውናህ ጥፁም መዓዛ ነው:: ብቻህን ብትሆን እንኳን በአፍቃሪ ኃይል ትክበባለህ፡፡ የሞተ ነገርን ለምሳሌ ግዑዝ ወንበርን ብትዳስስ እንኳን ከእጅህ ፍቅር ይፈልቃል:: ፍቅርህን የምትሰጠው ለምንም ወይንም ለማንም ሊሆን ይችላል፡፡

በፍቅር ስሜት ውስጥ መሆን የለብክም እያልኩ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን በፍቅር ስሜት ውስጥ መኖር የምትችለው ቀድሞውን የፍቅር ግንኙነት አስተሳሰብህን በምትተውበት ጊዜ ነው:: ፍቅር በሰዎች መሀል የሚመሰረት ግንኙነት ዓይደለም።

ሁለት ሰዎች አንድ ላይ እጅግ አፍቃሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አፍቃሪነታቸው በጨመረ ቁጥር በመካከላቸው የሚፈጠረው የፍቅር ግንኙነት ይጠፋል። አፍቃሪነታቸው በጨመረ መጠን፣ አንዳቸው ከሌላቸው የሚፈልጉትንና አንዳቸው በሌላቸው የሚጥሉት ተስፋ ይቀንሳል፡፡ ውስጥም ይገባሉ፡፡

በውል ሳይተዋወቁ ፍቅርን ብቻ እያሰቡ ሲወዳደሱ በመጨረሻ መወቃቀስ ይጀምራሉ፡፡ ለዚህም ነው ምንም ዓይነት ተስፋ ማድረግ እንደማያስፈልግ ልታስታውስ የምፈልገው፡፡ ፍቅር የራስህ ውስጣዊ እድገት መሆኑን አውቀህ አፍቅር። ፍቅርህ ወደላቀ ብርሀን፣ ወደላቀ እውነትና ነፃነት ከፍ ያደርግሀል፡፡ ግን የፍቅር ግንኙነት አትፍጠር፡፡

አንድ ነገር ብቻ አስታውስ፣ ፍቅር ማንኛውንም ዓይነት መጥፎ ነገር የማጥፋት አቅም አለው፣ ፍቅርን ወደ ፍቅር ግንኙነት እንዲለወጥ ከፈቀድክለት ግን፣ ፍቅር ይጠፋና የጓደኝነት ስሜት በውስጥህ ያለው ውብ ባህሪ ሲሆን ጓደኝነት ግን ወደ ትስስር ያመራል፡፡

ስለዚህ ፍቅር መልካም ነገር ነው:: እንደውም ፍቅር የሌለበት ነገር
ሁሉ ስህተት ነው:: ግን ፍቅር ከፍተኛ ዋጋ በመሆኑ ከማንኛቸውም ዓይነት በካይ መርዘኛ ነገሮች መጠበቅ አለበት፡፡ ትስስር ይበክለዋል። ዓለም በግለሰቦች የተሞላች እንድትሆን እፈልጋለሁ:: «ጥንድ» የሚለው ቃል እንኳን ይጎዳኛል፡፡ የሁለት ግለሰቦችን ህልውና አጠፋችሁ ማለት ነው፡፡ ጥንድ በራሱ ውበት የለውም፡፡

ዓለም በግለሰቦች ብቻ የተሞላች ትሁን፡፡ ፍቅር በራሱ ጊዜ ጎምርቶ ሲፈነዳ ፍቅርን ዘምሩት ፣ ጨፍሩት፣ ኑሩት፣ ግን ፍቅርን ወደ ሰንሰለት አትለውጡት፡፡ ሰውን በባርነት ለመያዝ አትሞክሩ፣ ሌላም ሰው በባርነት እንዲይዛችሁ አትፍቀዱ፡፡

ነፃ ግለሰቦችን የያዘች ዓለም በትክክል ነፃ አለም ትሆናለች።

ይቀጥላል

@Zephilosophy
@Zephilosophy