Get Mystery Box with random crypto!

ሕይወት በሚታይና በማይታይ ማዕበል የተከበበች ናት! ሰው ሃሳቡ በግንባሩ ላይ ቢጻፍ ማን ማንን ቀ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ሕይወት በሚታይና በማይታይ ማዕበል የተከበበች ናት!

ሰው ሃሳቡ በግንባሩ ላይ ቢጻፍ ማን ማንን ቀና ብሎ ያያል? ደግነቱ በውስጣችን ያለውን ማንም አያውቅብንም። የምናስበውን አስበን፤ የፈለግነውን አሳውቀን የምንደብቀውን ደብቀን የመኖር ጥበቡ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ጥበብ ነው። ልብ በሃዘን ደምቶ ፊት በፈገግታ ሲፈካ ፤ ግንባር ኮስተር ብሎ ልብ በሃሴት ሲሞላ ፤ ጉልበት ተንበርክኮ ልብ በትዕቢት ሲቆም ፤ አፍ እንደ ማር ጣፍጦ ልብ እንደ እሬት ሲመር ፤ ማን ማንን ያውቃል ያሰኛል?!

የሰው ልጅ በሚታየውና እና በማይታየው ማዕበል ውስጥ ያልፋል፤ የሚታየው ማዕበል ሌሎች የሚረዱት እና የሚያዩት ችግራችን ሲሆን፤ የማይታየው ማዕበል ደግሞ ከሌሎች ደብቀን ለብቻችን የምንጋፈጠው ችግር ነው”።

ሌሎች የማውቁት ምን አይነት ጭንቀት ይሆን እያንዳንዳችን በውስጣችን ያለው? ምን አይነት የማይታይ ማዕበል እየተጋፈጥን ይሆን?

አዎ በሰው ፊት እንስቃለን ለብቻችን ግን እንባችንን በገዛ መዳፋችን ያለማቋረጥ እናብሳለን። ከሰው መሃል ደምቀን ለብቻችን ስንሆን መግቢያ እናጣለን። ከህዝብ ፊት ከብረን በቤታችን ግን የሰው ያህል የሚቆጥረን የለም። ጠንካራ መስለን፤ ልባችንን ግን በክህደት ስብርብሩ ወጥቷል። ከላይ ሰላም የሰፈነብን እንመስላለን፤ ውስጣችን ግን በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ይተራመሳል። ከውጪ ሲታይ ቤታችን የደመቀ ቢመስልም ውስጡ ግን እንደ ዋሻ ቀዝቅዟል። ተለቀም አነሰም ሁላችንም ለሌሎች የማይታይ ለብቻችን የምንጋፈጠው ማዕበል አለን።

እናም በየመንገዳችን ስንተላለፍ ልብ እንበል፤ ሌላው ከኛ ያነሰ ትግል የሚታገል እየመሰለን ፊት አንንሳው፤ እየረገጥን አንለፈው። የኔ ችግር እና ጭንቀት ከሌላው ይበልጣል የሚል አስተሳሰብ ሲኖረን ለሌሎች የምንዘረጋው እጅ ያጥረናል። ትኩረታችን ሁሉ የራሳችን ችግር ላይ ሲሆን ይበልጥ እናማርራለን፤ ሌሎች ለብቻቸው የሚገፈጡትን ማዕበል ስለማናይ “ምነው እኔን ብቻ” እያለን የሃዘናችንን ጉድጓድ ይበልጥ ወደታች እንቆፍረዋለን።

ከትዳር አጋራችን ጋር ክንድ ተንተርሰን እያደርን፤ እርስ በርሳችን የምንፋለመውን ትግል አናውቅም። ለዚህ ነው ጭቅጭቅ ሲነሳ መሸናነፍ እና እርቅ ማውረድ የሚከብደን፤ ማን የማንን ማዕበል ያያልና? እናም በየመንገዳችን የሚያጋጥሙን ሰዎች ሁሉ የራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው፤ በጫማቸው ሳንቆም አንፍረድ። በደቂቃ ውስጥ ያየነውን ምግባራቸውን ተንተርሰን አንፍረድ።

ሌላውም እንደኔ ስሜት አለው የሚል አስተሳስብ መያዝ ስንጀምር፤ የሌላው ህመም ይሰማናል እናም ብዙ ስህተቶችን ከመፈጸም እንድናለን። ምናልባት ለብቻሽ/ ለብቻህ የምትጋፈጠው ማዕበል ካለህ በርታ… አጋዥ የለኝም ብለህ አትስጋ ፈጣሪ የማትችለውን ችግር አይሰጥህም። አንተ/አንቺ ብቻ ከሰው የተለየ መከራ አልተሰጠሽም/አልተሰጠህም እንደየአቅማችን ለሁላችንም የታደለን ነው እንጂ……ከምንም በላይ ግን እርስ በርሳችን እንተጋገዝ፤ እየተገፈታተርን መተላለፉን እናቆም ምክንያቱም ሁላችንም ለየብቻችን በምንጋፈጠው ማዕበል ደክመናልና።

                       ሚስጢረ አደራው

            ውብ አሁን

@zephilosophy