Get Mystery Box with random crypto!

“መቼም አልሰማ ብለህ ክሴን እቀጥላለሁ” ካልክ የሆንከውን አብራርተህ ተናገር! አታደናግር!” ሽማግ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

“መቼም አልሰማ ብለህ ክሴን እቀጥላለሁ” ካልክ የሆንከውን አብራርተህ ተናገር! አታደናግር!” ሽማግሌው ጮኸ።

“ነገሩ እንዲህ ነው። የሆነ ቀን አለልማዴ ዓለሜን አስከትዬ ዛፍ ቆረጣ ሄድሁ። በእኔ ቤት ዛፍ ቆርጬ ገንዘብ ላገኝ ነው እንግዲህ። አዬ! ...ምነው በቀረብኝ። ዓለሜን አርቄ አስቀምጬ መጥረቢያዬን ይዤ ዛፉ ላይ ወጣሁና መተግተግ ጀመርሁ። ምን የተረገመው ቀን እንደሆነ እንጃ ከዛፉ ላይ አንዲት ሰላላ ቅርንጫፍ ብላት ብሠራት አልቆረጥ አለችኝ። ዛሬ ደግሞ የምን ተአምር ነው የገጠመኝ? እያልሁ ደጋግሜ ብመታት ጭራሽ እንደድንጋይ መጥረቢያዬን አንጥራ ትመልሳለች እንጂ ፍንክችም አትልም። ሠላሳ ዓመት ዛፍ ስቆርጥ እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝም አያውቅም። የዚህ ሀገር እንጨት እንደምታውቁት ገራም ነው፤ እንኳን ቅርንጫፍ ግንዱም ዐሥሬ ደኅና ካገኙት ይበቃዋል። ተንጋልሎ ያርፋል። የትንግርቴን ተፋጥጬ ሳነሣ ስለው፣ ሳነሣ –ስለው ...እልህ ይዞኝ እንጂ እጄ ዝሎ ኖሮ መጥረቢያው አምልጦኝ ቁልቁል ተምዘገዘገ። በዓይኔ ስከተለው...

” ዕድሉ ቀና ሳግ አንቆ አላናግር ስላለው አቀርቅሮ ጊዜ ወሰደ።

“ለቅሶህን ተውና ቀጥል ተብለሃል!”

“በዓይኔ ስከተለው እንደ ኪሩብዔል ሰይፍ ሲገለባበጥ ወርዶ ከየት መጣች ያላልኳት የልጄ አናት ላይ ሰመጠ። ይታያችሁ! ለእንጨት የሰነፈ መጥረቢያ ለልጄ ሲሆን በረታ። ለካ ዓለሜን አርቄ ባስቀምጣትም አሳዝኛት ሥሬ መጥታ ሽቅብ ስታየኝ ነበር። እኔ አፈር ልብላላት ...ሞት ሲጠራት እኮ ነው! ታዲያ ፈጣሪ ቢለው አይደል ሠላሳ ዓመት ሙሉ ገጥሞኝ የማያውቀውን የእዚያ ቀን መጥረቢያ ያመለጠኝ? ታዲያ ፈጣሪ ቢለው አይደል አድርጌ የማላውቀውን መጥረቢያ የሚያመልጠኝ ቀን ልጄን ይዤ የመጣሁት? ታዲያ ፈጣሪ ቢለው አይደል ከዓመት እስከ ዓመት የሚያሰቃያት ንዳድ ያንን ቀን ጋብ ያለላት? ታዲያ ፈጣሪ ቢለው አይደል ለእጅ የምትሰንፍ ቅርንጫፍ በስል መጥረቢያ የለገመቸው? ለምን “እንቢ! ስትለኝ አልተውኋትም? ምነው መጥረቢያውስ ካልጠፋ አውላላ መዳፍ የማታህል የልጄን አናት የመረጠው? ፈጣሪ ቢለው አይደል?”

አዝማሪው ሐዋዝ ተነሣ
“መቼም እንደሰው ልጅ ጉድ የትም የለም። ጠማማ ዕድሉንም፣ ስንፍናውንም በፈጣሪ ማሳበብ ይወዳል። አንተ የአርባ ዓመት ጎልማሳ ስትሆን ምነው ልጅህን መጠበቅ አላወቅህበት? እጅህ እስኪዝል አንድ ቅርንጫፍ ቀጥቅጥ ያለህ ፈጣሪ ነው? ከእጅህ አሽቀንጥረህ ስትጥለውም ወደወረወርክበት ይሄዳል እንጂ መጥረቢያ እግር የለው፤ ዓይን የለው፤ ምን አድርግ ነው የምትለው? ይህን ድፍረት ለተናገርህበት ራሱ ቅጣት ይገባሃል። ኧረ ምነው! ስንት ነገር ጥለን ነው የመጣነው፤ ጊዜያችንን ባንፈጅ...?”

ዕድሉ ቀና ክሱን ሰምቶ የሚደግፈው አለማግኘቱ አንገበገበው። ኀዘኑ እጥፍ ድርብ ሆነ። መናገሩ እንደማይጠቅም ሲሰማው ልቡ አመነታ። ቢሆንም የተበደለው አላለቀም። ቢያንስ “ተናግሬ ይውጣልኝ!” ብሎ ተቀበለ።

“አይ ሐዋዝ! አንተ ጎረቤቴ ሆነህ የደረሰብኝን ሁሉ ስታውቅ እንዲህ ማለትህ አሳዝኖኛል። ጊዜ የተፈጀብህ ለምኑ ነው? አናውቅም የት ውለህ የት እንደምታነጋ? ሌላ ምንም አልልህም አንተም ሴት ልጅ አለችህ። በልጅ የመጣ እንዴት እንደሚያንሰፈስፍ ደርሶብህ እየው።” ንግግሬ እንዳልጠቀመ አይቼያለሁ። ቢሆንም ልናገረውና የመጣው ይምጣ...”

ዋናው ዳኛ አንካሳ እግራቸውን በእጆቻቸው እያመቻቹ የሚሆነውን በዝምታ ይሰማሉ።

“ይቅር ብዬ አልፌው እንጂ የተበደልሁትስ ይህ ብቻ አልነበረም። ከሆነ አይቀር ግን ይኸው ስሙት። ታላቁ ልጄ እንደምታውቁት የቀኝ እጁ አራት ጣቶች ቆራጣ ናቸው። የእርሱ ታናሽ ደግሞ እጁም እግሩም ላይ ስድስት ስድስት ጣት አለው። ይህ እንዴት ሆነ? ሲቀለድብኝ መሆኑ ነዋ! .....አንድ ቀን ጠዋት የጀመርሁ ሥራ ፍለጋ ስንከራተት ውዬ ሰውነቴ ዝሎ አመሻሽ ላይ ቤት ደረስኩ። ምንም ምንም ሳልል፤ እህልም ሳልቀምስ፤ ልብሴንም ሳላወልቅ መጥረቢያዬን ቆጥ ላይ ሳልሰቅል ተኛሁ። ብዙም አልቆየ ታላቅ ልጄና ነፍሰጡር ሚስቴ በጩኸት ቤቱን ሲያናጉት ብትት ብዬ ተነሣሁ። ሳይ ከልጄ መዳፍ ላይ ደም እንደወራጅ ውኃ ይንዠቀዠቃል። ዘልዬ አፈፍ ሳደርገው አራት ጣቶቹ ተራ በተራ ጠብ፣ ጠብ ብለው እንደጉድፍ መሬት ላይ ወደቁ። ያ መጥረቢያ ከንፈሩ ደም ጠግቦ ተጋድሟል። የሆነው ወዲያው ገባኝ። ታዲያ ምን ዋጋ አለው? ከረፈደ ዕውቀት የቀደመ ጠርጣራነት እንደሚበልጥ ማን አስተምሮኝ ያኔ? ደንቆሮ፣ የደንቆሮ ዘር አይደለሁ። አንድ ቀን መጥረቢያዬን ማራቅ ብረሳ... ። ዛሬም ድረስ አውራ ጣቱ በመዳፉ ላይ ብቻዋን ፍርፍር ስትል ሳያት እንባዬ ይመጣል። ጠማማ ዕድሌን መግራት ተስኖኝ እንዳጎደልሁት ይሰማኛል!”

"ይበቃል ተብለሀል።"

...
“አይበቃኝም ገና መች ጀመርኩትና?! ኋላ ስንቀዠቀዠ ቤቱ ሄድኳ። ምነው ፈጣሪ ምነው ሳምንህ ጉድ ሠራኸኝ? ስል አለቀስሁ። ስለትህን አጉድዬ አውቃለሁ? የምበላው ባጣ እንኳ አሥራትና መባህን ነክቼ አውቃለሁ? ውለታ አታውቅም? አምላክ አይደለህም ተንደርድረህ ከሰው ልታንስ ነው? ምነው እኔን እንዳሻህ ብታደርገኝ? ምነው ልጆቼን ብትተውልኝ?” አልኩት። ሞኝ፣ የሞኝ ዘር አይደለሁ? ...የሰማኝ መሰለኝ። “አይዞህ
ያለኝ መሰለኝ። “ይቅርታህን! የዛሬን ብቻ እለፈኝ ትቼሃለሁ” ያለኝ መሰለኝ። “ታርቀናል” ብዬ እንባዬን ጠርጌ ተነሣሁ። ቤት ስደርስ ያቺ ወረግቡ ሚስቴ ስታምጥ ደረስኩ። ቀበቶዬን አላልቼ የምትሰጥም አንተ፤ የምትነሣም አንተ ተመስገን!” አልሁት። ክፋቱን ረሳሁለት። ሚስቴ ምዉ ሳይጠና ተገላገለች። ቆንጅዬ ወንድ ልጅ በጨርቅ ጠቅልለው አሳቀፉኝ። ሳይደግስ አይጣላም!” ይሉ የለ የእኛ ሀገር ሰዎች? ...ደጋጎቹ። “መከራዬን አይተሃልና ኀዘኔን በሳቅ፣ ለቅሶዬን በደስታ ቀይረሃልና” ስል ስሙን ካሣ አልኩት። የካሠኝ መስሎኝ! አይ ደንቆሮ፣ የደንቆሮ ዘር ...ቶሎ አይነቃም እኮ።

ያዋለደችው ሴት በደስታ የምሆነውን ሲያሳጣኝ ፊቷን ጨምታ ስታየኝ ጠረጠርኩና ጨርቁን ገለጥሁት። በእጆቹም በጣቶቹም ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች አሉ። ስድስተኛ ሆነው የበቀሉት እንደሌሎቹ ጠንካራ ስላልሆኑ ወዲያና ወዲህ ተንከርፍፈዋል። ደነገጥሁ። ከማዘን ማበድ ቀረበኝ። ጣቱ ስድስት መሆኑ አይደለም፤ ነገረ-ሥራው ገርሞኝ እንጂ። የታላቁን አራት ጣት ነሳኸኝ ብዬ “ምነው?” ስላልኩት ካሣ ላይ መመለሱ ነው? ይሄ ቀልድ እንጂ ሌላ ምን ይሆናል? ድርቅ በጎርፍ ይካሣል? ሥርጉዳት በእባጭ ይሣሳል? ኧረ እንዲህም አድርጎ ቀልድ የትም የለ!”