Get Mystery Box with random crypto!

ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም ....የቀጠለ ሽማግሌው የግራ ጆሯቸ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም
ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም

....የቀጠለ

ሽማግሌው የግራ ጆሯቸውን፤ ከፊቶች አንዱን እያከኩ ተነሡ።

“እንግዲህ ሰማንህ ዕድሉ። ለሰሚ የቸገረ ነገር ነውና የሸንጎውን ሐሳብ አድምጠን ፍርዱን ለዋናው ዳኛ እንሰጣለን። ፈጣሪና መጥረቢያ አጥፍተዋል። ፍርድ ይገባቸዋል? የምትል እጅህን አውጣ ተብለሃል!”

ማንም ሰው እጁን አላወጣም። ዕድሉ ይባስ ከፋው። ከዚህ ሁሉ በደሉ ጀርባ ዓለም ያሴረ መሰለው።

“ተው አንተ ሸንጎ አንተም እንደምሳር በወደቀ ላይ አትዝመት፣ ተው ንጉሥም ሲያጠፋ አጥፍተሃል ይባል፣ ተው መፈራራት ይቅር፤ ተው ለበዳዮችህ አታቀርቅር፣ ተው ፍርዴን አታጣምም፤ ተው ተፈጥሮን አታሳምም። ተው እውነት እየመረረችህም ጠጣት። ተው የምታሽርህን ጋታት!”

“ፈጣሪና መጥረቢያን ነጻ ናቸው የምትል። ፈጣሪ አይከሰስም! የምትል እጅህን አውጣ ተብለሃል” ሁሉም እጁን አወጣ። ማውጣት ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ በደንብ እንዲያየው ወደ ሰማይ እየተንጠራራ።
ሽማግሌው ወደ ዋናው ዳኛ ዞረው “እንግዲህ ፍርዱን ለእርስዎ ሰጥተናል!” አሉ።
“እንግዲህ ፍረድ ካላችሁኝ ይኸው ፍርዴ። በእውነት ይሄ ሰው ቀላል እፍዳ አላሳለፈም። ፈጣሪም መጥረቢያም በድለውታል። ኧረ እንደውም እስከ ዛሬ እንደዚህ የተበደለ ሰው ገጥሞኝም : አያውቅም። ስለዚህ መጥረቢያው በእጃችን ነው። እንጨቱ ተፈልጦ ማገዶ ይሁን። ብረቱ ሲቃጠል ይኖር ዘንድ፤ ያበላሸውን ይክስ ዘንድ ተቀጥቅጦና ቀልጦ የተበሳ ሰታቴ ወይ ላመፈጅ ይጠገንበት። ፈጣሪም ካለበት ተይዞ “ዕድሜ ይፍታሕ” እንዲታሰር ፈርጃለሁ። ይዞ ላመጣውም ያሻውን ያህል የምትታለብ ጥገት፤ ሮጦ የደረሰበትን ያህል ጋሻ መሬት፤ ልቡ የፈቀደውን ያህል ሚስትና እቁባት ይሸለም ዘንድ ፈርጄያለሁ። ይግባኝ አለኝ! የሚል ተከሳሽ ከተያዘ በኋላ ማሰማት ይችላል። ጨርሼያለሁ!”

ዕድሉ ቀና በአዛውንቱ ቅንነት እየተደነቀ አመስግኖ ወረደ። ሕዝቡም ገጸበረከቱ እያጓጓው፤ ፈጣሪን በየመቅደሱ በርብሮ ሊያገኝ ተመመ። “ፈጣሪ” ያልነው ማንን ነው? ዳኛውም ማንንም ሳያስከፋ ሸንጎውን መበተኑን ለሚቀጥሉት ብዙ ዓመታት በኩራት ሊያወራ ከግንባሩ ግራ እስከ አገጩ ከተዘረጋው፤ በከንፈሩና በዓይኑ ከሚቋረጥ ጠባሳው ጋር አንከስ አንከስ እያለ ወደ ቤቱ አዘገመ። ተከሳሽ በሌለበት ከሳሽ ሙግቱን ቢረታ ማነው ያሸነፈው?

ድሕረ “ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም”

የዕድሉ መጥረቢያ እጀታ ተፈልጦ በጋመ እሳት ውስጥ ገባ። እንደ ትዝታ በትናንሽ ዓይኑ የሚያፈጥ እንጀራ ለመጋገር ከሌሎች እንጨቶች ጋር አበረ። ሚስቱ ሰው ጠርቷት በወጣችበት ኩሽናው በእሳት ተያያዘ። በቀላል ሊያጠፉት አልቻሉም። እሳቱ እንደሰደድ ተዛምቶ የአዝማሪው ሐዋዝንና ሌሎች ሦስት ቤቶችን አወደመ። ሚስቱ ስትጠየቅ “እንዲህ በፍጥነት የሚዛመት እሳት አይቼ አላውቅም! ይኸማ የፈጣሪ ቁጣ ነው!” ትላለች። በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው የተኙት እትዬ ተዋቡ በእሳቱ ተቃጥለው ሕይወታቸው አለፈ። ዕድሉ ሞታም ሰው መፍጀት ያልተወችውን መጥረቢያው ውስጥ ዕጣ ፈንታው እያወካ የሚስቅበት መሰለው። ከሰማይ፣ ከምድሩም እንደተጣላ ጠረጠረ። “እንጀራ እበላበታለሁ” ባለበት አንድ መጥረቢያ ጦስ ሕይወቱ ምስቅልቅል ሲል መታገስ አልቻለም። ሞቱን አልፈራም። እየተበደሉ ይቅር አለማለት ዞሮ ራሱን ተገተገው። “ተበድለህም ይቅርታ መጠየቅ ምን ማለት ነው?” ...ልጆቹን ሳያሳድግ መሞቱ እያንገበገበው አጣጣረ። ከሰውም፣ ከአማልክትም መታረቅ የማይችል ቂም ቋጥሮ ሳይበረክት በተወለደበት አልጋ ላይ ሞት ተገናኘው።

ልክ ነፍሱ ስትወጣ

አንዳንዶች “መጣሁልህ! ምን ልታደርገኝ እንደሆን አይሃለሁ?!” ብሏል
ይላሉ።

አንዳንዶች “ይቅር በለኝ?! እኔም ይቅር ብዬሃለሁ!” ብሏል ይላሉ።

ሚስቱ ግን ዛሬም ድረስ ዕድሉን ሲያነሡባት ልጆቿን ታቅፋ አምርራ ታለቅሳለች።

“እንግዲህ አይዞሽ! ፈጣሪ የወደደውን ነው
የሚጠራው!”
አሉ ሰባኪው ሾላ።

ጤናው እብዱ ከነግሣንግሡ እያለፈ ሳቀ። ረዥም ሳቅ ሳቅ ...ሁሌ እንደሚስቀው የልግጫ ሳቅ ሳቀ። “ታዲያ ፈጣሪ ሲጠራ፤ እንዳንከራተተ ነው እንዴ? ሳይክስ? ሳይዳስስ?”

@Zephilosophy
@Zephilosophy