Get Mystery Box with random crypto!

ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም ደራሲ-ሄኖክ በቀለ መፅሀፍ- ሀገር ያ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም
ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም

ደራሲ-ሄኖክ በቀለ
መፅሀፍ- ሀገር ያጣ ሞት

እዚህ ሀገር ውስጥ መቃብራቸው ሊማስ አንድ ሐሙስ የቀራቸው፤ ሕይወትን በዓይናቸው ቂጥ ገላምጠው የጨረሱ፤ “ፍርድና ርትዕ ዘልቋቸዋል” የተባሉ አዛውንት የሚፈርዱበት በሰንበት አንዴ የሚቆም ሸንጎ አለ። በዳይና ተበዳይ ተጠፍረው ይቀርቡና ይካሰሳሉ። በዳይም፣ ተበዳይም የመጡበትን ተናግረው የተሰጠውን ፍርድ ተቀብለው አመስግነው ይሄዳሉ።

ዕድሉ ቀና “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ!” በሚል ማኅበረሰብ መሃል እየኖረ —ሰማይ ሊያርስ ንጉሥ ሊከስ እንባውን እያዘራ ደረሰ። ነታባ ጋቢ የለበሱ ዳኞች በሸንጎው መሃል ተሰይመዋል። ተከሳሽና ከሳሽ፤ ወሬ ሊያጦለጡል የመጣ የሀገር ሰው፤ ከወደቀው ዋርካ ጀርባ ተንቋጠው አሰፍስፈው ገቢር የሚቀላውጡ ሕፃናት ቦታውን ሞልተውታል።

ሸንጎውን የሚመሩት ሽማግሌ ከተቀመጡበት ብድግ ብለው ሁሉም ዝም እንዲል እጃቸውን እያወዛወዙ ምልክት ሰጡ። ሽማግሌው ፊታቸው በሽብሽባት የተፈሰፈሰ አሮጌ ቦርሳ የመሰለ፤ ድክም ፍዝዝ ብለው ዓይኖቻቸው ብቻ የነቁ፤ ጭብጥ የምታህል አናታቸው ላይ ግራና ቀኝ ትላልቅ ጆሮዎቻቸው ተሰፍተው ሦስት ፊት እንዳላቸው ነገር የሚያስቱ፤ ከወገባቸው ጎበጥ ያሉ ሰው ናቸው።

“ክስ ያለህ ቅረብ ተብለሃል!” አሉ ባለች በሌለች አቅማቸው ጅንን ብለው። ከልባቸው አበጥ ስላሉ ይሆን ከወገባቸው ጎበጥ ያሉት?

ዕድሉ ተንደርድሮ ከሳሽ የሚቆምበት ጉብታ ላይ ተሰየመ። “ይህ ሁሉ ነሆለል የተሰበሰበው “ሚስቴን ወሸሙብኝ”፤ “በሬዬን ነዱብኝ”፤ “አጥሬን ደፈሩብኝ” ሊል አይደል? እንደእኔ የተበደለ በድፍን ሀገሩ ቢታሰስ አንድ ይገኛል? ...ኧረ እንዲያውም!”

ዕድሉ ቀና ለወትሮው ክስና ክርክር ባለበት የማይደርስ፤ ከምድርም ከሰማይም የተስማማ፤ ቢበድሉት ውጦ ቢወጉት ደምቶ ዝም የሚል ጭምት ነበር። ዛሬ የከሳሽ ጉብታ ላይ ቆሞ ሲታይ የሸንጎው ታዳሚ ጸጥ እረጭ ብሎ አፈጠጠ። ሸንጎውን የሚመሩት ሽማግሌ ብቻ ደስ አላላቸውም ። ዕድሉ በዕድሜ የሚበልጡትን ከሰሾች ገፈታትሮ መቅደሙ አበሳጭቷቸው ይሁን፤ ወይ የስልጣናቸውን  አቅም የሚያሳዩበት ምቹ ጊዜ ጠብቀው ስላገኙ ይሁን..

“ተከሳሾችህን ወደ ፊት ጥራ ተብለሃል!”

ዕድሉ ቀና ከከሳሽ መደቡ ላይ ፈንጠር ብሎ ወረደ።
ለተከሳሽ የተዘጋጀው ክብታ ላይ ደርሶ በእጁ የያዛትን መጥረቢያ አስቀመጣት። የተሰበሰበው የሀገር ሕዝብ ሁኔታውን በግራ መጋባት ይከታተላል።

“ተከሳሾቼ ሁለት ናቸው። አንዱ ይኸው! ይሄ መጥረቢያ ነው። ሁለተኛውን እንኳ የት እንዳለ አላውቅም። ብጠራው አይመጣም። ብቆጣው አይፈራም። በሰው ሕግ አይመራም። “ተወኝ! ስለው ይስቅብኛል። ምን እንደበደልሁት እንጃ ብቻ ሰባት ሰማያዊ ጋቢ ለብሶ እያደፈጠ ያጠቃኛል። ባለክንፍ አሽከሮች፣ የገዘፉ አዝማቾች፣ እልፍ ነጫጭ ሎሌዎች አሉት...”

“ማሸሞሩን ትተህ ምናል ብትናገር?” ሽማግሌው ትዕግስት አጥተው ይቅበዘበዛሉ።

“እንደውም ሁለተኛው ተከሳሽ ፈጣሪ ነው።”

ዙሪያውን ከቦ የተዘለለው የሀገር ሰው ቦታውን በቱማታ አተረማመሰው። እዚያም እዚህም የተቆጡ ሰዎች በዕድሉ ድፍረት ተለኩሰው መንቦግቦግ ጀመሩ። አንዳንዱ ፈጣሪ ለእዚህ የንቀት ንግግር እዚያው በመብረቅ እንዳያደባያቸው ይለምናል። እስከነተረቱስ “ለኃጥአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል!” ይሉ የለ? አንዳንዱ “ዕድሉ መወገሩ አይቀርም!” በሚል ተስፋ ሹል ባልጩት ፍለጋ በዓይኑ ይማትራል። አንዳንዱ ዓይናቸው ሥር ላበደው ዛፍ ቆራጭ ከንፈር ይመጥጣል። ከዋርካው ጀርባ ያደፈጡ አመዳም ሕፃናት ምን እንደተከሰተ ለመቅለብ ጆሮዎቻቸውን ዘርግተው ይቀላጠፋሉ።

ዕድሉ ድምፁ በጩኸት ማዕበል ተውጦ ምን እንደሚል አልተሰማም እንጂ፤ የሀገር ሰው ቁጣ ምንም ሳይመስለው ኃይለቃል እያወራ ይውረገረጋል።

ሽማግሌው ሕዝቡን እንደምንም ዝም አሰኝተው ወደ ዋናው ዳኛ ዞሩ። ፊታቸው ላይ ወፍራም ቁጣና ቀጭን ደስታ እኩል ተሸርቧል። በሰው ፊት ያዋረዳቸው ይህ ሰው አፍታ ሳይቆይ የሞቱን መግነዝ በራሱ እጅ ስለፈተለ ከንፈራቸው ላይ የታፈነ ፈገግታ ያጣጥራል።

“ምን ይላሉ እርስዎ?”

ዋናው ዳኛ ፊታቸው ላይ የተጋደመውን ጠባሳ ቆርጣ የምትስለመለም ዓይናቸውን አጨንቁረው “እስቲ እንስማው?! መቼም አይገድለን...” አሉ። ቁጣ ያደበላለቀው ሸንጎ ከዕድሉ ድፍረት በላይ በዳኛው ውሳኔ ተደናገጠ። ፊቶች ወዛቸው ተመጦ ተቁለጨለጩ። እንኳን ፈጣሪን ያህል ነገር ተከሶ ወትሮም ግራና ቀኝ ማገናዘብ አልተለመደም። ዋናው ዳኛ ከእዚህ በፊት ሸንጎ ረግጠው የማያውቁ ለሄላ-ገነት በቀረበው ሀገር በኩል የሚኖሩ ሽማግሌ ናቸው። በሰው በሰው ጠቢብነታቸው የሀገር ሸንጎ ጠሪዎች ጋር ደርሶ ተፈልገው የተገኙ ስለነበሩ ሕዝቡ እያጉረመረመም ቢሆን ትዕዛዛቸውን ተቀበለ።

ሽማግሌው እየቀፈፋቸው ወደ ዕድሉ ዞረው “ቀጥል ተብለሃል!” አሉ። የጎበጠ ጀርባቸው ተቃና። ያበጠች ልባቸው ፈርጣ ይሆን?
ዕድሉ ጉሮሮውን ጠራርጎ፤ ለፍልሚያ እንደሚዘጋጅ ሰው ሰውነቱን አፍታቶ ቀጠለ።

“እንግዲህ ክሴን ስሙት። ይህቺ መጥረቢያና ፈጣሪ በደካማ ጉልበቴ ገብተው በድለውኛል። በማይመጣ መጥተውብኛል። ካደፈጠ አውሬ፤ ከተሰበቀ ጦር፣ በክፉ ከሚያይ ጎረቤት ሸሽጌ ለወግ ትብቃ ያልኳት ልጄን ገድለውብኛል። እውነት እዚህ ሀገር ፍትሕ ካለ በእዚህ እንዲጠየቁልኝ ነው የምሻው።”
አንዱ ቁጣው ያልበረደ ወጣት ብድግ ብሎ...

“ምነው? ምነው ዕድሉ ምነው? ሰብሉ ሰምሮ፤ አዝመራው አሽቶ፤ ጠላት ደሞ በደጅ ቆሞ እያጓራ እያየህ ሲሆን ሲሆን ማመስገን ሳይሆን በንስሓና በጸሎት መትጋት ሲገባህ፤ ደረትህን ገልብጠህ ከአምላክ ጋር እኩል ቤት ትገጥማለህ? ምናል መቅሰፍት ባትጠራብን?!!”

ዕድሉ ቀና የወጣቱ መልስ እንደ አንዳች እያደረገው ከአፉ ላይ ነጥቆ ቀጠለ።

“ዝምበል!
“ያልተነካ ግልግል ያውቃል! ማለት እንደአንተ ዓይነቱን ነው። የራስህ ጉዳይ! የልጄን ደም ጠጥቶ የበቀለ አዝዕርት ምን ይረባኛል? ለምን ያሸተውን ጠራርጎ ነቀዝ አያነቅዘውም። ለምን አንበጣና ተምች አያደብነውም?! ሆድ ቢሞላ የልጄን ክብልል ዓይን ይሆነኛል? ጠግቤ ባገሳ የአንገቷን ሽታ የአንገቷን ሽታ ይለኛል? ምነው ደኅና ሰው ነህ ስልህ እንዲህ ቀለልህ?!”

ይቀጥላል...

@Zephilosophy
@Zephilosophy