Get Mystery Box with random crypto!

ዓርብ ጠዋት! ግንቦት 4/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ምርጫ ቦርድ ከሦስት ዓመታት | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ዓርብ ጠዋት! ግንቦት 4/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ምርጫ ቦርድ ከሦስት ዓመታት በኋላ በመቀሌ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን ትናንት እንደገና ከፍቶ ሥራ ማስጀመሩን ቪኦኤ ዘግቧል። ቦርዱ ወደ መቀሌ የላካቸው ባለሙያዎችም ከትግራይ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮችና መገናኛ ብዙኀን ጋር እንደተወያዩ ዘገባው ጠቅሷል። ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ከሦስት ዓመታት በፊት በተናጥል ያካሄደውን ክልላዊ ምርጫ ውድቅ ያደረገ ሲኾን፣ በቀጣዩ ዓመት የክልልና የፌደራል ምክር ቤቶች ምርጫ እንደሚያካሄድ ሰሞኑን እንደተገለጠ ይታወሳል።

2፤ ጅዳ ውስጥ ንግግር ላይ የሰነበቱት ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የሰብዓዊ ዕርዳታ መስመሮችን ለመክፈት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የውጭ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። ሁለቱ ወገኖች ሲቪሎችን ከጥቃት ለመጠበቅ እና ተዋጊዎቻቸውን ከሆስፒታሎችና ሌሎች ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ ለማስወጣትም እንደተስማሙ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ኾኖም ተፋላሚዎቹ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ተብሏል።

3፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳን ለተመድ ሰብዓዊ መብት ባለሙያ ተጨማሪ ሃላፊነቶችን ሰጥቷል። ተቆጣጣሪ ባለሙያው ባሁኑ ወቅት በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት መካከል በቀጠለው ግጭት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጭምር እንዱከታተሉና ሪፖርት እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ አዟል። ምክር ቤቱ ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆምና ሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲኾንም ጠይቋል። ምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳቡን ያጸደቀው፣ በ18 ድጋፍ፣ በ15 ተቃውሞ እና በ14 ድምጸ ተዓቅቦ ነው።

4፤ ኬንያ በግዙፎቹ ዳዳብ እና ካኩማ የስደተኛ መጠለያዎች የተጠለሉ ስደተኞች ወደ አገሬው ኅብረተሰብ እንዲቀላቀሉ ወስናለች። አዲሱ ፖሊሲ ስደተኞች ከመንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል ሲኾን፣ ዳዳብ እና ካኩማ መጠለያዎችም ወደ ማዘጋጃ ቤት ደረጃ እንደሚያድጉ የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኬንያ መንግሥት ከ200 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙባቸው ሁለቱ መጠለያዎች የጸጥታ ስጋት እንደደቀኑ በመግለጽ፣ ጨርሶ እንደሚዘጋቸው ላለፉት ዓመታት ሲዝት እንደነበር ይታወሳል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja