Get Mystery Box with random crypto!

ዓርብ ምሽት! ግንቦት 4/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ዓርብ ምሽት! ግንቦት 4/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አሻሽሎ ያጸደቀው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ የጥቅማ ጥቅምና ጡረታ መብት ጥያቄያችን አልመለስም በማለት ቅሬታቸውን ለዋዜማ ገልጸዋል። ፓርላማው በረቂቅ አዋጁ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት፣ የቀድሞው ጦር ሠራዊት አባላት ከውጊያ ሜዳይ አሰጣጥና የጡረታ መብት አጠባበቅ ዙሪያ የሠራዊቱ አባላት መብት እንዲካተት ጠይቀው ነበር። ኾኖም የጸደቀው አዋጅ፣ የቀድሞው ሠራዊት አባላት ላነሷቸው የጡረታ መብትና ሜዳይ አሰጣጥ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥ በመቅረቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የሠራዊቱ የድጋፍና ልማት ማኅበርና አባላቱ ተናግረዋል።

2፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስምንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለባቸው አሞኜ ዛሬ ቢሯቸው ውስጥ "የዕለት ተለት ተግባራቸውን" በማከናወን ላይ እንዳሉ ከጧቱ አራት ሰዓት ላይ በሽጉጥ እንደተገደሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሥራ አስፈጻሚውን ገድሏል ተብሎ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካዛንቺስ አካባቢ የማኅበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት አባል እንደኾነ ኮሚሽኑ ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ ተጠርጣሪው በዋና ሥራ አስፈጻሚው ላይ ግድያውን የፈጸመው፣ ለወረዳው አስተዳደር ያመለከትኩት የግል ጉዳዬ "እንዳይፈጸም የከለከልከው አንተ ነህ" በማለት ሟቹን ተጠያቂ በማድረግ ነው ብሏል። ተጠርጣሪው የወረዳው አስተዳደር አልፈጸመልኝም ያለው የግል ጉዳዩ ምን እንደኾነ ግን ኮሚሽኑ አላብራራም።

3፤ ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የአገሪቱ ዓለማቀፍ የልማት አጋሮች ግልጽ ቃል ኪዳን በቡድን-20 ማዕቀፍ ውስጥ የአበዳሪዎች የፋይናንስ ድጋፍ ማረጋገጫ ያስፈልጋል በማለት የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጁሊ ኮዛክ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸውን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። ድርጅቱ ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ መርሃ ግብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ በሚችልበት ኹኔታ ዙሪያ እስካኹንም ከአገሪቱ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ መኾኑን ቃል አቀባይዋ መጥቀሳቸውን ዜና ምንጩ አመልክቷል። ኢትዮጵያ በቡድን-20 ማዕቀፍ ስር የውጭ ዕዳ ክፍያ ሽግሽግ እንዲደረግላት የጠየቀችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢትዮጵያ የዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት 2 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዲሰጣት መጠየቋን ሮይተርስ ባለፈው ወር መዘገቡ ይታወሳል።

4፤ አንጋፋዋና ዝነኛዋ ድምጻዊት ኂሩት በቀለ በ83 ዓመቷ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየች የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኂሩት ከ1953 ዓ፣ም ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኖችን የተጫወተች ተወዳጅ ድምጻዊት ነበረች። ድምጻዊት ኂሩት ወደ መጨረሻው የሕይወት ዘመኗ ገደማ ዓለማዊ ሙዚቃዎችን መዝፈን አቁማ፣ ሐይማኖታዊ መዝሙሮችን ስትዘምር እንደነበር ይታወቃል። ዋዜማ ለአንጋፋዋ ድምጻዊት ኂሩት ቤተሰቦችና ለአድናቂዎቿ መጽናናትን ትመኛለች።

5፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በፕሬዝዳንት ዢ ፑንግ ግብዣ በመጭው ዕሁድ ቻይናን እንደሚጎበኙ የቻይናው ሲጂቲኤን ዘግቧል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ፕሬዝዳንት ዢ ፒንግ፣ የኹለቱን አገራት ግንኙነት ወደ "ስትራተጂካዊ አጋርነት" ለማሳደግ ባለፈው የአውሮፓዊያን ዓመት ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ማስታወሳቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ቻይናባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሾመቻቸው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኳ ኤርትራን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

6፤ በደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ አምባሳደር ሩበን ብሪጌቲ ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ ጦር መሳሪያዎችንና ተተኳሾችን ሰጥታለች በማለት ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መክሰሳቸውን የውጭ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። አምባሳደር ብሪጌቲ፣ ባለፈው ታኅሳስ "ሌዲ አር" የተባለች የሩሲያ መርከብ ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የሰጠችውን ጦር መሳሪያ ከኬፕታውኑ ከደቡብ አፍሪካ ወደብ ጭና ወደ ሩሲያ ስለመጓጓዟ "አሜሪካ ርግጠኛ ናት" ማለታቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። አምባሳደሩ አያይዘውም፣ ደቡብ አፍሪካ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ላይ ይዠዋለኹ የምትለውን "ገለልተኛ አቋም" አለማክበሯ፣ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን "በእጅጉ አሳስቧል" በማለት ተናግረዋል ተብሏል። የአምባሳደሩን ውንጀላ ተከትሎ፣ የፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎዛ ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል። አምባሳደሩ ውንጀላውን ያቀረቡት፣ ደቡብ አፍሪካ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ላይ የያዘችውን አቋም ለአሜሪካ ባለሥልጣናት ለማስረዳት ልዐካን ቡድኗን ወደ ዋሽንግተን በላከች ማግስት ነው።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ2211 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ3055 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 65 ብር ከ2287 ሳንቲም እና መሸጫው 66 ብር ከ5333 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ2366 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ4213 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ0728 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2143 ሳንቲም ተሽጧል ተብሏል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja