Get Mystery Box with random crypto!

ሐሙስ ምሽት! ግንቦት 3/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ብሄራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም ኩባ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሐሙስ ምሽት! ግንቦት 3/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ብሄራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም ኩባንያ አካል ለኾነው ሳፋሪኮም ኤምፔሳ የሞባይል የፋይናንስ አገልግሎት ንዑስ ኩባንያ የገንዘብ መገበያያና መላላኪያ አገልግሎት "ኤምፔሳ" እንዲጀምር ፍቃድ ሰጥቷል። ሳፋሪኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ የሞባይል ገንዘብ መገበያና መላላኪያ አገልግሎት ፍቃድ በማግኘት የመጀመሪያው የውጭ ኩባንያ ኾኗል። ኩባንያው የ"ኤምፔሳ" አገልግሎቱን ከተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት በፊት እንደሚጀምር የኬንያው ቢዝነስ ደይሊ ኩባንያውን ጠቅሶ ዘግቧል። ሳፋሪኮም ኬንያ ውስጥ "ኤምፔሳ" የጀመረው ከ15 ዓመታት በፊት ሲኾን፣ ባሁኑ ወቅት በኬንያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከ50 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አሉት።

2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለሚያስገነቡት አዲስ ቤተመንግሥት ተጨማሪ ሦስት ተቋራጮች መቅጠራቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። የ"ጫካ" ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪው 49 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ሲገለጽ የቆየ ሲኾን፣ የምዕራባዊያን ዲፕሎማቲክ ምንጮች ግን ወጪው 850 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል በመናገር ላይ ናቸው። ፕሮጀክቱ በ503 ሔክታር ላይ የቅንጡ መኖሪያና መዝናኛ መንደሮችንና ሦስት ሰው ሠራሽ ሐይቆች ግንባታ ያካተተ ሲኾን፣ ግንባታው የሚካሄደው በየካ ክፍለ ከተማ የካ ተራራ ግርጌ ነው። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን እስካኹን የ29 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ አካሂዷል።

3፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተወሰኑ የግል ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ ዓመት እናደርገዋለን ባሉት የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ዙሪያ ከወላጆች ጋርመግባባት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ሪፖርተር ዘግቧል። የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ለማድረግ ከወሰኑት 1 ሺህ 253 ትምህርት ቤቶች መካከል፣ 1 ሺህ 31 ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ጋር ባደረጉት ውይይት 20 በመቶ ጭማሪ ብቻ ለማድረግ መግባባት ላይ እንደደረሱ የከተማዋ የትምህርት ሥልጠናና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዛሬ በሰጠው መግለጫ መናገሩን ዘገባው አመልክቷል። ባለሥልጣኑ የግል ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ ዓመት ከወርሃዊ ክፍያ ውጭ በዓይነትም ኾነ በገንዘብ የክፍያ ጭማሪ ማድረግ አይችሉም ማለቱ ተገልጧል። የግል ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ጋር የተወያዩት፣ ከ20 እስከ 100 ፐርሰን የሚደርስ ጭማሪ ለማድረግ መወሰናቸውን ለባለሥልጣኑ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው።

4፤ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የቁጫ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካዮች የኾኑ ሦስት የክልሉ ምክር ቤት አባላትን ከግንቦት 1 ጀምሮ ከአባልነት መሰረዙን የጋሞ ዞን ኮምንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። ሦስቱ የፓርቲው ተወካዮች ከምክር ቤቱ አባልነት የተሰረዙት፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ እና ምርጫ ቦርድ በፍርድ ቤት ሲያካሂዱት የቆዩትን ክርክር መሠረት በማድረግ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በቁጫ ምርጫ ክልሎች በድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ በወሰነው መሠረት መኾኑን ቢሮው ገልጧል። ከክልሉ ምክር ቤት አባልነት የተሰናበቱት የፓርቲው ተወካዮች፣ ጌዲዮን ጌታቸው፣ ማሳሞ ማዳልቾ እና ሊዲያ በለጠ ናቸው። በጋሞ ዞን በሁለት ወረዳዎች የሚኖረው የቁጫ ሕዝብ ለዓመታት ሲያነሳው የቆየውን የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያስገባ ሲኾን፣ ምክር ቤቱ ግን እስካኹን በጥያቄው ላይ ውሳኔ አልሰጠም።

5፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የሱዳኑ ግጭት ባስከተለው ሰብዓዊ መብት ተጽዕኖ ዙሪያ መክሯል። የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ "ጾታዊ ጥቃትና ግድያ" እንደሚፈጽሙ ገልጸው፣ ተፋላሚዎች የጦርነት ሕግጋትን እንዲያከብሩ ጠይቀዋል። ተርክ፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት በሰላማዊው ሕዝብ መኖሪያዎች ላይ የአየር ድብደባዎችን መፈጸሙንና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱም በሲቪሎች ሠፈሮች መሸጎ እየተዋጋ መኾኑንም ገልጸዋል። በተፋላሚ ወገኖች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ አገራት ሀሉ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት እንዲያደርጉ ተርክ ተማጽነዋል።

6፤ ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ ውስጥ ሲያደርጉት የሰነበቱት የቅድመ-ድርድር ንግግር አበረታች ውጤት ማሳየት መጀመሩን ሮይተርስ አደራዳሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል። ተፋላሚዎቹ ወገኖች በቅርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው አመልክቷል። የጅዳውን ንግግር የሚመሩት፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና አሜሪካ ናቸው።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ2167 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ3010 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 65 ብር ከ3270 ሳንቲም እና መሸጫው 66 ብር ከ6335 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ3890 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ5768 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja