Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ጠዋት! ግንቦት 2/2015 ዓ.ም የEMS ዋናዋና ዜናዎች 1፤ ሕገመንንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ረቡዕ ጠዋት! ግንቦት 2/2015 ዓ.ም የEMS ዋናዋና ዜናዎች

1፤ ሕገመንንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመገልበጥ አሲረዋል ተብለው በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች ላይ ትናንት መርማሪ ፓሊስ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14 ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው መጠየቁን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው፣ መርማሪ ፖሊስ ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረበውን ምክንያት ደግሞ አቅርቦታል በማለት፣ ችሎቱ ጥያቄውን እንዳይቀበል እንዲኹም የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ክስ በመገናኛ ብዙኀን አዋጅ መሠረት እንዲታይ እንደጠየቁ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ችሎቱ ግራ ቀኙን መርምሮ ዛሬ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል። ትናንት ችሎት ከቀረቡት መካከል፣ ጅቡቲ ላይ ተያዘ የተባለው የበይነ መረብ ጋዜጠኛው ጎበዜ ሲሳይ እና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ይገኙበታል።

2፤ ዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት እስካለፈው ሰኞ 15 ሺህ ከሱዳኑ ግጭት የሸሹ ሰዎች በመተማ በኩል ኢትዮጵያ መግባታቸውን በትዊተር ገጹ አስታውቋል። ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ሰዎች የተለያዩ ድጋፎችን እየሰጠ መኾኑን ገልጦ፣ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ግን ተጨማሪ የገንዘብ ዕርዳታ እንደሚፈልግ ገልጧል። ከሱዳን በመተማ በኩል የሚገቡት፣ ኢትዮጵያዊያን ተመላሾች፣ ሱዳናዊያን ስደተኞችና የሌሎች አገራት ዜጎች እንደኾኑ ድርጅቱ ቀደም ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።

3፤ የሳፋሪኮም ኩባንያ የሞባይል መገበያያ ዘዴ "ኤምፔሳ" ገንዘብ ላኪዎች ስማቸውንና ስልክ ቁጥራቸውን ከገንዘብ ተቀባዩ እንዲደብቁ የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የኬንያው ቢዝነስ ደይሊ ድረገጽ ዘግቧል። ኩባንያው አዲሱን አሠራር የጀመረው፣ በ"ኤምፔሳ" ላይ የሚፈጸሙ የዲጂታል ማጨበርበርና የግል መረጃ ሥርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል እንደኾነ መግለጡን ዘገባው አመልክቷል። ኾኖም የአዲሱ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ተጨማሪ የገንዘብ መላኪያ ታሪፍ እንደሚከፍሉ ተገልጧል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ፣ "ኤምፔሳ" ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎቱን እንዲጀምር በቅርቡ ፍቃድ እንደሚሰጥ ባለፈው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል።

4፤ ዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት ሱማሊያ ውስጥ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ ለሚያልፉ በሺዎች ለሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ፍልሰተኞች ከሰኔ በፊት 3 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን ካላገኘ፣ በሱማሊያ በኩል ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለሚሻገሩ በዓመት 50 ሺህ ያህል ፍልሰተኞች የምግብ፣ ሕክምናና ሕይወት አድን ድጋፎችን መስጠት እንደማይችልና ቦሳሶ እና ሐርጌሳ የሚገኙ ማዕከሎቹንም ለመዝጋት እንደሚገደድ ገልጧል። በሱማሊያ በኩል ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት የሚሻገሩት ሕገወጥ ፍልሰተኞች አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

5፤ የሱማሊያዋ ፑንትላንድ ወታደሮች "ደመወዝ አልከፈለንም" በማለት በራስ ገዟ መንግሥት ላይ ማደማቸውን ጋሮዌ ድረገጽ ዘግቧል። አድመኞቹ ወታደሮች የፑንትላንድ ዋና ከተማ ጋሮዌን መውጫና መግቢያ ከፊል መንገዶችንና ጋሮዌን ከቦሳሶ ወደብ ጋር የሚያገናኘውን አውራ ጎዳና መዝጋታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ወታደሮቹ አድማ የመቱት፣ የሥልጣን ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት የራስ ገዟ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ ከአካባቢ ምርጫና ከሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከፍተኛ ውጥረት በገቡበት ወቅት ላይ ነው። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja