Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ምሽት!ግንቦት 2/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ረቡዕ ምሽት!ግንቦት 2/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) በሠራተኞች ጥያቄዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ለመወያየት ጥያቄ ማቅረቡን ሪፖርተር ዘግቧል። ኢሠማኮ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የሠራተኛው የኑሮ ኹኔታ መፍትሄ ለመፈለግ "ብቸኛው አማራጭ ጠቅላይ ሚንስትሩን ማነጋገር ነው" ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ኢሠማኮ፣ የሠራተኞች የደመወዝ ግብር እንዲቀነስ፣ ከታክስ ነጻ የደመወዝ ወለል ከ600 ብር ከፍ እንዲልና አነስተኛ የምግብ ፍጆታዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲኾኑ ለገንዘብ ሚንስቴር ደብዳቤ መጻፉም በዘገባው ተመልክቷል። ኢሠማኮ በዓለም ወዛደሮች ቀን ላይ የሠራተኞችን ጥያቄ ለማስተጋባት የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዳገደው መግለጡ ይታወሳል።

2፤ ምርጫ ቦርድ በትግራይና ምርጫ ባልተካሄደባቸው የሌሎች ክልሎች አካባቢዎች ለሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ለማካሄድ ለመንግሥት የበጀት ጥያቄ አቅርቤያለሁ ማለቱን ሪፖርተር ዘግቧል። ቦርዱ ከትግራይ በተጨማሪ፣ በኦሮሚያ፣ አማራና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ለክልል እና ፌደራል ምክር ቤቶች ምርጫ ባልተካሄደባቸው የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች በቀጣዩ ዓመት ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑን መግለጡን ዘገባው ጠቅሷል። ቦርዱ በተጠቀሱት ክልሎች በሚገኙ ምርጫ ክልሎች በአገራዊው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ምርጫ ሳያካሂድ የቀረው፣ በጸጥታ መጓደልና በፖለቲካዊ ምክንያቶች እንደነበር በወቅቱ መግለጡ ይታወሳል።

3፤ መንግሥት "በሽብር ወንጀል" እፈልጋቸዋለኹ ያላቸው አንጋፋው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ክስ ከተመሠረተብኝ ክሱን ለመከላከል ከአሜሪካ "ወደ አገር ቤት እመለሳለኹ" ማለታቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ልደቱ እስከ ትናንት ድረስ ክስ እንዳልተመሠረተባቸው ከጠበቃዬ ተረድቻለኹ ማለታቸውን የጠቀሰው ዘገባው፣ ባኹኑ ወቅት አሜሪካ ውስጥ የሕክምና ክትትል ላይ እንደኾኑ መግለጣቸውን ጠቅሷል። ልደቱ፣ መንግሥት የሽብር ክስ ሊመሠርትብኝ የፈለገው በፍራቻ ወደ አገሬ እንዳልመለስ ለማድረግ ነው ማለታቸውንም ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። የጸጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይል፣ በውጭ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ከዓለማቀፉ የፖሊስ ተቋም ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት አደርጋለኹ ማለቱ ይታወሳል።

4፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከጅቡቲ ተያዘ የተባለውን የበይነ መረብ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ በስድስት የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት መፍቀዱን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ችሎቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ ያደረገው፣ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ባስተባበሩት "የሽብር ድርጊት በርካታ ንጹሃን ዜጎች እንዲሞቱና ንብረት እንዲወድም ኾኗል" በማለት ያቀረበውን አቤቱታ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል።

5፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት በካርቱም ተከታይ የአየር ድብደባ መፈጸሙንና ውጊያው ተባብሶ መቀጠሉን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት፣ የሱዳን አየር ኃይል በፕሬዝዳንታዊ ጽሕፈት ቤቱ ላይ የአየር ድብደባ ፈጽሟል በማለት ከሷል። በከተማዋ ሕግና ሥርዓት መፍረሱንና ዝርፊያ መንሠራፋቱንም የተለያዩ የዜና ምንጮች አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን አገራቸው በተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚካሄድ ኹሉን ዓቀፍ ንግግር ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ለሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን በስልክ እንደገለጡላቸው ተዘግቧል። ኹለቱ ተፋላሚ ወገኖች የሰብዓዊ ዕርዳታ መስመሮችን ስለመክፈት ቅዳሜ'ለት ጅዳ ውስጥ የጀመሩት ንግግር፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ አልተቋጨም።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ2086 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ2928 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 65 ብር ከ3068 ሳንቲም እና መሸጫው 66 ብር ከ6129 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ5048 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ6949 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja