Get Mystery Box with random crypto!

ማክሰኞ ምሽት! ግንቦት 1/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ማክሰኞ ምሽት! ግንቦት 1/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የሚካሄደውን ግጭት በድርድርና በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ዝግጁ መኾኑን ዛሬ የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ መናገራቸውን ዶይቸቨለ ዘግቧል። ኾኖም የቢሮ ኃላፊው፣ ታንዛኒያ ውስጥ በፌደራል መንግሥቱ እና በአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በቅርቡ ስለተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የፊት ለፊት ድርድር ሂደትና ውጤቱ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ቀጥተኛ መልስ ሳይሰጡ እንደቀሩ ዘገባው ጠቅሷል። ኹለቱ ወገኖች ቀጣይ ድርድር በማድረግ አስፈላጊነት ላይ እንደተስማሙ መግለጣቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የመንግሥት ጦር ትናንት በምዕራብ እና ምሥራቅ ሸዋ በኩል አዲስ ጥቃት ከፍቶብኛል ሲል ዛሬ ማለዳ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

2፤ ኢትዮጵያ የኬንያን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ኡጋንዳንና ታንዛኒያን በመብለጥ ቀዳሚውን ደረጃ መያዟን ደይሊ ኔሽን አስነብቧል። ከአንድ ዓመት በፊት በነበረው መረጃ፣ የኬንያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገበያ ያፈሰሱት ሙዓለ ንዋይ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ደርሶ እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና የኬንያ ኩባንያዎች ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ በመኾን ታንዛኒያ ቀዳሚዋ እንደነበረች ዘገባው አመልክቷል። ኢትዮጵያ የኬንያ ኩባንያዎች ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ በመኾን የቀዳሚነቱን ደረጃ የያዘችው፣ የኬንያው ሳፋሪኮም የቴሌኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዩን ማፍሰስ ከጀመረ ወዲህ ነው።

3፤ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜ ሽኩሪ ዛሬ ጁባ መግባታቸውን የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ሽኩሪ ጁባ የገቡት፣ የሱዳኑን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚቻልበት ኹኔታ ዙሪያ ከሱዳን ጎረቤት አገራት የሰላም ጥረቶችን ለማስተባበር እንደኾነ ሚንስቴሩ ገልጧል። ሽኩሪ ለሱዳኑ ግጭት መፍትሄ በማፈላለግ ዙሪያ፣ ከደቡብ ሱዳኑ አቻቸው እንዲኹም ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

4፤ በሱዳኑ ግጭት ሳቢያ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 700 ሺህ ማሻቀቡን ዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። እስካለፈው ሳምንት ድረስ በግጭቱ የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች ብዛት 334 ሺህ ገደማ የነበረ ሲኾን፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ግን ውጊያው ጋብ ማለቱን ተከትሎ በርካቶች የውጊያ ቀጠና ከኾኑ ቀየዎቻቸው እንደለቀቁ ተገልጧል። ከ100 ሺህ በላይ ሱዳናዊያን ደሞ ወደ ጎረቤት አገራት በተለይም ወደ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድና ግብጽ እንደተሰደዱ ድርጅቱ በሪፖርቱ ጠቅሷል። ተፋላሚዎቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ መተላለፊያ መስመሮችን ለመክፈት ጅዳ ውስጥ ቅዳሜ'ለት የጀመሩት ንግግር እንደቀጠለ ሲኾን፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ንግግሩ ምን ውጤት እንዳስገኘ የታወቀ ነገር የለም።

5፤ በደቡባዊ ኬንያ ፖል ማካንዚ የተባለ የፕሮቴስታንት ሰባኪ "እየሱስ ክርስቶስን ለመገናኘት ራሳቸውን አስርበው እንዲሞቱ" ካደረጋቸው ከመቶ በላይ ተከታዮቹ የተወሰኑ አስከሬኖች ላይ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች እንደተወሰዱ በምርመራ መረጋገጡን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ኪቱሪ ኩንዲኪ ድርጊቱን "በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ ወንጀል" በማለት እንደፈረጁት የጠቀሱት ዘገባዎቹ፣ ዛሬን ጨምሮ የሰባኪው ቤተክርስቲያን በሚገኝበት ጫካ በተደረገ አሰሳ 133 አስከሬኖች በጅምላ መቃብሮች ውስጥ እንደተገኙ አመልክተዋል። መርማሪ ፖሊስ፣ ድርጊቱ ከሰውነት ክፍሎች ንግድ ጋር የተያያዘና በርካታ ተዋናዮች የተሳተፉበት ወንጀል ሳይኾን እንደማይቀር መግለጡና፣ በሰባኪው ላይ የ"ሽብር ወንጀል" ክስ እመሠርታለኹ ማለቱ ተገልጧል። መንግሥት ወንጀሉን የሚመረምር ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁሟል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ2048 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ2889 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 65 ብር ከ5404 ሳንቲም እና መሸጫው 66 ብር ከ8512 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ8855 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ0832 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja