Get Mystery Box with random crypto!

የቅዳሜ ምሽት!ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም የEMS አጫጭር ዜናዎች 1፤ ኢዜማ ከመንግሥት ጋር ባለው | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የቅዳሜ ምሽት!ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም የEMS አጫጭር ዜናዎች

1፤ ኢዜማ ከመንግሥት ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ጥናት እንዲያደርግ ያቋቋመው ግብረ ኃይል ሪፖርቱን ዛሬ ይፋ እንደሚያደርግ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ሪፖርቱ፣ ፓርቲው ከመንግሥት ጋር የፈጠረው ትብብር ለአገሪቱ ምን ፋይዳ እንዳስገኘ ጭምር የሚዳስስ ሲኾን፣ የእስካኹኑን የፓርቲውን አካሄድ የሚያስቀጥል ወይም ሥር ነቀል የትግል መስመር ለውጥ እንዲደረግ ምክረ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። ፓርቲው ጉዳዩን ለማስጠናት የወሰነው፣ ከመንግሥት ጋር የፈጠረው ቅርርቦሽ ለውስጣዊ አንድነቱና ኅልውናው ስጋት መፍጠሩን ተከትሎ ነበር። የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ በመንግሥት በተሰጣቸው ሹመት ትምህርት ሚንስትር ኾነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

2፤ የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች "በመንግሥት ጸጥታ አካላት ላይ ትንኮሳ" በመፈጸም "የውጭና የውስጥ ኃይሎች መጠቀሚያ" ኾነዋል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። ፌደራል መንግሥቱ በአማራ ክልል ባኹኑ ወቅት እያካሄደው የሚገኘው የሕግ ማስከበር ርምጃ "በጣም ውስን" በኾኑ አካባቢዎች የሚካሄድ መኾኑን የጠቀሰው የክልሉ መንግሥት መግለጫ፣ ክልሉ "ሕዝባዊ እምቢተኝነት" ውስጥ አለመኾኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል። "የተሳሳተ ዓላማ ውስጥ" የገቡ "ጽንፈኛ ግለሰቦችና ቡድኖች" ከድርጊታቸው እንድትቆጠቡና "መንግሥት ያስቀመጣቸው የሰላም አማራጮች" ተጠቃሚ እንዲኾኑ የክልሉ መንግሥት አሳስቧል። መግለጫው አያይዞም፣ የሕግ ማስከበር ርምጃው በክልሉ ሰላም፣ ፍትሃዊ ልማትና ተጠቃሚነትን" ለማረጋገጥ ያለመ መኾኑን አውስቷል።

3፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሸገር ከተማ ውስጥ የሚካሄደውን የመስጅዶች ማፍረስ ድርጊት እንዲያስቆም ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል። ምክር ቤቱ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር "የፈረሱ መስጅዶች በፍጥነት እንዲሰሩ" እንዲያደርግና የሙስሊሙን ኅብረተሰብ "በይፋ ይቅርታ መጠይቅ እንዳለበት" በደብዳቤው ላይ ማሳሰቡን ገልጧል። ምክር ቤቱ አስተዳደሩ አፈረሳቸው ያላቸውን አራት መስጅዶች በስም ዘርዝሯል።

4፤ ኢትዮጵያ በጀኔቫ በመካሄድ ላይ ላለው የተመድ ጸረ-ሥቅየት ኮሚቴ 76ኛ ጉባኤ ትናንትና ከትናንት ወዲያ ሪፖርቷን አቅርባለች። ኾኖም ኮሚቴው፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተለይም የጸረ-ሥቅየት ሪፖርት ላይ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር የተያያዙ በርካታ ትችቶችንና ጥያቄዎችን ማቅረቡን ኮሚቴው ካሰራጨው መረጃ ተመልክተናል። የጸረ-ሥቅየት ኮሚቴው አባላት፣ ኢትዮጵያ በምዕራብ ትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ "የብሄር ማጽዳት" ወንጀሎችን"፣ "ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎችን" እና "ሕገወጥ እስራቶችን" አስተባብላለች በማለት ከሰዋል። ኮሚቴው፣ ኢትዮጵያ በጦርነቱ ተፈጸሙ ለተባሉት ወንጀሎች "ተጠያቂነትን አላሰፈነችም"፤ "የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ ስለመሳተፋቸው መረጃ አልሰጠችም"፤ ዓለማቀፍ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪዎች ወደ ጦርነቱ ቀጠና እንዳይገቡ ከልክላለች" በማለት ወቅሷል። የኢትዮጵያን ሪፖርት ያቀርበው የፍትህ ሚንስትር ደኤታ አለማንተ አግደው የመሩት ልዑካን ቡድንም ለኮሚቴው ጥያቄዎችና ትችቶች ምላሽ ሰጥቷል።

5፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ጅዳ ውስጥ "ለሰብዓዊነት ዓላማ ተኩስ አቁም" ማድረግ በሚችልበት ኹኔታ ዙሪያ ዛሬ ፊት ለፊት ንግግር ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሁለቱም ወገኖች ተወካዮች ጅዳ መግባታቸውን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የፊት ለፊት ንግግሩን የሚያስተባብሩት ሳዑዲ ዓረቢያና አሜሪካ፣ ሁለቱ ወገኖች ወደተኩስ አቁም የሚያመራ ንግግር እንዲያደርጉና ግጭቱ በዘላቂነት እንዲቆም ከወዲኹ ባወጡት መግለጫ ተማጽነዋል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja