Get Mystery Box with random crypto!

የቅዳሜ ዕረፋድ! ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም የEMS አጫጭር ዜናዎች 1፤ በጎንደር ከተማ በፋኖ ታ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የቅዳሜ ዕረፋድ! ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም የEMS አጫጭር ዜናዎች

1፤ በጎንደር ከተማ በፋኖ ታጣቂዎችና መከላከያ ሠራዊት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ያለመ ውይይት እንደተጀመረ መስማቱን ጠቅሶ ቪኦኤ ዘግቧል። ውጥረቱን ለማርገብ፣ በአካባቢው ሽማግሌዎች አመቻችነት በኹለቱ ወገኖች መካከል ትናንት ውይይት እንደተደረገ ዘገባው ጠቅሷል። በውይይቱ ከተነሱ ነጥቦች መካከል፣ ሰሞኑን ወደ ጎንደር የገባው መከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው እንዲወጣና የፋኖ ታጣቂዎች አደረጃጀት እንዲቀጥል የሚሉት እንደሚገኙበት በውይይቱ የተሳተፉ የፋኖ አባላት መናገራቸው ተገልጧል። የክልሉ መንግሥትም ኾነ መከላከያ ሠራዊት ጎንደር ላይ ተደረገ ስለተባለው ውይይት፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያሉት ነገር የለም።

2፤ ሲዳማ ክልል ልዩ ኃይሉን ትናንት በይፋ ማፍረሱን ዶይቸቨለ ዘግቧል። የክልሉ ጸጥታ ቢሮ፣ የልዩ ኃይሉ አባላት ወደ ፌደራል እና ሌሎች የክልል ጸጥታ ተቋማት ተቀላቅለዋል ማለቱን ዘገባው አመልክቷል። የክልሉ መንግሥት በተንኳቸው ያላቸውን የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ብዛት ዘገባው አልጠቀሰም።

3፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከ8 ሺህ በላይ ከፊል ሥልጠና የወሰዱ ሥራ ተቀጣሪ ዜጎችን ወደ ውጭ አገራት መላኳን የሥራ ፈጠራና ክህሎት ሚንስትር ሙፈሪያት ከሚል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። መንግሥት የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዘርፉን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማዘመኑን ሚንስትሯ ገልጸዋል። ሰልጣኞቹ ተቀጣሪዎች ወደየትኞቹ አገሮች እንደተላኩ ግን ሙፈሪያት አልገለጡም። መንግሥት ለ500 ሺህ ተቀጣሪዎች ሥልጠና ሰጥቶ ወደውጭ አገራት በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለመላክ እየተንቀሳቀሰ ስለመኾኑ በቅርቡ ተዘግቦ ነበር።

4፤ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፊኤል በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ፍትህ እና ካሳ እንዲሰጣቸው ጥሪ ማድረጋቸውን የቫቲካን ዜና ምንጭ ዘግቧል። ካርዲናል ብርሃነየሱስ እውነተኛ ሰላም ለማምጣት በጦርነቱ ተጎጂዎች መካከል ይቅርታ እንዲሰፍን መጠየቃቸውን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ለተመላሽ ፍልሰተኞች፣ ለውስጥ ተፈናቃዮችና ኢትዮጵያ ውስጥ ለተጠለሉ ስደተኞች የክህሎት ሥልጠና ለመስጠት የተቋቋመው ዓለማቀፍ ፈንድ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴም ለዜና ምንጩ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፈንዱን ከኹለት ዓመት በፊት ያቋቋሙት፣ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት፣ የግል ኩባንያዎችና ዓለማቀፍ ድርጅቶች በጋራ በመኾን ነበር።

5፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት በአገሪቱ የሰባዓዊ ዕርዳታ መስመሮችን ማስክፈት በሚቻልበት ኹኔታ ዙሪያ ከፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ጋር ለመነጋገር ተወካዮቹን ወደ ጅዳ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚልክ አስታውቋል። በተያያዘ፣ የጦር ሠራዊቱ አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን፣ ልዩ መልዕክተኛቸውን በቀጣዩ ሰኞ ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚልኩ ለፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ቃል እንደገቡላቸው የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጧል።
ፕሬዝዳንት ኪር ለግጭቱ ሰላም ለማፈላለግ ኢጋድ ያቋቋመው የመሪዎች ቡድን ሰብሳቢ ናቸው። ተፋላሚ ወገኖች ከሐሙስ ጀምሮ ለሰባት ቀናት ቃል የገቡትን ተኩስ አቁም እስከ ትናንት ሌሊት ድረስ አላከበሩም። #ሼር በማድረግ ተባበሩን
ሰናይ ቅዴ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja