Get Mystery Box with random crypto!

የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታው ሁኔታ ውጥረት ውስጥ መግ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታው ሁኔታ ውጥረት ውስጥ መግባቱን የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዶቼ ቬለ የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት ጎንደር ከተማ ላይ መንገዶች ተዘጋግተው የሥራ እንቅስቃሴ የቆመ ሲሆን እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስም በአንዳንድ የከተማው አካባቢዎች የተኩስ ድምጽ ሲሰማ ነበር። በተኩሱ የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውን በማመልከትም በዛሬው ዕለት ደግሞ የተዘጉ መንገዶችን ለመክፈት እንቅስቃሴ መኖሩንም አመልክተዋል። እማኙ እንደሚሉትም ኅብረተሰቡ ለሀገር ሕልውና በመንግሥት ጥሪ ቀርቦላቸው ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው የነበሩ የአካባቢው ታጣቂዎች ላይ በመንግሥት ኃይሎች የሚወሰደውን የጥቃት እርምጃ አጥብቆ እየተቃወመ ነው። ለዚህ ተግባር በስፍራው እንደ ዙ 23 ያሉ የቡድን ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ሳይቀር ይዞ የተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ እየጠየቁ መሆኑንም ገልጸዋል። በጎንደር እና አካባቢውም ማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ መቆሙን ተመሳሳይ እርምጃም በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች በቀጣይ ሊኖር እንደሚችልም አክለው ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ይኽ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥና በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መኖሩን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል። የተኩስ ልውውጥና ጥቃት ተፈጽሟል ባላቸው «በሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ያለ መሆኑን፤ በተለይም ሸዋ ሮቢት፣ አርማኒያ፣ አንጾኪያ፣ ገምዛ እና ማጀቴ» ላይ «በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት የደረሰ መሆኑን እንዲሁም ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ጊዜያት የተዘጋ መሆኑን» ማረጋገጥ መቻሉንም ገልጿል። በተጨማሪም «በአማራ ክልል የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማዋቀር ውሳኔን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎችን መርተዋል/አስተባብረዋል የተባሉ የተወሰኑ ወጣቶች እና ከፋኖ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ የተወሰኑ ሰዎች እንደታሰሩ» መረዳቱንም አመልክቷል። ኢሰመኮ አክሎም «በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን አንድምታና ተጽእኖ» በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝም አመልክቷል። ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ም በበኩሉ ባወጣው መግለጫ «በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ሰላምና መረጋጋት እንደሌለና ዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዳልቻሉ መንግሥታዊ ሥራዎች ማከናወን አስቸጋሪ ሆኖ ኅብረተሰቡ ስጋት ውስጥ እንደወደቀ» መረጃዎች በአካባቢው ከሚገኘው ምንጮች እንደደረሱት አስታውቋል። «ውጥረቶች በሰላማዊ ውይይት እንጂ በጠመንጃ አፈሙዝ አይረግቡም» ያለው ኢዜማ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሰላማዊ መንገዶችን እንዲያስቀድሙ ጥሪውን አቅርቧል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ደግሞ በአማራ ክልል ለተፈጠሩ የፀጥታ ቀውሶች ምክንያቶቹ የፖቲካ ችግሮችና የመንግሥት ፍላጎት ማጣትና አቅም ማነስ ናቸው ሲል ተችቷል። አብን አክሎም በክልሉ የሚታዩት ችግሮች እልባት እንዲያገኙ መንግሥት ግንባር ቀደም ሚናውን እንዲወጣ በመጠየቅ፤ ፋኖና ሌሎች በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ከመካረር አልፈው ከመንግሥት የፀጥታ አመራሮች ጋር ንግግር እንዲጀምሩ አሳስቧል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ ም ጀምሮ «በኢ መደበኛ የታጠቁ» ያላቸውን ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ በሰላም አስከባሪና በሚሊሺያ ሠራዊት እንዲደራጁ፣ የማይፈልጉ ደግሞ ወደ ግል ሥራቸው እንዲገቡ ተከታታይ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን አስታውቋል። «በሕገወጥ መንገድ በቡድን ታጥቃችሁ ግድያና ዘረፋ የምትፈፅሙ ኃይሎች በሰላም እጃችሁን ለመንግሥት እንድትሰጡ ጥሪ እናቀርባለን» ሲል የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል። የክልሉ መንግሥት «ከሕግ የራቁና የታጠቁ» ያላቸውን ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየሠራ እንደሆነ በማመልከትም፣ «አጥፊዎች» ያላቸው ኃይላት ወደ ሥግ እስኪቀርቡ ድረስ ሕግ የማስከበሩ ሥራ የሚቀጥል መሆኑን አሳስቧል። #ሼር ማድረግ ግን ለምንድነው የምትረሱት? መረጃ አይናቅም ሼር ይደረግ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja