Get Mystery Box with random crypto!

ዓርብ ማለዳ! ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢዜማ በአማራ ክልል ባለው | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ዓርብ ማለዳ! ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ኢዜማ በአማራ ክልል ባለው ግጭት ተጨማሪ የሰው ሕይወትም ኾነ የንብረት ውድመት እንዳይከሰት መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት "ከግጭት በመለስ ያሉ ሰላማዊ መንገዶችን" እንዲያስቀድሙ ኢዜማ ጥሪ አድርጓል። ፓርቲው፣ በመንግሥት ውስጥና ከመንግሥት ውጭ ያሉ "ጽንፈኛ ዘውጌ ብሄርተኛ ኃይሎች ጽንፍ የወጣ ትርክትና እንቅስቃሴ" በክልሉ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረትና ግጭት አባብሶታል ብሏል። የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራል ጸጥታ መዋቅር የማዋሃድ ሂደት የተከናወነበት "ደካማ መንገድ" በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ስጋትና ጥርጣሬ መፍጠሩንም ፓርቲው ገልጧል።

2፤ ብሄራዊ ባንክ ከሚያዝያ 28 ጀምሮ ተግባራዊ የሚኾኑ የተለያዩ የወርቅ መግዣ ተመኖችን ማውጣቱን የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። በማሻሻያው መሠረት፣ ባንኩ እስካሁን ከዓለማቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ ለወርቅ አቅራቢዎች ሲሰጥ የቆየው የ35 በመቶ ተጨማሪ ክፍያ እንዲቀር ተደርጓል። በምትኩ ባንኩ ከዓለማቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ በየዕለቱ በሚወጣው ዓለማቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ፣ ከ50 እስከ 150 ግራም ወርቅ ላይ 35 በመቶ፣ ከ150.01 ግራም እስከ 1 ሺህ ግራም 52 በመቶ፣ ከ1,000.01 ግራም እስከ 5 ሺህ ግራም 55 በመቶ እና ከ5 ሺህ ግራም በላይ 60 በመቶ ተጨማሪ ክፍያ ለመክፈል መወሰኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።

3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጋር ትናንት በታላቁ ቤተመንግሥት መወያየታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። ሾልዝ በኢትዮጵያ በነበራቸው የግማሽ ቀን ቆይታ፣ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር ጭምር ተነጋግረዋል። ሾልዝ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው፣ ትናንት ማምሻውን ናይሮቢ ገብተዋል።

4፤ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ቀናት ተኩስ አቁም ለማድረግ የገቡትን ቃል ኪዳን ሳያከብሩት ቀርተዋል። በጦር ሠራዊቱና ፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት መካከል ውጊያው እስከ ትናንት እኩለ ሌሊት እንደቀጠለ የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀኔራል ቡርሃን ልዩ መልዕክተኛ ዳፋላህ አልሃጂ ጋር ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው መነጋገራቸውንና ኹለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች "ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ" ጥሪ ማስተላለፋቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪም፣ ልዩ መልዕክተኛውን በጽሕፈት ቤታቸው ማነጋገራቸውን በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል።

5፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ላይ ማዕቀብ ለመጣል የአሜሪካ ግምጃ ቤት "ጦርነት አጋጋዮችንና ሰላም አደፍራሾችን" እንዲለይ አዲስ ባወጡት ፕሬዝዳንታዊ መመሪያ አዘዋል። የባይደን ትዕዛዝ፣ ተፋላሚ ወገኖችን በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የረዱ ወይም ለመርዳት የሞከሩ የውጭ አካላት በአሜሪካ ያላቸው ገንዘብ እንዲታገድና ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር የንግድ ግንኙነት እንዳያደርጉ ያዛል። ባይደን፣ ማዕቀቡ በሱዳን ሰላምና ጸጥታ ላይ ስጋት የሚደቅኑና ሲቪል ሽግግር መንግሥት እንዳይመሠረት እንቅፋት የሚኾኑ ድርጊቶችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያስቀራል ብለዋል። ግጭቱ በአሜሪካ ብሄራዊ ደኅንነትና የውጭ ፖሊሲ ላይ "ያልተለመደና የተለየ ስጋት" ደቅኗል ተብሏል። #ሼር ማድረግ ግን ለምንድነው የምትረሱት? መረጃ አይናቅም ሼር ይደረግ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja