Get Mystery Box with random crypto!

በደብረ ኤልያስ በሚገኙ አራቱ ገዳማት ውስጥ አንድ መነኩሴ ብቻ መገኘታቸው ተገለጸ በአማራ ክልል | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

በደብረ ኤልያስ በሚገኙ አራቱ ገዳማት ውስጥ አንድ መነኩሴ ብቻ መገኘታቸው ተገለጸ

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሥር ባሉ አራት ገዳማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት፤ በገዳማቱ አንድ መነኩሴ ብቻ መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች፡፡

በገዳማቱ ከግንቦት 18 እስከ 23/2015 ለተከታታይ አምስት ቀናት “የታጠቁ ኃይሎች በገዳሙ ውስጥ ይገኛሉ” በሚል በተደረገ ኦፕሬሽን እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ መነኮሳት መሞታቸውን፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓበርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አሥተዳደር መምሪያ ኃላፊ መጋቤ ካህናት አባ ሀብተጊዎርጊስ አሥራት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ኃለፊው አክለውም፤ በአራቱም ገዳማት አቢያተ ክርስቲያናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ለአዲስ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በገዳሙ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “ሕግ ማስከበር” ያሉትን ዘመቻ ከማካሄዳቸው በፊት በርካታ መነኮሳት እና አገልጋዮች ይኖሩ እንደነበር ገልጸው፣ የገዳማት አስተዳደር መምሪያው ወደ ሥፍራው ባቀናበት ወቅት የተገኙት አንድ መነኩሴ ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

“መሞታቸው ከታወቀው መነኮሳቱና አገልጋዮች ውጭ ሌሎቹ የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡” ያሉት ኃላፊው፤ በገዳሙ ውስጥ ባለው ሰፊ የአትክልት እርሻ በርካታ ያልተቀበሩ አስከሬኖች መኖራቸውንና በአካባቢው ከፍተኛ የአስከሬን ሽታ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “በገዳሙ የታጠቁ ኃይሎች መሽገዋል” በሚል ኦፕሬሽን ቢያደርጉም፤ በተለያዩ ጊዜያት ሽፍታዎች የገዳሙን ንብረት ለመዝረፍ ወደ ሥፍራው ይመጡ ስለነበር፣ መነኮሳቱ ምሽግ ቆፍረው ንብረቱን ከዝርፊያ ለማዳን እና ሕይወታቸውንም ለመታደግ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተደረገው ዘመቻ ጉዳት የደረሰባቸው አቢያተ ክርስቲያናት የሥላሴ፣ ኪዳነምሕረት፣ የኤልያስ እና የጊዎርጊስ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ አቢያተ ክርስቲያናቱ የውጭ ክፍላቸው ጨምሮ ቅኔ ማሕሌቱ፣ ቅድስቱ እና ቤተመቅደሱ ላይ የደረሰው ድብደባ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።

“በተለይ በኪዳነምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው ጉዳት ከኹሉም የከፋ ነው፡፡” ያሉት ኃላፊው፣ ንዋተ ቅድሳትን ጨምሮ የቤተ መቅደስ መገልገያዎች መውደማቸውን እና ጉልላቱም ተመትቶ መውደቁን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ “በገዳማቱ ውስጥ ራሳቸውን “የኢትዮጵያ ዓለም ብርሃን” ብለው የሚጠሩ አካላት አሉ”” ተብሎ ስለሚነሳው ገዳይ ላነሳችላቸው ጥያቄም፤ “እነዚህ አካላት በትክክል በገዳሙ ውስጥ አሉ ለማለት ባያስደፍርም በአንዱ ቤተክርስቲያን ላይ የእነሱ አርማ ያለበት ሰንደቅ ዓላማ ታይቷል” ብለዋል።

አሁን ላይ በአራቱም አቢያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ የተጎዱትን አቢያተ ክርስቲያናት መልሶ ለመጠገን እና የጉዳት መጠኑን በሚገባ ለማወቅ በመንበረ ፓትርያርክ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና አገረ ስብከቱ የጋራ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ


t.me/emsmereja
t.me/emsmereja
t.me/emsmereja