Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ምሽት! ሰኔ 14/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሌሎች አ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ረቡዕ ምሽት! ሰኔ 14/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሌሎች አገራት አየር መንገዶች ያልከፈለውን 95 ሚሊዮን ዶላር የተከማቸ ዕዳ እንዲከፍል ዓለማቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር በአዲስ አበባ እያካሄደው ባለው ስብሰባ ላይ ማሳሰቡን ሪፖርተር ዘግቧል። በመንግሥት ላይ የተከማቸው ዕዳ፣ ሌሎች አየር መንገዶች አዲስ አበባ ውስጥ በትኬት ሽያጭና ሌሎች አገልግሎቶች ያገኙት ብሄራዊ ባንክ በዓለማቀፍ ሕግ መሠረት ወደ ዶላር ቀይሮ ያልሰጣቸው ገቢያቸው ነው። መንግሥት ዕዳውን ለአየር መንገዶቹ ካልከፈለ፣ የአገሪቱ ዓለማቀፍ የአየር በረራ ግንኙነቶች ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ማኅበሩ ማስጠንቀቁን ዘገባው ጠቅሷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፣ ኤርትራና ናይጀሪያን ጨምሮ የተወሰኑ አገራት ከትኬት ሽያጭና ሌሎች አገልግሎት ያገኘውን 180 ሚሊዮን ዶላር እንዳልለቀቁለት ገልጧል ተብሏል።

2፤ መንግሥት ለቀጣዩ በጀት ዓመት በራያና አካካቢው ለሚገኙ ሦስት ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር የመደበውን የፌደራል ድጎማ በጀት ለትግራይ ክልል እንዳይለቅ የሚጠይቅ የ145 ሺህ ሕዝብ ፊርማ ሰኞ'ለት ለፌደሬሽን ምክር ቤት መቅረቡን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ከአካባቢው ሕዝብ ፊርማውን አሰባስቦ ያቀረበው፣ የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በሦስቱ ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር የሚኖረው ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱና ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ ግን ሕዝቡ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ መኾኑ በአቤቱታው ላይ ተገልጧል ተብሏል። ፌደሬሽን ምክር ቤትም አቤተታውን እመረምራለኹ ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል።

3፤ ከፍትህ ሚንስቴር እና ፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ጅቡቲ የሚገቡባቸውን መተላለፊያዎች ተዘዋውሮ መመልከቱን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። ልዑካን ቡድኑ፣ የጎበኛቸው የሕገወጥ ፍልሰተኞች መተላለፊያዎች፣ "ኦቦክ" እና በቀይ ባሕር በኩል ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በጅልባ መውጫ የኾነው "ፋንታሂሮ" የተባለ ቦታ እንደኾኑ አምባሳደሩ ጠቅሰዋል። ልዑካን ቡድኑ፣ ከአካባቢው የጅቡቲ አስተዳዳሪዎችና ከዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት ሃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያዊያን ሕገወጥ ፍልሰት ዙሪያ መወያየቱም ተገልጧል።

4፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱቸው በኪሳራ የተነሳ ለበርካታ ዓመታት በረራ ያቋረጠውን የናይጀሪያ አየር መንገድ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት እንደገና ወደ በረራ ለመመለስ ብርቱ ጥረት እያደረገ መኾኑን ለኢዜአ ተናግረዋል። አየር መንገዱ ባለፈው ወር የናይጀሪያ አየር መንገድን በረራ ለማስጀመር፣ አንድ የራሱን ቦይንግ አውሮፕላን ወደ ናይጀሪያ ልኮ ነበር። ኾኖም የናይጀሪያ ሲቪል አቬሽን በአዲስ መልክ ለተዋቀረው አየር መንገድ የበረራ ፍቃድ ባለመስጠቱና የናይጀሪያ የግል አየር መንገዶች የመሠረቱበት ክስ ባለመቋጨቱ፣ በረራው ሳይጀመር መቅረቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደገና በተዋቀረው የናይጀሪያ አየር መንገድ ውስጥ 49 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲኾን፣ የናይጀሪያ መንግሥት 5 በመቶ እንዲኹም ናይጀሪያዊያን ባለሃብቶች ቀሪውን ድርሻ ይዘዋል።

5፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች አልሸባብ ዛሬ በኢትዮጵያና ሱማሊያ የጋራ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ላይ ባደረሰው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት 5 ወታደሮች እንተገደሉና በርካቶች እንደቆሰሉ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የቡድኑ አጥፍቶ ጠፊዎች በወታደራዊ ጦር ሠፈሩ ላይ ጥቃት የፈጸሙት፣ ከጦር ሠፈሩ 100 ሜትር ርቀት ላይ ፈንጂዎችን በማፈንዳት እንደነበር ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የፈንጂ ፍንዳታውን ተከትሎ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የቡድኑ ታጣቂዎች ተገድለዋል ተብሏል። አልሸባብ በድንበር አካባቢ ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ለማድረስ ሞክሮ ሳይሳካለት እንደቀረ ይታወሳል።

6፤ ዛሬ ጧት ዋሽንግተን የገቡት የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ ዛሬ ከአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ኦስቲን ሎይድ ጋር በኹለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ፔንታጎን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ከዚያም ወደ ኒውዮርክ በማቅናት፣ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በሱማሊያ ወቅታዊ ጸጥታ ላይ በሚያካሂደው ልዩ ስብሰባ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉና ጸጥታው ምክር ቤት በሱማሊያ ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ እንዲያነሳ እንድንጠይቁ ይጠበቃል። ጸጥታው ምክር ቤት፣ በሱማሊያ ላይ ልዩ ስብሰባ እንዲቀመጥና ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ንግግር እንዲያደርጉ የጋበዘቻቸው የጸጽታው ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ናት።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ5114 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ6016 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 66 ብር ከ4317 ሳንቲምና መሸጫው 67 ብር ከ7603 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ከ5592 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ7504 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ


t.me/emsmereja
t.me/emsmereja
t.me/emsmereja