Get Mystery Box with random crypto!

የቀድሞዋ አፈጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም መረጃ በማጥፋታቸው የራያ አላማጣ የማንነት ጥያቄ እንዲጓተት ምክ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የቀድሞዋ አፈጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም መረጃ በማጥፋታቸው የራያ አላማጣ የማንነት ጥያቄ እንዲጓተት ምክንያት ሆኗል ተባለ

የራያ አላማጣ ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄ እልባት እንዲሰጠው በሚል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የላከው ደብዳቤ በቀድሞ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም አማካኝነት እንዲጠፋ ተደርጓል ተብሏል።

የአላማጣ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሞገስ እያሱ፤ የራያ አላማጣ የማንነት እና የበጀት ጥያቄ ከ2011 ጀምሮ ለፌደሬሽን ምክርቤት ሲቀርብ እንደነበር ገልጸው፤ “የወቅቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኬሪያ ኢብራሂም የማንነት ጥያቄውን ለማዳፈን በማሰብ ለምክር ቤቱ የገባው መረጃ እንዲጠፋ አድርገዋል፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም ለምክር ቤቱ የገባው መረጃ እንዲጠፋ መደረጉ፤ የራያ አላማጣ ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄ መፍትሄ ሳያገኝ ለአራት ዓመታት እንዲጓተት ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት።

“አፈጉባኤዋ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ በገባው ደብዳቤ መሰረት የማንነት ጥያቄው መልስ እንዲያገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ስንጠይቅ፤ መረጃው መጥፋቱ ስለተነገረን ቅጂውን በድጋሜ ለማስገባት ተገደናል፡፡” ሲሉ ጠቁመዋል።

ባሳለፍነው ሰኞ ሰኔ 12/2015 የራያ አላማጣ እና ባላ አካባቢዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ከ150 ሺሕ በላይ የሕዝብ ፊርማ ተሰብስቦ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መግባቱን የጠቀሱት ኃላፊው፤ “ዋና ዓላማውም የማንነት ጥያቄያችን ተፈቶ ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን እንድንካተትና በጀቱ በትግራይ ክልል ሳይሆን በአማራ ክልል በኩል እንዲለቀቅልን ነው፡፡” ብለዋል።

አክለውም፤ በተለይ የፌደራል ተቋማት በአካባቢው የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ፣ ከባንክ፣ ከኤሌክትሪክና ከኢንተርኔት ጋር ያለው አገልግሎት በቶሎ ምላሽ ሊስጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለዚህም አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የራያ አላማጣ የማንነት እና የበጀት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ኮሚቴ ተቋቁሞ፤ ሰኞ ሰኔ 12/2015 ለፌድሬሽን ምክር ቤት መግባቱ ነው የተገለጸው።

ሕወሓት ለራያ እና አላማጣ አካባቢዎች አመራር መድቧል በሚል የሚነሳውን ጉዳይ በተመለከተም መድቧል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ አምስት አመራሮችን የቀያየረ መሆኑን ጠቁመው፤ “ወደ ራያ እና አላማጣ ግን ሊመጡ አይችሉም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።

ራያ አላማጣ ለኹለት ዓመታት ያለ በጀት መቆየቱን የገለጹት ኃላፊው፤ የማንነት ጥያቄው እና ለኹለት ዓመት የተቋረጠው በጀት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ህዝቡ በተደጋጋሚ በመጠየቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።

በተያያዘም፤ በዛሬው ዕለት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ''መንግሥት የማንነት ጥያቄቸውን ሕጋዊ እንዲያደርግላቸው'' በሰላማዊ ሰልፍ የጠየቁ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ በሰላማዊ ሰልፉ “አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም”፣ “የፌደራል መንግሥት ተቋማት ዲስትሪክት ወደ ሰሜን ወሎ ዞን ይዛወሩልን”ና ሌሎች የተለያዩ መፈክሮችን ማሰማታቸውን የሰሜን ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን አስታውቀል።
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ


t.me/emsmereja
t.me/emsmereja
t.me/emsmereja