Get Mystery Box with random crypto!

የቀድሞ አስረኛ ክፍል ተማሪዎች ከመጭው ዓመት ጀምሮ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን መከታ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የቀድሞ አስረኛ ክፍል ተማሪዎች ከመጭው ዓመት ጀምሮ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበት እድል መመቻቸቱ ተገለጸ

በቀድሞው ስርዓተ ትምህርት አስረኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች፤ በ2016 የትምህርት ዘመን በማንኛውም ትምህርት ቤት በመግባት የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመደበኛ ትምህርት መቀጠል እንደሚችሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስተር የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታ አማካሪ አዝመራ ከበደ፤ “በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የቀድሞው የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን መቀጠል ይችላሉ፡፡” ብለዋል።

የተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን አንተነህ ሙሉ በበኩላቸው፤ የቀድሞው አስረኛ ክፍል ተማሪዎች በዲፕሎማ የሚሰጡ ማንኛውንም አይነት ትምህርቶችን መከታተል ይችሉ እንደነበር ጠቁመው፤ ከዚህ በኋላ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የአስረኛ ክፍል የምስክር ወረቀት ያላቸውን ተማሪዎች እንደማይቀበሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከመጭው ዓመት ጀምሮ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን ብቻ፣ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሚያወጣው መቁረጫ ነጥብ መሰረት እንደሚቀበሉም ጠቁመዋል።

ተማሪዎቹ በመደበኛው 11 እና 12ኛ ክፍልን ከመማር በተጨማሪም፤ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መምሪያ መሰረት አጫጭር ስልጠናዎችን መውሰድ እንደሚቸሉም ገልጸዋል፡፡

በቀድሞው ስርዓተ ትምህርት አስረኛ ክፍል አጠናቀው የብሔራዊ ፈተና ማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች፤ ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በመግባት በዲፕሎማ የሚሰጡ ትምህርቶችን መከታተል ይችሉ እንደነበር ይታወሳል።ሼር አድርጉ

t.me/emsmereja