Get Mystery Box with random crypto!

በሰሜን ሸዋ በርካታ ቁጥር ያላቸው አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች በኦነግ ‹‹ሸኔ›› ታፈነው መወሰዳቸው | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

በሰሜን ሸዋ በርካታ ቁጥር ያላቸው አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች በኦነግ ‹‹ሸኔ›› ታፈነው መወሰዳቸው ተሰማ

ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገርበ ጉራቻ ከተማ፤ ቅዳሜ ዕለት ሰኔ 10/2015 ከጠዋቱ 12 ሰዓት አካባቢ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከባድ መኪና እና የሕዝብ ትራንሰፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በማገት በርካታ አሸከርካሪዎችንና ተሳፋሪዎች አፍነው መወሰዳቸውን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።

ለእገታ የተዳረጉት የኹሉም ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እና ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ጉዞ በማድረግ ላይ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

በዕለቱም ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን ከገርበ ጉራቻ ከተማ ወጣ ብሎ ልዩ ሥሙ ኡላ በተባለ ቦታ መንገድ በመዝጋት መኪኖቹን ካስቆመ በኋላ፤ ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ሰዎችን ወስዶ ከስፍራው መሰወሩን ነው ነዋሪዎች የተናገሩት፡፡  

ነዋሪዎቹ አክለውም፤ ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው በተደጋጋሚ መሰል ተግባራትን ማድረጉ የተለመደ ቢሆንም፣ የአሁኑ ለየት የሚያደርገው በቁጥር ብዙ የሆኑ ሰዎችን አፍኖ መውሰዱ እና ሌላ ጊዜ ሌሊት ላይ የሚያደርገውን ተግባር በቀን መፈጸሙ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ድርጊቱ በተፈጸመበት አካባቢ የአገር መከላከያ ሰራዊት ካምፕ በኩዩ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ “ከበላይ አካል ትዕዛዝ አልተቀበልንም” በማለት ሰዎቹን ሊታደጓቸው አለመቻላቸው ነው የተገለጸው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ከአንድ ሳምንት በፊት በፊቼ ከተማ መውጫ ላይ በተለምዶ ገንደ ጉዳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ በቅርብ ርቀት ላይ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ታፍነው መውሰዳቸው ተነግሯል።

የአካባቢው ማህበረሰብ በታጣቂ ቡድኑ በተደጋጋሚ በሚደርስበት ጥቃት የስነልቦና ድቀት እንዲሁም በሰው ሕይወትና በንብረት ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደ ነውም ብለዋል።

በታገቱ ሹፌሮች ቁጣ፣ በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል ከደብረ ማርቆስ ወደ ደንበጫ የሚወስደው መንገድ ከረፋድ ጀምሮ ዝግ መሆኑ አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

የታገቱ አሽከርካሪዎችን ለመልቀቅ አጋቾች ለአንድ ሰው ከ500 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እየጠየቁ መሆኑም ተነግሯል።

አዲስ ማለዳ ከአሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ


t.me/emsmereja
t.me/emsmereja
t.me/emsmereja