Get Mystery Box with random crypto!

ቅምሻ አዲስ ዘመን ከወቅትና ከመልክአ ምድራዊ፣ ከባህልና  ከሃይማኖት አንጻር አዲስ ዘመ | Yoni Arts

ቅምሻ

አዲስ ዘመን ከወቅትና ከመልክአ ምድራዊ፣ ከባህልና  ከሃይማኖት አንጻር

አዲስ ዘመን የሚከበርበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛ ወንዞች የሚጎሉበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት አርሶ ዘርቶ አርሞ ወዘተ… የአዝመራውን አላባ የሚጠብቅበት፣ የጥጋቡ ዘመን የሚመጣበት፣ ብርሃናት ዑደታቸውን ጨርሰው አዲስ የሚጀምሩበት  ወዘተ. ሲሆን ሁኔታውን ከወቅቶችና ከመልከአምድራዊ ሁኔታ ጋር አሰናስሎ መመልከት ይቻላል፡፡

መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣
እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ፡፡


የሚለው ግጥም ወቅትና መልከአ ምድርን የሚመለከት ነው፡፡ በክረምት ወንዝ እስከሚጎድል /ድልድይ እንኳን ያኔ አሁንም በየጎጡ አይታሰብም/ ዘመድና ዘመድ የማይገናኝበት መሆኑን ያመላክታል፡፡

ሁለተኛው በኖኅ ዘመን ምድርን ያጥለቀለቃት የጥፋት ውሃ የደረቀበት በመሆኑ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ መጽሐፈ ኩፋሌ ላይ በአስረኛው ወር፣ የተራሮች ራስ ታየ ይልና፤ ምድር በመጀመሪያው ወር መባቻ መታየቷን ይመሰክራል፡፡ /ኩፋሌ ምዕ 7፥1/ ከዚህ በተጨማሪ ሄሮድስ የቅዱስ ዮሐንስን ጭንቅላት ያስቆረጠበትን፤ በዚህም የቅዱሱን ሰማዕትነት ለመዘከር ነው የሚሉ ሀሳቦች ናቸው፡

በሌላ በኩል ከባህላዊ ዳራ አንጻር የምንመለከታቸው ሲሆኑ ጭፈራው፣ ምርቃቱ፣ ችቦ ማብራቱ፣ ድግሱ ወዘተ. ናቸው፡፡ ዝናቡ የምህረት፣ እህሉ የበረከት እንዲሆን፣ ሰላም እንዲወርድ ይጸለያል፡፡ “እህል ይታፈስ ገበሬ ይረስ፤ አራሽ ገበሬውን ሳቢ በሬውን ይባርክ...” እየተባለ በሽማግሌዎች ይመረቃል፡፡ ጭፈራዎቹም የባህሉ አንድ አካል ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የተወሰኑ ስንኞች ወስደን እንመልከት፡፡

የጎመን ምንቸት ውጣ፣
የገንፎ ምንቸት ግባ፡፡
አይዞሽ ነፍሴ ፣
ደረሰልሽ ገብሴ፡፡
አትኩራ ገብስ፣
ጎመን ባወጣው ነፍስ፡፡


ገበሬው የአመት ቀለቡ የሚሟጠጥበት፣ ለዘር ያስቀመጣትን እህሉን ለመሬት አደራ ሰጥቶ /የዘር እህል አይበላም/ ቶሎ የሚደርሱትን እነጎመንን እየተመገበ ይከርማል፡፡ መስከረም ጥቅምት ላይ በተለይ የገብስ ዘሮች ይደርሱና ገንፎም በሶም ይበላል፡፡ ስለዚህ በዘመን መለወጫ ጊዜ ጎመን ሲቀቅልበት የከረመውን ምንቸት ውጣ እያለ በአዲስ ተስፋ የገንፎ ምንቸቱን ግባ ሲልና፤ ወደዚህኛው ምግብ የሚዞርበትን ሁኔታ ሲገልጽ እንሰማለን፡፡ በሽታውን፣ ችግሩን፣ ተንከሊሱን ሁሉ በችቦ የተስፋ ብርሃን እንጎሮጎባሽ እያለ በመተርኮስ ያባርራል፡፡

እዚህ ላይ ለነፍሱ ገብስ እንደደረሰለት ያስገነዝብና ተመልሶ ገብስ በዚህ እንዳይኮራ፣ የጎመንም ውለታ እንዳይረሳ “ገብስ፤ ነፍሴን አትርፎ ለአዲስ ዘመን ያደረሰኝ ጎመን ነውና አትንቀባረር” ለማለት “አትኩራ ገብስ፣ ጎመን ባወጣው ነፍስ” ብሎ ሸንቆጥ ያደርገዋል፡፡

ችቦም ድቅድቁን ጨለማ የሚሰነጥቅ ብርሃን ስላለው፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሄዳችን ትዕምርት ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡

መልካም አዲስ አመት!

Welcom 2015

በየቀኑ የምንለቃቸው ጽሑፎች እንዲደርሷችሁ ለዚህ ቻናል አዲስ የሆናችሁ Join በማድረግ ተቀላቀሉን።

@yoniarts5
@yoniarts5
@yoniarts5