Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነት ብዙ የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተዋኅዱበት አካል ክፍል መሆን ነው። | Yoni Arts

ኢትዮጵያዊነት

ኢትዮጵያዊነት ብዙ የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተዋኅዱበት አካል ክፍል መሆን ነው። ኢትዮጵያዊነት ከጎሠኝነት በላይና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት የዚች ውጥንቅጥ መሬት ባለቤትነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት፣ የደጋው ዝናብም ከቆላው ወንዝ ጋር የተዛመደበት ኃይል ነው።

ኢትዮጵያዊነት በቄጤማ ጉዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብና መፈቃቀር ነው።

ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፣ የሚዛናዊነት የጨዋነት ባሕርይ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ረዢምና ተጽፎ ያላለቀ ታሪክ ነው፤ ብዙ ሰዎችም የተሰዉለት ስሜት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ስቃይና መከራ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ክብርም ነው።

ኢትዮጵያዊነት ጭቆናና ጥቃት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አሻፈረኝና እምቢ ባይነትም ነው።

የኢትዮጵያዊነት ዓላማ ያለችውንና የኖረችውን ኢትዮጵያን እንደገና ለመፍጠር አይደለም። የኢትዮጵያ ዓላማ ለኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚስማማ እድገታቸውንም የሚያፋጥንና፣ ኅብረታቸውን የሚያጠነክር ሥርዓትን መፍጠር ነው።

  የኢትዮጵያዊነት ችግር ኢትዮጵያ አይደለችም፣ ችግሩ የሥርዓት ችግር ነው። የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀኝ እንዳለው ቂል እንዳንሆን።

  ኢትዮጵያዊነትን መካድ የራስን ማንነት መካድ ብቻ አይደለም። አባቶችንና እናቶችን፣ ቅድም አያቶችን ከነቅርሳቸው መካድ ነው። በእንደዚህ ዓይነቱ ክህደት ላይ የተመሰረተ ማንነት የት ይደርሳል? ከበሽታ በቀርስ ትርፉ ምን ይሆናል? ክህደት ራሱን የቻለ በሽታ ሲሆን ማስካድ ደግሞ የባሰ ነው። ክዶ ማስካድ ታምሜያለሁኝ፣ ታመሙ እንደማለት ነው።

አስታማሚ እንኳን እንዳይገኝ የማድረጉ ጥረት የበሽታውን ምልዓትና ጽናት ያመለክታል።

ሆኖም የኢትዮጵያ ታሪክ ሊያስተምረን እንደሚችለው ኢትዮጵያዊነት እንደ ላስቲክ ነው። ሲስቡት ይሳባል፣ሲለቁት ይሰበሰባል። ማለት-ይሳብና ይሳሳል እንጂ አይበጠስም።

ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

በየቀኑ የምንለቃቸው ጽሑፎች እንዲደርሷችሁ ለዚህ ቻናል አዲስ የሆናችሁ Join በማድረግ ተቀላቀሉን።

@yoniarts5
@yoniarts5
@yoniarts5