2022-03-22 22:02:10
በወጣትነት ሁሉም ነገር ትክክል ነው ከሚል መመሪያ
ውጣ ፤ ሁሉንም ካላየሁ አላምንም አትበል ። ሰምቶ ማመን ፣
ከተጎዱት መማር አስተዋይነት መሆኑን አትርሳ ። የሰማንያ
ዓመት ዕውቀትን ለመገብየት ግድ ሰማንያ ዓመት መኖር
የለብህም ። ሰማንያ ዓመት ከኖሩት በትሕትና መጠየቅ
ይገባሃል ።
:
ምክርን ብትሰማ በነጻ ትማራለህ ። ምክርን አልሰማ
ብትል ግን በዋጋ እንደምትማር እወቀው ። በዋጋ መማር ግን
አድካሚ ደግሞም የሚያስመርር ነው ። ብልህ ከሆንህ በሰው
ከደረሰው ትማራለህ ፣ ሞኝ ከሆንህ ግን በራስህ ሲደርስ
ትማራለህ ።
:
የታየህን አሳይ ፣ ያልታየህን አጥራው ። በደንብ
ያልተረዳኸውን አታስተምረው። ያልቀመስከውን ለሰው
አትጋብዝ ። የሰማኸውን ሁሉ አትመን ። ያየኸውን ሁሉ ስጡኝ
፣ የተናገርከውን ሁሉ ፈፅሙ አትበል ። የሰጠኽውን እርሳ
እንጂ አታውራ። ፍፃሜውን ሳታይ ምስጋና አታብዛ ። ቀኑ
ሳይመሽ ቀኑ ጥሩ ነው አትበል ።
:
ዓይንህ የፊቱን ቢያይ ልብህ የኋላውን ያስብ ። ነገ ላይ
እንድትደርስ የትናንቱን አትርሳ ። የምትሄድበት እናዳይጠፋህ
የመጣህበትን አትዘንጋ ።
:
የአባቶችህን መልካም ሥራ አብነት አድርግ ። ካሳለፉት
ሕይወት ተማር እንጂ አወዳሽና ወቃሽ አትሁን ። ሌሎች
መሆን ያለባቸውን ስታውቅ አንተ መሆን ያለብህ
እንዳይጠፋህ ተጠንቀቅ ። ደግሞም አንተም በታሪክ ፊት
መሆንህን እወቀው ።
:
ክፋት አይሙቅህ ፣ መልካም ነገርም ብርድ ብርድ
አይበልህ ። ለክፋት አቅም ካለህ ለበጎ ነገርም አቅም አለህና
ተግባርህ የምርጫ ውጤት ነውና አስብበት ።
:
ገንዘብ የሚመልሰው የገንዘብን ጥያቄ ብቻ ነውና ሁሉንም
ነገር ገንዘብ ያስገኝልኛል ብለህ አታስብ ። ላለው አትሩጥ ፣
ምጽዋትህና ተግባርህ በአቅምህ መጠን ይሁን እንጂ
ከአቅምህ አትነስ ። ድሃም ሆነህ ተበድረህ ስጦታ አትስጥ ።
በጣም ካልቸገረህ ለቅንጦት አትበደር ። ያንተን ድርሻ
ከጨረስህ ያልተጨረሰ የሌሎችን ድርሻ ፈፅምላቸው ።
:
ለሀብታም አትሳቅ ፣ የደሀ ጉልበት አይለፍብህ ፣ ያለ ሰው
ሰው አልሆንክምና ሰው አትጥላ ፣ የወጣህበትን መሰላል
አትገፍትር ፣ ለመውረድም ያስፈልግሃልና ፣ ያየኽውን ሴት
ሁሉ የመውደድ ጠባይህ ካለቀቀህ ትዳር አትያዝ ፣
ካልጋበዙህ በቀር አማካሪ አትሁን ፣ ባልጠሩህ ሥፍራ አቤት
አትበል ፣ ካልሾሙህ መሪ አትሁን ፣ ጉድለት በሌለበት ቦታ
ጊዜህን አታባክን ፣ የሰው ፊት ጥገኛ ሁነህ ሲስቁልህ
የምትስቅ ሲቆጡህ የምታለቅስ አትሁን ፣ ነገርህን በልክ ፣
ቃልህን በጣዕም ፣ ድምፅህን በዝግታ ፈፅመው ።
:
እውር እንዳይሉህ ያልታየኽን አያለሁ አትበል ። ጨካኝ
እንዳይሉህ ያልተሰማህን ጩኸት እሰማለሁ አትበል ። ንፉግ
እንዳይሉህ ያለ አቅምህ እረዳለሁ አትበል ። ነገር
አይገባውም እንዳይሉህ ያልገባህን እንደገባህ አድርገህ
አትለፍ ። አንድ በጎ ዕውቀት ሳትጨብጥ የዋልክበትን ቀን
እንደ ኖርክበት አትቁጠረው ፣ ስለዚህ መፅሐፍትን አንብብ ፣
አዋቂዎችን ጠይቅ ፣ ሁሉን ሳትንቅ ስማ ።
:
ሥልጣን ሲሰጥህ መሪ እንጂ አለቃ አትሁን ፤ ከፊት
እየቀደምህ አስከትል እንጂ ከኋላ ሆነህ አትቅደም ።
:
በዓላማ ኑር ፤ እንቅፋቶች የሚያጸኑህ እንጂ ተግባርህን
የሚያስተውህ አይሁኑ ። ሕይወት ትምህርት ቤት መሆኑና
ባለማወቅ ብዙ ትህምርቶች እንዳያመልጡህ ተጠንቀቅ ።
:
የመከራ ቀን ወዳጆችህን አትርሳ ፤ የዛሬ ሰው ብቻ አትሁን
፤ የትላንቱንም አስብ ፤ አንገት የተፈጠረው ዞሮ ለማየት ነውና
።
:
ዓለም ዋዣቂ ናት ። ከፍና ዝቅ ስትል አትደናገጥ ፤ ፀሐይ
ዝናብን ተከትላ ትፈነጥቃለች ። ከመከፋትም በኋላ ትልቅ
መፅናናት ይሆናል ። ከሌሊት በኋላም ሌሊት አይመጣም ።
ከሀዘን በኋላ ደስታ ይሆናልና በርታ!
:
መነቀፍን አትፍራ ፤ ነቀፋህን ግን አጥራው ፤ ስለ ሀሰት
ሳይሆን ስለ እውነት ተገፋ ፤ ሌሎችን ውደድ ፍቅር ስጦታ
እንጂ ብድር አይደለምና አልወደዱኝም ብለህ በአበዳሪዎች
አንቀጽ አትካሰስ ፤ የገባህን አድርግ የዚህ ዓለም ሰው
ሲወድህም ሲጠላህም ባለማወቅ ነው ። ብዙዎች
ስለወደዱህ ይወድሃል ፤ ብዙዎች ስለጠሉህ ይጠላሃል ።
:
ሁልጊዜ የበላዮችህን አትመልከት ፤ የበታቾችህንም
ተመልከት ። ለድምፅ አልባዎች ጩህላቸው ፣ ለተጠቁት
ተሟገትላቸው ። እውነት እውነት በማለትህ የምታጣው
ሀሰተኛ ወዳጅህን ብቻ ነው ። እውነት እውነት በማለትህ
የምታተርፈው ግን እውነተኛ ወዳጅን ነው ።
:
ደጋፊዎች ተከታዮች አይደሉም ። ሰዎች ስለደገፉህም
የያዝኩት እውነት ነው ብለህ መንቻካ አትሁን ፤ ምናልባት ዛሬ
የሚጮሁልህ ዛሬን ሊረሱብህ ሊሆን ይችላልና ።
ሲያለቅሱልህም ቃልህ ማርኳቸው ሳይሆን የሞተ ዘመዳቸው
ትዝ ብሏቸው ሊሆን ይችላልና አለቀሱ ብለህ ንግግርህን
ድንበር አታሳጣው ። እውነትንም በደጋፊ ብዛት እንዳትመዝናት
ተጠንቀቅ ።
:
ለእውነታ እንጂ ለይሉኝታ አትኑር ፤ ያን ስልህ የምትኖርበት
ሕዝብና ባሕል ከእውነት ጋር እስካልተጋጨ መጋፋት
የለብህም። ሠዎች የሚቀበሉህ ባሕላቸውን ስታውቅና
ስታከብርላቸው ነው ።
:
ልጅነት የለሰለሰ መሬት ፣ ወጣትነት የአዝመራ ዘመን ፣
ሽምግልና ደግሞ የአጨዳ ዘመን መሆኑን አስተውል ።
በሽምግልናህ የምታጭደው የወጣትነትህን አዝመራ ነውና
ዛሬ ለምትዘራው ተጠንቀቅ ።
:
የሰዎችን ያለማወቅ አግዝ ፤ ዕውቀትህ ባላወቁት ላይ
እንድትኮራና እንድትፈርድ አያድርግህ የአዋቂ ኩሩ ቁጥሩ
ካላዋቂዎች ነውና ማወቅ ባለዕዳነት እንዳይሆን አላዋቂዎችን
እርዳቸው !!
፡
ሁሉን ወሬ ላውራ አትበል ፣ የደበቁህን ምስጢር
አታውጣጣ ፣ የሰማኽውን ወሬና የተገለጠልህን ምስጢር
ምን መፍትሔ ሰጠኸውና ? ያየህውን ሥራ ሁሉ እሰራለሁ
የሰማኸውን ትምህርት ሁሉ እማራለሁ አትበል ። ይህ
የተሰወረው የቅንዓት ጠባይ ነውና ሁሉን ልያዝ ማለትም ዝንጉ
አድረጎ እንዳያስቀርህ ሁሉም ውስጥ ልኑር አትበል ።
፡
ቆንጆዎች ቁንጅናቸው ሁሉን የሚተካ እየመሰላቸው
ከዕውቀትና ከትሕትና ይርቃሉ ። ሁሉንም ሰው በመልካቸው
የሚማርኩት ስለሚመስላቸው ኩሩና ተንኮለኞች ይሆናሉ ።
አንተ ግን ቆንጆ ወዳጅን እንጂ ቆንጆ ቁመናን አትሻ ፤ ቆንጆ
ትዳርን እንጂ ቆንጆ ሴትን አትመኝ ፤ የላይ ነገር ከንቱና ኀላፊ
ነውና በሚፈርስ አካል ፣ ኑሮ በሚለውጠው መልክ አትደለል።
፡
እወድሃለሁ ብለህ የምትናገረውን ቃል ውለታ አታድርገው
፣ መውደድህን የምትናገረው እንወድሃለን እንዲሉህ አይሁን ፣
ሠላም ያለው አፍቃሪ የራሱን ፍቅር ያለ ምክንያት መፈፀም
የሚችል ብቻ እንደሆነ እወቅ ። መወደድህን ለመስማት
አትጠብቅ ።
፡
የሰዎችን ያለማወቅ አግዝ ፤ ዕውቀትህ ባላወቁት ላይ
እንድትኮራና እንድትፈርድ አያድርግህ የአዋቂ ኩሩ ቁጥሩ
ካላዋቂዎች ነውና ማወቅ ባለዕዳነት እንዳይሆን አላዋቂዎችን
እርዳቸው ።
፡
ዛሬ የመዝራት ዘመንህ ነገ መከርህ ነውና በእምነት
እውነትን ዝራ ፤ በምታውቀው ቦታ ላይ አገልጋይ
በማታውቀው መልካም ተግባር ላይ ደጀን ሁን ፤ በቦታህ
መምህር ያለቦታህ ተማሪ ሁን ፤ ክብሩ እንዳይቀንስብህ ከዕቃ
ትምክህት ፣ ከዕውቀት ሙግት ራቅ ።
ይቀጥላል.....
1.3K viewsedited 19:02