Get Mystery Box with random crypto!

በአዲስ አበባ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የመታወቂያ መስጠት እና እድሳት አገልግሎት በቀጣዩ ሳምንት ዳ | YeneTube

በአዲስ አበባ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የመታወቂያ መስጠት እና እድሳት አገልግሎት በቀጣዩ ሳምንት ዳግም ይጀመራል ተባለ!

በአዲስ አበባ ከተማ ከአንድ ሳምንት በላይ ተቋርጦ የቆየውን የመታወቂያ መስጠት እና እድሳት አገልግሎትን በሚቀጥለው ሳምንት ለመጀመር የጥገና ስራ እያከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ገለጸ። ኤጀንሲ ይሰጣቸው የነበሩ መደበኛ አገልግሎቶች የተቋረጡት፤ ከመረጃ ማከማቻ ቋቱ ጋር በተገናኙ “የቴሌኮም ኬብሎች” ላይ ጉዳት በመድረሱ መሆኑን ገልጿል።

በአዲስ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፤ የመታወቂያ ስርጭት፣ የልደት እና የሞት ምዝገባ፣ ያላገባ የምስክር ወረቀት፣ የማስረጃ የማረጋገጥ ስራን እንዲሁም የጋብቻ እና የፍቺ ምዝገባን የሚከውን ተቋም ነው። ኤጀንሲው በመዲናዋ የሚገኙ 106 ወረዳዎችን “በዲጂታል” ስርዓት” በማስተሳሰር ይሰጣቸው የነበሩ አገልግሎቶች፤ ካለፈው አንድ ሳምንት ወዲህ በመቋረጣቸው በተገልጋዮች ላይ መጉላላትን አስከትሏል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት የሚገኝ የነዋሪነት ምዝገባ ጽህፈት ቤትን በትላንትናው ዕለት በአካል ተገኝቶ የተመለከተው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ ለወትሮ በሰው ብዛት ይጨናነቅ የነበረው አገልግሎት መስጪያ ባዶ መሆኑን ታዝቧል። አገልግሎት መቋረጡን ባለመስማት ወደ ጽህፈት ቤቱ የመጡ ሁለት ነዋሪዎችም እምብዛም ሳይቆዩ መመለሳቸውንም ተመልክቷል።

[Ethiopia Insider]
@YeneTube @FikerAssefa