Get Mystery Box with random crypto!

ከኢትዮጵያ ለመጡ ዜጎች የተሰጠው ጊዜያዊ የከለላ ፈቃድ ተራዘመ! ለተለያዩ ጉዳዮች መጥተው አሜሪካ | YeneTube

ከኢትዮጵያ ለመጡ ዜጎች የተሰጠው ጊዜያዊ የከለላ ፈቃድ ተራዘመ!

ለተለያዩ ጉዳዮች መጥተው አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ በሀገራቸው ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ካለፈው ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለ18 ወራት ተሰጥቶ የነበረው የከለላ ፈቃድ ወይም ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ እንዲቆዩ የሚፈቅደው ደንብ፣ ለሌላ 18 ወራት መራዘሙን የአሜሪካው የሀገር ውስጥ ደህነት ሚኒስትር አሌሃንድሮ ማዮርካስ ዛሬ አስታውቀዋል።

አዲስ የተራዘመው የከለላ ፈቃድ ከሐሙስ ሰኔ 6፣ 2016 እስከ ታኅሣሥ 3፣ 2018 ተግባራዊ እንደሚደረግ ከሃገር ውስጥ ደህነት ሚኒስቴሩ ዛሬ ዓርብ ሚያዚያ 4፣ 2016 የወጣው መግለጫ አመልክቷል።“በሃገሪቱ የሚካሄደው የትጥቅ ግጭት እንዲሁም ለየት ያሉ ጊዜያዊ አስቸጋሪ ሁኔታዎች፣ ግለሰቦች ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ስለማያስችሉ፣ የከለላው መራዘም አስፈላጊ ሆኗል” ሲል መግለጫው ጨምሮ ገልጿል።

“በኢትዮጵያ የትጥቅ ግጭቱ እና ሁከቱ በበርካታ ክልሎች ቀጥሏል፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ተበራክተዋል፣ ሲቪሎች ለጥቃት ተጋልጠዋል። ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ እና የበሽታ ወረርሽኝ የሚሊዮኖችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል” ሲል አክሏል። በመሆኑም የከለላው መራዘም አስፈላጊ እንደሆነ አመልክቷል። ሚኒስትሩ አሌሃንድሮ ማዮርካስ ከተለያዩ ሌሎች መ/ቤቶች ጋራ በመመካከር ከለላው ለ18 ወራት እንዲራዘም መወሰናቸው ተመልክቷል።

በከለላው ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ ኢትዮጵያን የሚመዘገቡበትን ድህረ ገጽም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ይፋ አድርጓል።ከከለላው መራዘም ጋራ ተያይዞ የወጣውና F–1 በሚል ቪዛ ወደ አሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን የሚመለከተው መግለጫ እንደሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸውና በአሜሪካ የሚገኙ ተማሪዎች፣ ከለላው በተራዘመበት የግዜ ገደብ ውስጥ፤ የሥራ ፈቃድ መጠየቅ እንዲችሉ፣ ተጨማሪ ሠዓታት እንዲሠሩ እንዲሁም የሚወስዱትን የትምህርት ኮርሶች መጠን መቀነስ እንዲችሉ ይፈቅዳል።

“ጊዜያዊ የከለላ ፈቃድ፤ በአሜሪካ የሚገኙ ግለሰቦች፣ በሃገራቸው ያለው ሁኔታ፣ ደህነታቸው በተጠበቀ መንገድ እንዲመለሱ በማያስችል ጊዜ ከለላ ይሰጣቸዋል” ሲሉ ሚኒስትሩ ማዮርካስ መናገራቸው በመግለጫው ተመልክቷል። ከትናንት ሚያዚያ 3፣ 2016 በፊት አሜሪካ የገቡ ኢትዮጵያን የገጠማቸው ሁኔታም ይኽው እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ “ለጊዜው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሰብአዊ እፎይታ የመሰለ ከለላ ሰጥተናቸዋል” ብለዋል።

ከተመዘገቡ እና ከለላው የሚጠይቀውን መሥፈርት ካሟሉ፣ ከዚህ ቀደም የወጣው ከለላ ተጠቃሚ የሆኑ 2ሺሕ 300 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እስከ ታኅሣሥ 3፣ 2018 ድረስ የከለላው ተጠቃሚነታቸው እንደሚራዘምላቸው ተመልክቷል።ኢትዮጵያን አስመልክቶ የተራዘመው የከለላ ደንብ፣ 12ሺህ 800 የሚሆኑና ከትናንት ሚያዚያ 3፣ 2016 በፊት አሜሪካ እንደገቡና በሃገሪቱ መቆየታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን፣ ወይም መኖሪያቸውን ኢትዮጵያ አድርገው የነበሩ ሌሎች ግለሰቦች፣ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ታውቋል።

ኢትዮጵያውያን፣ ወይም መኖሪያቸውን ኢትዮጵያ አድርገው የነበሩ ሌሎች ግለሰቦች፣ አሜሪካ የገቡት ከትናንት ሚያዚያ 3፣ 2016 በኋላ ከሆነ፣ ከለላው እንደማይመለከታቸው የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር መ/ቤቱ አስታውቋል።

እንደገና ከለላ ለማገኘት መመዝገብ የሚችሉትም፣ ከዚህ በፊት በመጀመሪያ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ወጥቶ በነበረው የከለላ ደንብ ተመዝግበው የነበሩት ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።በአሁኑ ወቅት የከለላው ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ከለላቸውንም ሆነ የሥራ ፈቃዳቸውን ይዘው ለመቆየት፣ ለምዝገባ በተፈቀደው 60 ቀናት ውስጥ፣ ማለትም ከሚያዚያ 7፣ 2016 እስከ ሰኔ 7፣ 2016 ድረስ እንዲመዘገቡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ አሳስቧል።

ከዚህ በፊት በወጣው ከለላ መሠረት ለከለላውም ሆነ ለሥራ ፈቃድ እስከ ሚያዚያ 7፣ 2016 ድረስ ያመለከቱ ወይም የሚያመለክቱ ግለሰቦች፣ ለሁለቱም ጉዳዮች እንደገና ማመልክት እንደማያስፈልጋቸው መ/ቤቱ አስታውቋል። የአሜሪካ የዜግነትና የፍልሰተኞች አገልግሎት (USCIS) ከዚህ በፊት የተቀበላቸውን ማመልከቻዎች እየተመለከተና ውሳኔ እየሰጠበት መሆኑም ተመልክቷል። ከዚህ በፊት በወጣው ከለላ መሠረት የገባን ማመልከቻ፣ የአሜሪካ የዜግነትና የፍልሰተኞች አገልግሎት (USCIS) የሚያጸድቀው ከሆነ፣ ከለላውም ሆነ የሥራ ፈቃዱ እስከ ታኅሣሥ 3፣ 2018 እንደሚሰጥ ታውቋል።በአዲሱ የከለላ ፈቃድ መሠረት ለከለላም ሆነ ለሥራ ፈቃድ ማመልከት የሚሹ፣ ከሚያዚያ 7፣2016 እስከ ታህሳስ 3፣ 2018 መመዝገብ እንደሚችሉ ታውቋል።

Via VoA
@YeneTube @FikerAssefa