Get Mystery Box with random crypto!

ታግተው የነበሩ አምስት የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች መገደላቸው ተነገረ! ለሁለት ሳምንት ያህል | YeneTube

ታግተው የነበሩ አምስት የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች መገደላቸው ተነገረ!

ለሁለት ሳምንት ያህል ታግተው የነበሩ አምስት የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ተገድለው መገኘታቸውን የፋብሪካውን አንድ ኃላፊ ለቢቢሲ ገለጹ።ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁት የስኳር ፋብሪካው ኃላፊ የአምስቱ ሠራተኞች አስከሬን ዛሬ ጠዋት መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. መገኘቱን ገልጸዋል።

አስከሬናቸው ከፋብሪካው ማሳ ወጣ ብሎ ጨካ በሚባል የገጠር አካባቢ ነው የተገኘው።ከተገደሉት መካከለ ሦስቱ ሠራተኞች ከወንጂ አካባቢ ሲሆኑ፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በዛሬው ዕለት መፈጸሙ ተገልጿል።ሌሎቹ ሁለቱ ሠራተኞች አንደኛው ከአዳማ የመጣው ሲሆን ቀብሩ ዛሬ የሚፈጽም ሲሆን፣ እንዲሁም ሌላኛው ከደሴ የመጣው ግለሰብ አስከሬን ወደ ስፍራው ተልኳል ተብሏል።

አራቱ ሠራተኞች በፋብሪካው ውስጥ በትራክተር ኦፕሬተርነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ እና ዕድሜያቸው ከፍ ያለ እንደሆኑም እኚሁ የፋብሪካው ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።ሌላኛው የኤሌክትሪክ ሠራተኛ (ፎርማን) ወጣት ሲሆን በቅርብ የተቀጠረ እና ለአንድ ዓመት ያህል በፋብሪካው አገልግሏል።

አንደ ኃላፊው ከሆነ ግለሰቦቹ ከሁለት ሳምንታት በፊት የአዳር ስር ላይ ምሽቱን አሳልፈው ጥዋት ላይ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን ዶዶታ ከሚባለው ፋብሪካው ከሚገኝበት ስፍራ በታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል።ኃላፊው፣ ሠራተኞቹን ያገቷቸው ሰዎች ገንዘብ ጠይቀው እንደነበር? ወይም የጠየቋቸው ጉዳዮች እንዳሉ ዝርዝሩን እንደማያውቁ አስረድተዋል።

ነገር ግን ፋብሪካው ከአጋቾቹ በኩል ምንም እንዳልተጠየቀ ገልጸው፣ ወዲያውኑ ለመንግሥት አካል ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።ፓሊስም ሠራተኞቹን ለማስለቀቅ እየተከታታለ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፤ ነገር ግን አስከሬናቸው ዛሬ ጥዋት 2 ሰዓት አካባቢ ተገኝቷል ብለዋል።ስለ ግድያው እንዴት? እና ስንት ሰዓት? ተፈጸመ የሚለውን ባያውቁም ምናልባትም ትናንት ምሽት ተገድለዋል ብለው እንደሚጠረጥሩ የተናገሩት ኃላፊው ሰራተኞቹ መገደላቸውን ሰምተው ወደ አካበቢው ሲሄዱ አስከሬናቸውን አግኝተናል ብለዋል።

በፋብሪካው እገታ ሲያጋጥም የመጀመሪያ መሆኑን እና እስካሁን ባለው ሁኔታ ሰላማዊ እንደነበርም ኃላፊው አስረድተዋል።በእገታው ዙሪያ ቢቢሲ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ለማናገር እየሞከረ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ስናገኝ እናካትታለን።በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ አቅራቢያ ከአዲስ አበባ 110 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ በ1946 ዓ.ም. ኤች.ቪ.ኤ በተባለ የኔዘርላንድስ ተቋም እና በኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ ባለቤትነት የተቋቋሙ በአገሪቱ ቀዳሚ የስኳር ፋብሪካ ነው።

ወታደራዊው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለቤትነት ስር መግባቱ ይታወሳል።ወንጂ ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 496/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉት አምስት ስኳር ፋብሪካዎች መካከከል አንደኛው ነው።

@YeneTube @FikerAssefa