Get Mystery Box with random crypto!

የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ በፍርድ ቤት | YeneTube

የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ በፍርድ ቤት ተወሰነ

“ሁከት እና በጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት 13 ቀናት በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ 100 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት ተወሰነላቸው። ለፖለቲከኛው ዋስትናውን የፈቀደው፤ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ነው።

አቶ በቴ ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ለተሰኘው የዜና ድረ ገጽ ዘጋቢ ከሆነው  አንቷን ጋሊንዶ ጋር ሐሙስ የካቲት 14፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በውይይት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው። ዛሬን ጨምሮ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት የኦነጉ ፖለቲከኛ፤ በፖሊስ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅባቸው ቆይቷል።

ዛሬ ረፋዱን በተካሄደው ችሎትም፤ ፖሊስ “ምርመራዬን አልጨረስኩም” በሚል ተጨማሪ 11 የምርመራ ቀናትን ጠይቋል። የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በነበረው ችሎት ለፖሊስ ተጨማሪ አምስት የምርመራ ቀናት የፈቀደው፤ ፖሊስ የሚያቀርበውን “የስልክ ምርመራ ውጤትን ለመስማት” ነበር።

በዛሬው ችሎት የተገኙት መርማሪ ፖሊስ፤ የአቶ በቴን የስልክ የምርመራ ውጤት ለመቀበል ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በተደጋጋሚ ጥያቄ ምማቅረባቸውን ሆኖም እስካሁን ውጤቱን አለመቀበላቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሰው ማስረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልጓቸው አስረድተዋል።

Via Ethiopia Insider