Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ የአየር ክልል በኩል መብረር አቆመ! የኢትዮጵያ አየር መንገድ | YeneTube

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ የአየር ክልል በኩል መብረር አቆመ!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስያ አገራት ለሚያደርጋቸው በረራዎች ይጠቀምበት በነበረው የሶማሊያ የአየር ክልል በኩል መብረር ማቆሙን አስታወቀ።አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች “አስተማማኝ የአየር ትራፊክ አገልግሎት” ባለማግኘቱ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስያ ለሚደርጋቸው በረራዎች “ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ” ይጠቀምበት በነበረው የሶማሊያ አየር ክልል መብረር ያቆመው፤ የአየር መንገዱ አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 16/2016 ዓ.ም. በአገሪቱ የአየር ክልል ውስጥ ካጋጠመው ክስተት ጋር በተያያዘ መሆኑን አቶ መስፍን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን፤ “በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም ለሚመለከታቸው የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣናት ሪፖርት እናደርጋለን። [የቅዳሜውን ክስተት በተመለከተም] ለሶማሊያ እና ለኢትዮጵያ የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣናት ሪፖርት ተደርጓል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይሁንና እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን አክለዋል።የቅዳሜ ዕለቱ ክስተት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት “አስተማማኝ ሆኖ እንዳያገኘው” ማድረጉን አቶ መስፍን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ይህ ክስተት ካጋጠመበት ማግስት እሁድ የካቲት 17/2016 ዓ.ም. አንስቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሶማሊያን አየር ክልል መጠቀም ለማቆም መወሰኑን አስታውቀዋል።አቶ መስፍን፤ ከክስተቱ በኋላ ካለው ቀን አንስቶ “አማራጭ ለመጠቀም ወስነናል። ለዚህም ዋናው ምክንያት [የቅዳሜ ዕለቱ ክስተት] ነው። እዚያ በነበረው ሁኔታ፤ የአየር ክልሉ አስተማማኝ የአየር ትራፊክ አገልግሎት ስላላገኘንበት ለደኅንነት ስንል አማራጭ መንገዶች እየተጠቀምን ነው” ሲሉ የአየር መንገዱን ውሳኔ አብራርተዋል።

አየር መንገዱ ወደ እስያ ለሚያደርጋቸው በረራዎች የሚጠቀመው የሶማሊያን የአየር ክልል እንደነበር ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በአሁኑ ሰዓት እነዚህ በራረዎች የሚደረጉት በጂቡቲ አየር ክልል በኩል መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጂቡቲን የአየር ክልል እየተጠቀመ ያለው “ተጨማሪ ወጪ በማያመጣ መልኩ” እንደሆነም አክለዋል።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሌለሎች አገራት ለሚደረጉ በራረዎች የሶማሊያን አየር ክልል መጠቀም ቢያቆምም ወደ ሞቃዲሾ እና ወደ የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ከተማዎች የሚያደርጋቸውን በራረዎች “ያለ ችግር” መቀጠሉን አብራርተዋል።

Via BBC
@YeneTube @FikerAssefa