Get Mystery Box with random crypto!

'አንተ ከምታውቀውና ከምታምነው በላይ ሌላ ማንነት አለህና እሱን ፈልገህ አግኝ' ሀይለጊዮርጊስ(ጵላ | የኛ ሳይኮሎጂ||🇪🇹

"አንተ ከምታውቀውና ከምታምነው በላይ ሌላ ማንነት አለህና እሱን ፈልገህ አግኝ"
ሀይለጊዮርጊስ
(ጵላጦስ)

በርካታ አሳባውያን የሚስማሙበት አንድ የሰው ልጅ የማንነቱ እውነት ቢኖር የፈፀመውን ማንኛውንም ድርጊት አምኖበትና ፈቅዶ መሆኑን ከመቀበል ይልቅ እንደስህተትና ኃጢአት በመቁጠር በንስሀና ይቅርታ ራሱን ቀፍድዶ በሌሎች ፊት የመቆሙ ጉዳይ ነው:: ይኸ ብቻም አይደለም:: የሰው ልጅ መከራ ምንጩም ሆነ ምክንያቱ ይኸው ስህተት ወይም ኃጢአት በማለት የሚፀፀትበትን ድርጊት በኃላፊነት ከመሽከም ይልቅ ወደሌላው ትከሻ ማሽጋገሩ ነው:: ነገር ግን የአንተን (የሰው ልጅ) ኃጢአትም ሆነ መከራ አልያም ጭንቀት የሚሽከም (የሚወስድ) ሌላ ማንም እንደሌለ ደግሞ ብትረዳ ጭንቀትህን ለማስወገድ የመጀመሪያውን እርምጃ እንደወሰድህ ይቆጠራል::

ከአንተ ከራስህ በቀር አንተን ተክቶ ፃድቅ ወይም ቅዱስ የሚያደርግህ ሊኖር አይችልምና:: ነገር ግን በድርጊትህ ምክንያት ከሚፈጠርብህ የኃጢአተኛነት ጭንቀት ወይም የቅድስና እርካታ ይልቅ ኃላፊነቱን ራስህ ብትወስድና ሕይወትን እንደነበረች በማስቀጠል (ወደኋላ ዞረህ ሳትመለከታት) በጉዞህ ብትቀጥል ያን ጊዜ በእውቀት መንቃት ለመጀመርህ ማረጋገጫ ይሆናል:: ኃጢአትም ሆነ ቅድስና ብለህ የምትጠራውን ነገር አንተ ለብቻህ እንደፈፀምከው ካመንክ ስለምን ምህረትም ሆነ በረከትን ፍለጋ ወደሌላ ትመለከታለህ?

እዚህ ላይ የሰው ልጅ የዘወትር ሃሣቡ፣ ጭንቀቱና ፍርሃቱ በሕይወት ውስጥ በአንዳች አጋጣሚ አምኖበት ከፈፀመው ድርጊቱ የሚመነጭ ለመሆኑ የሚካድ አይደለም:: በመሆኑም ዛሬ የሚያጋጥምህን መከራ ትናንት ተሳስቼ ፈፀምኩት ከምትለው ድርጊት (በአንተ ቋንቋ 'ኃጢያት') የተነሣ እንደመጣብህ እያሰብክና ይኸው ምክንያትህ በሚያተርፍልህም ጭንቀት ሕይወትን አስቀያሚ አድርገህ በመመልከት ልትቀጥል አይገባም:: ኃላፊነትና ነጻነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው! የሰው ልጅ ለማናቸውም ድርጊቱ ሌሎች ኃላፊነቱን ወስደው የሚቆሙለትና የሚሸከሙለት እንዳሉ በማመኑ ዘወትር የሚከተላቸውን "አዳኞቹን" (saviors) በፀፀት፣ በልመናና በንስሀ ከፊታቸው መቅረቡን ተለማምዶታል።

ከዚህም የተነሳ ፈጣሪውን ሳይሆን ፈጣሪውን ወክለው በምድር ላይ የተገለጡትን ሁሉ በመከተል የእነሱን ፈቃድና ትዕዛዝ ፈፃሚ ሆኖ በመቅረቡ አንድ ቀን በራሱ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የፈፀመው ድርጊት "ኃጢአት" ቢኖር እንኳን ከእነሱ ምህረትና ይቅርታ ለማግኘቱ እርግጠኛ እስከሚሆን ድረስ ህይወቱን በጭንቀት መግፋቱ አይቀሬ ይሆናል:: በመሆኑም "የሰው ልጅ ይኸንና ያንን አታድርግ፤ እኔን ተከተል፤ እኔን እመን... እኔም አድንሃለሁ፤ እኔ ጠባቂህ ነኝ ወዘተ በሚለው የተስፋ ትዕዛዝና ቃላቸው የታመነባቸውን እየተከተለ የራሱን ማንነት ግን ለመጣል ይገደዳል ::

ይልቁንም ለፍቶና ደክሞ ያገኘውን ሀብት እየተመለከተ በነፃነት ከመደሰት ይልቅ ዘወትር ሀብቱን ሰጠኝ ብሎ የሚያምንበትን "አምላኩን" በፍርሀትና በጭንቀት ማመስገንን ይመርጣል:: እርግጥ ነው መከራ ከሌላ አምላክ የሚመጣ ቁጣ አድርጎ ሊቀበል የቻለ ሰው እንዲሁ የበረከት ምንጩን ሌላውን ቢያደርግ፤ በደስታውም ምትክ ጭንቀትና መከራን ቢያተርፍ የሚደንቅ አይሆንም:: ነገር ግን እዚህ ላይ የሚነሣው ጥያቄ "በመከራህም ሆነ በደስታህ የራስህን ኃላፊነት ወስደህ በነፃነት መቆም ካልቻልክ በሕይወት ውስጥ ድርሻ ምንድነው?" የሚለው ይሆናል::

ከንባብ ዳርቻ ለህይወት ጠአም!
#share and join for more
@KenibabDaricha
@KenibabDaricha