Get Mystery Box with random crypto!

+ የሰጠኸኝ ሴት + እግዚአብሔር አዳምን 'አትብላ ካልሁህ ዛፍ በላህን?' ብሎ ጠየቀው:: አዳምም | አፈምዑዝ🗣

+ የሰጠኸኝ ሴት +

እግዚአብሔር አዳምን "አትብላ ካልሁህ ዛፍ በላህን?" ብሎ ጠየቀው:: አዳምም :- ከእኔ ጋር እንድትሆን የሠጠኸኝ ሴት ከዛፉ ሠጠችኝና በላሁ አለ::

የሰጠኸኝ ሴት! በጣም ይገርማል:: ሚስቴ አላለም::
አዳምና ሔዋን የተገናኙ ቀን አዳም ያለውን አስታውሱ
"ይህች አጥንት ከአጥንቴ
ይህች ሥጋ ከሥጋዬ" ብሎአት ነበር::
ምንም እንክዋን አዳም ወላጆች ባይኖሩትም ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ብሎም ነበር::
ራቁታቸውን ቢሆኑም አይተፋፈሩም ነበር::

አሁን በራቁቱ ብቻ ሳይሆን በሔዋንም አፈረባት::
እናትና አባቱን ይተዋል እንዳላለ ሔዋንን ራስዋን ተዋት::
ከሚስቱ ጋር መተባበር ቀርቶ ክስ ጀመረ::

አካሌ አጥንቴ ሥጋዬ ማለቱ ቀረና የሠጠኸኝ ሴት አለ::
የጫጉላው ጊዜ አለፈና ከሚስትነትዋ ሴትነትዋ ብቻ ታየው::

በጋብቻ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሠጠንን ነገር
ሁሉ ቀድመን የራሳችን እናደርጋለን ነገሮች ሲበላሹ ግን ባለቤትነቱን ወደ እርሱ እንመልሰዋለን::

የሠጠኸኝ ሥራ
የሠጠኸኝ ወላጆች
የሠጠኸኝ ሰፈር
የሠጠኸኝ ሀገር
የሠጠኸኝ መሪ
የሠጠኸኝ ጉዋደኞች
የሠጠኸኝ ደካማ ሥጋ
የሠጠኸኝ ዓይን

ትናንት ሲሠጠን ዘምረን የተቀበልነውን ሥጦታ ዛሬ ለምሬት እንጠቅሰዋለን:: የሠጠኸኝ የሠጠኸኝ .... ሠጠኝና በላሁ ብለን ቀርጥፈን ለበላነው ዕፀ በለስ ፈጣሪን እንከስሰዋለን::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ግንቦት 17 2012
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ