Get Mystery Box with random crypto!

ሀመቺሣ/Hammachiisaa- እንደ ጥምቀተ ክርስትና ============================ | አፈምዑዝ🗣

ሀመቺሣ/Hammachiisaa- እንደ ጥምቀተ ክርስትና
==================================
‹‹ሀመቺሣ›› በአፋን ኦሮሞ ‹‹ማሳቀፍ›› ማለት ነው፡፡ ይህ ባህል የተወለዱ ሕጻናት በ‹‹መንፈሳውያን የሃይማኖት አባቶች›› (አባ ሙዳ፣ ሉባ፣ ቃሉ፣ ወዘተ) ታቅፈው የሚባረኩበት ሥርዓት ነው፡፡ በዕለቱም አዲስ ስም ይሰጣቸዋልና፥ አመቺሳ፡- ‹‹የሕጻናት/ልጆች ስም ማውጫ ቀን›› በመባልም ይታወቃል፡፡[1] ብዙውን ጊዜ በተወለዱ በመንፈቅ ዕድሜ እንደሚከናወን ቢገመትም ትክክለኛ ቀኑን ለመወሰን አስቀድመው ሙሉ ቀን መቁጠር ወደሚችሉት አዋቂዎች ዘንድ በመሄድ ጨረቃ የምትታይበትን ቀን አስበው ‹‹ጨጊኖ›› (ጎደሎ/መጥፎ ቀን እንደማለት ነው) በማይውልበት ዕለት ስለሚወሰን አመቺሣው ሊዘገይ ይችላል፡፡[2] በእርግጥ፥ የማኅበረሰቡ አዛውንት የወንድና የሴት ሕጻን አመቺሣ በቀናት እንደሚለያዩ (የወንዱ እንደሚቀድም) ቢናገሩም ትክክለኛውን ግን ለመግለጽ ይቸገራሉ፡፡
የሀመቺሣ ዋና ዓላማ የተወለዱ ሕጻናት በሃይማኖት አባቶች አማካይነት ከፈጣሪያቸው ፀጋና ረድኤት እንዲያገኙበት ሲኾን የሕፃኑ እናት የታቀፈችውን ልጇን ስታስታቅፍ፥ ‹‹ከዚህ በኋላ ለአንተ ሰጠሁህ›› በሚል ለፈጣሪ አደራ ማስረከቧ ነው፡- ልጁ ካልታቀፈ አያድግም (ይቀሰፋል)፣ ቢያድግም አይፋፋም፣ እንከን አያጣውም ተብሎ ይታመናልና፡፡ ምንም እንኳ እናቲቱ በወለደች በአምስተኛ ቀኗ (ሸነኒ በሚባል ሥርዓት) በተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎች ገላዋን ታጥባ ‹‹የነጻች›› ብትኾንም የአራስነቷን ጊዜ ጨርሳ ወደ ሥርዓተ አምልኮው የምትሔደው ግን በዚህ ዕለት ነው፤ እርሷም አስፈላጊውን ‹‹መባ›› (አሞሌ ጨው፣ አረቂ፣ ዳቦ፣ በኑግ የታሸ ቆሎ፣ ማር፣ ወዘተ) ለልጁና ለራሷ ይዛ ሄዳ ''garaa jiidhaa ta'i, ilma lammiif ta'u da'i'' (‹‹ማኅፀነ ርጥብ /ወላድ/ ኹኚ፤ ለወገን የሚተርፍ ወንድ ልጅ ውለጂ››) ተብላ ትመረቃለች፡፡
ሥርዓቱ፡- በትክክለኛው ቀን የሕጻኑ ቤተሰቦች ወደ ሥፍራው ይወስዱትና በእርጥብ ሣር ተጎዝጉዞ፣ በገል እሳት አማካይነት በሚሸቱ እጽዋት ጢስ በታወደው ማምለኪያ ቤት ይገኛሉ፡፡ እናት ልጇን ታቅፋ ከፊት፣ አባት ከኋላ፣ ሌሎችም እንደየማዕርጋቸው ኾነው ከታቃፊው ፊት ይቀርቡና ሁለት አሞሌ ጨው አበርክተው ልጁን ይሰጡታል፡፡ የሃይማኖት አባትም ልጁን ታቅፎ ወደ ‹‹ዋቃ ቶኪቻ›› እንዲህ ሲል ይጸልያል፡-[3]
‹‹ኹሉን የፈጠርክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከአባት ጀርባ ደም አንስተህ፣ በእናት ማኅፀን ቋጥረህ፣ እስትንፋስ ያለው አድርገህ፣ መውለድና ምጥ ረድተህ ገላግለህ በዓይናችን ስላሳየኸን ከፍ ባለ እምነት እናመሰግንሃለን፡፡ እንደዚሁም፥ ይኽንን ልጅ በአንተ ስጦታ በእነዚህ በሁለቱ መካከል የተገኘውን ወገኑን የሚረዳና የሚያስተዳድር፣ እናት አባቱን የሚጦር፣ የሽማግሌዎችን ምክር የሚሰማ፣ የጎሣውን ባህል የሚጠብቅ፣ አንተን ፈርቶ አንተን አምኖ ባንተ የሚያድር እንድታደርግልን ከልብ እንለምንሃለን፡፡ ረጅም ዕድሜ ስጠው፣ እናትና አባቱ እርሱ ከተወለደ ደላን ብለው እንዲያመሰግኑህ[4] መልካም ገድ አድርግላቸው፤ የእነዚህን አማኞች ሕዝቦችህን ልመና እህ ብለህ ስማ፣ የምህረት መልስም መልስላቸው!››
ከዚህ በኋላ ለልጁ ስም ያወጣለታል (እናትና አባቱ ካወጡለት ሌላ)፡፡ እንትፍ ብሎ እንዲያድግ መርቆት መልሶ ይሰጣቸዋል፡፡
በመሠረቱ ይህ ሥርዓት በዘሌዋ.12፥1-8 ላይ ከተቀመጠውና ዛሬም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጠው የ፵ እና ፹ ልጅነት ጥምቀት (ክርስትና ማስነሣት) ጋር የሚመሳሰል ኾኖ እናገኘዋለን፡፡[5] በኦሪቱ ሴቷ የግዳጅዋ ጊዜ ሲፈጸም ከእነ ሕጻኗ ወደ ቤተመቅደስ ገብታ ከሕርስ የምትነጻበት ሥርዓት ሲኾን ቀናቱም አዳምና ሔዋን ተፈጥረው በልጅነት ክብር ወደ ገነት የገቡባቸውን ጊዜያት እንደሚጠቁሙ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ አሁንም በዚሁ መሠረት ታቅፈው የሚመጡትን ሕጻናት መርቃ፣ የሥላሴን ልጅነት ሰጥታ (አጥምቃ)፣ ሥጋ ወደሙን ታቀብላለች፤ የክርስትና አባትና እናትም ኃላፊነታቸውን ይውጡ ዘንድ ታስረክባለች፡፡ ደግሞም፥ ለሕጻናቱ አዲስ ስም መሰጠቱም ሀመቺሣንና ክርስትና ማንሣትን ያመሳስላቸዋል፡፡
እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር ቢኖር ሀመቺሣ የግድ ከክርስትና በፊት መፈጸሙ ነው፡፡ አንድ ሕጻን አስቀድሞ ክርስትና ከተነሣ በምንም ተአምር አይታቀፍም፤ ይህን ያደረገ ቤተሰብም ‹‹እስከ መወገዝ›› ይደርሳል፡፡ ይኽ ምናልባትም፥ ‹‹የሁለቱን መናፍስት ተቃራኒነት›› በግልጽ ቢያሳይም አዛውንቱ ግን ቁርጥ ያለ መልስ አይሰጡም፤ በቃ ''qooda isaati'' (ሥርዓቱ ነው) በሚል ይቋጫሉ፡፡ 
~~~~~~~