Get Mystery Box with random crypto!

ሜዴቻ-እንደ ክርስትና ‹‹ማዕተብ››? ================================== ሜደቻ | አፈምዑዝ🗣

ሜዴቻ-እንደ ክርስትና ‹‹ማዕተብ››?
==================================
ሜደቻ (Meedhacha) ማለት ከኮርማ በሬ ቆዳ ላይ በቀጭኑ ቀድዶ በማውጣት በሞጋሣ ሥርዓት ደንብ መሠረት ኦሮሞነት ለተሰጣቸው ወገኖች በእጅ አንጓቸው ላይ የሚታሰር ምልክት ነው፡፡ የገዳ አባላትም በገዳ ሥርዓት ወቅት ሜደቻ በእጃቸው አንጓ ላይ ያስራሉ፡፡[1] ይኽ ማለት፥ ሜደቻ የሚታሠረው ኦሮሞነትን ተቀብለው ወደ ገዳው ሥርዓት ለተቀላቀሉ አዳዲስ ሰዎች ነው፤ የገዳ አባልነት ምልክት ተደርጎም ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ደግሞም፥ ከሞጋሣ ሥርዓት (አዲስ የኦሮሞ ስም መስጠት) ቀጥሎ መደረጉንም ልብ ይሏል፡፡
በኦሪት ውስጥ፥ መንታ ልጆችን ፀንሳ የነበረችው ትዕማር ቀድሞ እጁን ባወጣው ልጇ እጅ ላይ ቀይ ፈትል ለምልክትነት ታስሮለት እንደነበር እናነባለን (ዘፍ.38፥28-30)፡፡ ጋለሞታዪቱ ረዓብ ኢያሪኮን እንዲሰልሉ ለተላኩት የኢያሱ መልእክተኞች መልካም አቀባበል በማድረጓ (ሰውራ ከጠላት ስላዳነቻቸው) ከሌላው ሕዝብ ተለይታ ሊመጣ ከሚችለው ጥቃት ራሷንና ቤተሰቦቿን መታደግ የቻለችው በተሰጣት የቀይ ፈትል ምልክት ነበር፤ በዚያ ምልክት ከሚድኑት ወገኖች ጋር አንድነቷ ታውጇልና (ኢያ.2፥18)፡፡
በሐዲስ ኪዳን የክርስትናው ትውፊት መሠረት ደግሞ፥ ከሊቀ ጳጳሱ በያዕቆብ ዘእልበረዲ ዘመነ ስብከት (5ኛው ምዕተ ዓመት) ጀምሮ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ለኾነ ኹሉ ማዕተብ ማሰር ክርስቲያናዊ ትውፊት ኾኗል፤ እርሱ ንስጥሮሳውያን ከጉባኤው እየገቡ ስላስቸገሩት ኦርቶዶክሳውያንን ከመናፍቃን ለመለየት ከእግዚአብሔር ባገኘው ምልክት ጥቁር ቀይ ቢጫ ክሮች አንድ ላይ ፈትሎ በአንገታቸው ላይ ያስርላቸው በመጀመሩ፡፡[2] ዛሬም ድረስ ማዕተብ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን አባላት ከሌሎች ለይተን ለማወቅ የምንጠቀምበት ዋነኛ ምልክት ሲኾን በሥላሴ አምነው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ለተቀበሉት [ሕፃናትን ጨምሮ] ተጠማቂያን ኹሉ በዚያው ቅጽበት የሚታሠር ነው፡፡ እናም፥ ‹‹የአባልነት ምልክት›› በመኾን የገዳው ሥርዓት ሜደቻ ከክርስትናው ማዕተብ ጋር አይመሳሰል ይኾን?!
~~~~~~~