Get Mystery Box with random crypto!

‹‹መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን የመጨረሻው ምሽግ እና የኢትዮጵያ የከፍታ ማማ ነው›› - ክቡር አቶ | 🗣 ወቅታዊ_መረጃ 🇪🇹

‹‹መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን የመጨረሻው ምሽግ እና የኢትዮጵያ የከፍታ ማማ ነው›› - ክቡር አቶ ግርማ የሺጥላ

በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ ግርማ የሺጥላ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መልእክት አስተላልፈዋል።

ኃላፊው በመልእክታቸው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ጫናዎችን ተቋቁማ ለመቀጠል፣ የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ እና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ለመዝለቅ በምታደርገው ትግል ውስጥ መከላከያ ሠራዊት ግንባር ቀደሙ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዚህ ልክ ሚናውን ሲወጣ የቆየ ሲሆን ከምንም በላይ ህይወቱን እየሰዋ ሀገርና ህዝብን ጠብቆ ያቆመ፣ አሁንም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ብሎም በኢትዮጵያውያን ደህንነት ላይ ከውስጥም ከውጭም የሚቃጡ ማናቸውንም ጥቃቶች በብቃት እየመከተና እያከሸፈ ያለ ታላቅ ተቋም ነው፤ "መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን የመጨረሻው ምሽግ ነው" የሚባለውም ለዚህ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ክቡር አቶ ግርማ አክለዉም ሠራዊታችን በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ለህዝብ እና ለሀገር ደህንነት ሲል ከውጭ ጠላቶቻችን እና ከውስጥ ባንዳዎች የሚቃጣብንን ጥቃት በመመከት እና ከባድ መስዋትነት በመክፈል ሀገርና ህዝብ እየታደገ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ሣምንታትም አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ለ3ኛ ጊዜ አማራን ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለመበተን ጦርነት ከፍቶ ወረራ እየፈፀመ የሚገኝ ሲሆን በመከላከያ ሠራዊቱ የሚመራው ጥምር ጦር አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተብንን ጦርነት እና ወረራ እየመከተና እየተከላከለ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሠራዊታችን በአስተማማኝ የመከላከል አቅም ላይ ይገኝ እንጂ በሠራዊቱ አስተማማኝ ጥንካሬ ዕኩይ ዓላማቸው ያልተሳካላቸው የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች በሠራዊታችን ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ከፍተው ይገኛሉ፤ የጠላቶቻችን እና የባንዳዎች ዋና ዓላማቸው ደግሞ የህዝብ እና የሀገር መከታ የሆነውን ተቋም ከህዝብ ጋር ተቃርኖ መፍጠር ሲሆን ይህን ተከትሎም በህዝብ የማይደገፍ ደካማ ሠራዊት እንዲኖር በማድረግ ሀገርራችንን የመበተን ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት በማለም የጠነሰሱት ድኩማን ሀሳብ ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የጠላቶቻችን ፅኑ ፍላጎት ደካማ ሠራዊት ተፈጥሮ ማዬት ይሁን እንጂ በተለይም ከህዝባዊ ንቅናቄ ለውጡ በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሠራ ሪፎርም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የውስጥ እና የውጭ ባንዳዎች በየትኛውም የጦርነት እና የትግል ዓውድ የማያሸንፉት ይልቁንም ተሸንፈው እና አፍረው የሚመለሱበት ተቋም ሆኖ ተገንብቷል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሪፎርም ከተካሄደባቸው እና እጅግ ውጤታማ ተቋማት ውስጥም አንዱና ቀዳሚው የመከላከያ ተቋም ነው ያሉት አቶ ግርማ ሠራዊቱ ቀደም ሲል በብቃት ሲወጣ ከነበረው ግዳጅ እና ተልዕኮ በበለጠ አቅም የፈጠረ ሲሆን ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ከነበረው የዕዝ ቁጥር አድጎ፣ ትልቅ መዋቅራዊ አደረጃጀት ፈጥሮ፣ እጅግ ዘመናዊ እና የቴክኖሎጂ የጦር መሣሪያ ውጤቶች ታጥቆ እንዲሁም የባህር ኃይል ጭምር ገንብቶ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህ በስልጠናና በትጥቅ የተገነባ ሠራዊት "ከራስ በላይ ለሀገር እና ለህዝብ" በሚል መርህ አሁን ላይ ከባድ መስዋትነት እየከፈለ ሀገራዊ ፈተናዎችን እየተወጣ ይገኛል። በመከላከያ ሠራዊታችን የሚመራው ጥምር ጦርም ከሰሞኑ አሸባሪው እና ወራሪው የከፈተብንን ጦርነትም በአስተማማኝ የህዝብ ደጀንነት ታጅቦ በብቃት እየተከላከለእንደሚገኝ የጠቆሙት ክቡር አቶ ግርማ ሠራዊታችን ከራሱ አልፎም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ስር የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተቀብሎ ሰላም በማስከበር ላይ የማገኝ ሲሆን ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ስራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በማቅረብ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይህም መከላከያ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ የከፍታ ማማ መሆኑን ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ክቡር አቶ ግርማ የሺጥላ በመልእክታቸዉ ለመላዉ ህዝባችን ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን መላው ኢትዮጵያዊያን የመከላከያ ሠራዊታችን የሀገር ህልውና ጠባቂው ምሽግ መሆኑን በውል ተገንዝቦ ተቋሙ በሰው ኃይል እና በግብዓት ከዚህ የበለጠ እንዲገነባ መስራት ይጠበቅብናል። ስለሆነም ተቋሙ ተጨማሪ የሰው ሃይል መልምሎ ለማሰልጠን ማስታወቂያ ያወጣ በመሆኑ መስፈርቱን የምታሟሉ ወጣቶች የተቋሙ አባል እንድትሆኑ ለማሳሰብ እወዳለሁ ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ሀገር እና ህዝብ የሚጠብቅ ሠራዊት ጠባቂ ህዝብ ያስፈልገዋል እና ህዝባችን እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ የሠራዊቱ ደጀን ሆኖ በቂ ስንቅ በማቅረብ ሊደግፈው እና ከጀርባው ሆኖ ጠላትን ሊፋለም ይገባል። ለዕኩይ ዓላማቸው እንዲመች በማሰብ በሀሰት ወሬ ጭምር ስሙን ከሚያጠለሹት ጠላቶቻችን ሊጠብቀው ይገባል የሚል መልዕክትም አለኝም ብለዋል።

"ኢትዮጵያ በሠራዊታችን ብርቱ ክንድ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!"

"ለሃገር ክብር በትግል እናብር"

ሼር በማድረግ ትክክለኛዉን መረጃ ለሌሎች ተደራሽ ያድርጉ። ለበለጠ መረጃ ቴሌግራም
https://t.me/Merja01