Get Mystery Box with random crypto!

'የሙሉቀን መለሰ ትዝታዎች' (በዕውቀቱ ሥዩም) ከብላቴናነቴ ጀምሮ ሙሉቀን መለሰን ስወደው ኑርያለ | ወግ ብቻ

"የሙሉቀን መለሰ ትዝታዎች"
(በዕውቀቱ ሥዩም)

ከብላቴናነቴ ጀምሮ ሙሉቀን መለሰን ስወደው ኑርያለሁ። አስቴር አወቀ፣ ኤፍሬም፣ ሙሉቀን እና አበበ ተካ በዜማ ባያጣፍጡት ኖሮ የጉብዝና ወራቴ ምንኛ እጅ እጅ ይል ነበር...!
"ስለምትመኘው ነገር ተጠንቀቅ አንድ ቀን ልታገኘው ትችላለህና" ይላል ጠቢብ...!
ታድያ አንድ ቀን ራሴን ሙሉቀን መለሰ ቤት አገኘሁት። በርግጥ ያገኘሁት በልጅነቴ የማልመውን ሙሉቀንን አልነበረም፤ ሙሉቀን የወጣትነት ሥራውን ሲኮንን ነበር የደረስኩበት። "የዘፈን ምንጭ ሰይጣን ነው" ይላል፡፡(ነገሩ እንዲህ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስትር ሰይጣን ላገራችን ኪነጥበብ ያደረገውን አስተዋጽኦ አስታውሶ ቢሸልመው ደስ ይለኛል...ሰይጣን አይሸለምም ያለው ማነው?)
ሙሌ የተራኪነት ተሰጥኦ አለው፡፡ ስለአማርኛ ዘፈን ታሪክ ሲነሣ ጠንከር ያለ ትንታኔ ያቀርባል፣ ለጊዜውም ቢሆን ዘፈን የሰይጣን መሆኑን ይረሳና በግሉ ስላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይተርካል።
በርግጥ የታዋቂ ዘፋኞችን ችሎታ ያጣጥላል። አንዱን ስሙን የማልጠቀሰውን ዘፋኝ ሣነሳበት...
“እሱ እንዲያውም መዝፈን አይደለም ዘፈን እንዲያዳምጥ እንኳ ሊፈቀድለት አይገባም” አለኝ በተለይ ጥላሁን ገሠሠን ተችቶ አያባራም...
”እሱ እኮ የጉልበት ዘፋኝ ነው” ይለዋል።
ነገሩን ማስ ማስ ሳደርገው ከጥላሁን ገሠሠ ጋር ያለው
ግኑኝነት የፉክክር ብጤ ይመስላል። አልፈርድበት
“ሁለት አንበሶች ባንድ ዋሻ ውስጥ አይኖሩም ” ይላል ጎርኪ። በቅርቡ ሙሌ፤ “ናፍቆት ኢትዮጵያ” ከተባለ መጽሄት ጋር ዘለግ ያለ ቃለ-መጠይቅ አድርጓል።
ከምልልሱ ውስጥ ይቺን በፈገግታ ቀንጭቤ ልሰናበት...
ናፍቆት:- ለመሆኑ እስከ ስንተኛ ክፍል ተምረሃል?
ሙሉቀን፡- ረሳሁት እስከ ሦስተኛ ክፍል የተማርኩ ይመስለኛል።
ናፍቆት፡- ድምፃዊው ጥላሁን ገሠሠ በሁለት ክፍል ይበልጥሃላ!
ሙሉቀን፡- እሱ እዚያ ደርሷል እንዴ?
ናፍቆት:– አዎ፣ የምናውቀው እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ መማሩን ነው ….
ሙሉቀን፡- እንዲያውም አሁን ትዝ አለኝ አምስተኛ ክፍል ድረስ ነው የተማርኩት...

(ቀንጭቤው ነው እንጂ ረጅም ነበር)

@wegoch
@wegoch
@paappii