Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሁለት) (ሜሪ ፈለቀ) የ | ወግ ብቻ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሁለት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የሳመውን እጄን ተቀብዬው ከሆስፒታሉ ወጥቼኮ ታክሲ ተሳፍሬ ወደቃሊቲ መንገድ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ። እጄን ተቀብዬው አልኩኝ እንጂ እየተሰማኝ ያለው ወይ ከንፈሩ እጄ ላይ የቀረ ወይ ደግሞ እጄ እዛው እሱጋ ከንፈሩ ላይ የቀረ አይነት ስሜት ነው። የሳመኝን እጄን የሳመኝን ቦታ አንዳች የእግዜር ተአምር የፈለቀበት ነገር ይመስል እየደጋገምኩ አየዋለሁ። ደግሞ እየደጋገምኩ እሱ እንደሳመው እስመዋለሁ። ቀስ ብሎ ልስልስ ያለ …… እርጥበት ያለው ግን የሚሞቅ …….. ከዛ ደግሞ ከእግሬ ጥፍር ድረስ እስከ አናቴ እንደኤሌክትሪክ ሞገድ ጥዝዝዝ ብሎ በደምስሬ ውስጥ ይሆን የተጓዘው ፣ ከጅማቶቼ  ጎን ለጎን ባገኘው ክፍት ቦታ ይሆን እየተሽሎከለከ የተጓዘው ባልገባኝ አካሄድ የናጠኝ …… የሆነ መለኮታዊ የሆነ መሳም ነገር …..

ስሳም የመጀመሪያዬ ሆኖ አይደለም። በትግል ፣ ኑሮን ለማሸነፍ በመጋጋጥ ፣ ኪዳንን ትልቅ ቦታ እንዲደርስ በመታተር ፣ በበቀል ፣ ሴራ በመጎንጎን ፣ ገንዘብ እና ጉልበትን በማካበት …… እና ሌሎች ብዙ ለሌላው ሰው ስሜት የማይሰጡ ነገሮችን በማድረግ ውስጥ ከወንድ ጋር የሚደራረጉ አልባሌ ነገሮችን ከማድረግ አልታቀብኩም። እንደእውነቱ ከሆነ ብዙ አድርጌያለሁ። አብሮ በመግባት እና በመውጣት እንደፍቅረኛ ወግ ያሳለፍኩት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ከዳዊት ጋር ነበር። ዳዊት በከተማችን ውስጥ አለ የሚባል ባለሃብት ልጅ ነው። አባቱ በገንዘቡ ባለስልጣናትን የሚሾፍር ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው። የእድሜ ልክ እስራት ፍርዴን በ6 ዓመት ያቀለለልኝ እሱ ነው። ውለታ ውሎልኝ አይደለም! በልዋጩ ሶስት ነገር ሰጥቼዋለሁ። አንድ የነበረኝን 48% የሚሸፍን የአንድ ባንክ አክስዮን (እሱ 20% ስለነበረው የእኔን ሲጨምር በባንኩ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ያደርገዋል።) ሁለት የራቁት ዳንስ ቤቱን ግማሽ ልሸጥለት (ዳዊት የገባው በዛ ነው) ሶስተኛው እና ዋነኛው (ሌሎቹ ተጨማሪ ናቸው) የአንድ እሱ የሚፈልገው ከፍተኛ ባለስልጣን ሚስጥር (ለምን እንደፈለገው አልገባኝም ምክንያቱም እስካሁን አልተጠቀመበትም። ወይም እያስፈራራበት እየተጠቀመበት ይሆናል አላውቅም! ሰውየው ግን እስካሁን ስልጣኑ ላይ ነው።)

አንዲት ከትንሽ መንደር መጥታ ኑሮን ለመግፋት ትፍጨረጨር የነበረች ሴት የባለስልጣናት ሚስጥር እጇ ላይ እንዴት ወደቀ? ይሄ ሁሉ ሀብትስ እንዴት ተቆለለ? የሚሆን አይመስልም አይደል? ሆኗል!!

እዚህ ሀገር አንድ የገባኝን ነገር ልንገራችሁ! በተለይ  እላይኛው የኑሮ መደብ እና ስልጣን ላይ የተፈናጠጡት ሰዎቻችን ዘንድ ….. በገንዘብ አቅም የማይሆን ምንም ነገር የለም። የሚለያየው የገንዘቡ መጠን ብቻ ነው። በመቶ ሺህዎች <ሀቀኝነቴን ፣ እምነቴን ፣ ህሊናዬን > ሲል የነበረ ለሚሊየኖች እጅ ይሰጣል። ለሚሊየኖች <ቤተሰቤን ፣ አምላኬን ፣ ቃሌን ፣ ህዝቤን > ያለው ደግሞ ለቢሊየን ወድቆ ይሰግዳል። ገንዘቡን የምታቀርብለት ሰው ወይም ድርጅት የሌለውን ያህል ወይም በቀላሉ ሊያገኝ የማይችለውን ያህል ገንዘብ መጠን አቅርብለት! የምትፈልገውን ይሸጥልሃል። ለምን ሚስቱ አትሆንም!!! በስህተት አምልጦ የሾለከ <በገንዘብ የማልሸጠው ህሊና አለኝ> ያለ ጎርባጭ ከተገኘ …… በነዛኛዎቹ ይሰለቀጣል። <ህዝብን በተገቢ ሁኔታ ባለማገልገል፣ የህዝብን ጥቅም ባለማስቀደም > ምናምን ምናምን የሚባሉ ፖለቲካዊ ሀቅ የሚመስሉ ውስልትናዎች ተለጥፈውበት እንደ እድሉ አርፎ የማይቀመጥ ቅብጥብጥ ከሆነ ወደ እስር ቤት ……. ለቤተሰቤ አንገቴን ልድፋ ያለ የቤተሰብ ሰው ከሆነ ደግሞ ወደቤት ይላካል።

እንግዲህ ከዳዊት ጋር አብረን መስራት የጀመርነው ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ መሆኑ ነው። ወድጄው አይደለም! ማለቴ እንደፍቅረኛ! እንደስራ ባልደረባ ጭንቅላቱ ለቢዝነስ የተፈጠረ፣ ለተንኮል እና ሴራ እኔን የተስተካከለ ፈጥኖ አሳቢ ፣ አባቱ ስለሚንቀው ለአባቱ የሆነ ጀብድ ሰርቶ ራሱን ማስመስከር አብዝቶ የሚሻ ሰው ነው። ከምለብሳቸው የወሮበላ ልብሶች ውስጥ ያለ የሴት ገላዬን ራቁቱን ሳያየው የተመኘ ብቸኛ ወንድ ይመስለኛል። ባለገንዘብ ፣ ባለጉልበት ፣ ባለሀይል ከሆንኩ በኋላ ለአመታት በዙሪያዬ ያለ ሰው ሁሉ እንደአለቃ የሚፈራኝ ፣ እንደሰው የሚያከብረኝ ፣ በዛ ካለ ትንሽ የሚቀርቡኝ እንደወዳጅ የሚያዩኝ ሴት ነበርኩ እንጂ ማንም በሴትነቴ የተመኘኝ አላስታውስም። ሴት መሆኔ ትዝ የሚላቸውም አይመስለኝም። እሱ ግን እንደስራ ባልደረባው ሳይሆን እንደሴት አየኝ!! የሚጋረፍ ፊቴ ሳያግደው ለወራት አበባ አመላለሰልኝ (እያየ ፊቱ ላይ አበባውን በጫጭቄ እበትነዋለሁ) ። <ደነዝ ነህ ወይ አትሰማም? አንተ ምኔም መሆን አትችልም!> እያልኩት በየቀኑ ቆንጆ መሆኔን ነገረኝ። በግልፅ <አይደለም ፍቅረኛዬ ልትሆን ለአንድ ቀን ተሳስቼ አብሬህ ብተኛ የምፀፀትብህ አይነት ሰው ነህ!> እያልኩት እንኳን በየቀኑ ሳይደክመው እንደሚወደኝ እየነገረኝ ዓመት ተቆጠረ። አንድ ቀን ከአባቱ ጋር ተጣልቶ ቢሮ ተቀምጦ እንደ ትንሽዬ ሴት ልጅ ሲንሰቀሰቅ ደረስኩ። ምን እንደሆነ ስጠይቀው እንባውን ከንፍጡ እየደባለቀ ማልቀሱን ሳያቆም በአባቱ ፊት ሁል ጊዜ ትንሽ መሆኑን ነገረኝ። አሳዘነኝኮ ግን ከማልወደው ነገሩ አንዱ ይሄ ልፍስፍስ ሴታ ሴት ነገሩ ነው። የዛን ቀን ግን

«ዛሬ እራት ልጋብዝህ?» አልኩት። እንባው ጥሎት ጠፋ! ከዛ በኋላ እንደፍቅረኞች የሚፈፃፀመውን ነገር ሁሉ እንፈፃፅማለን። አልጋ ላይ ሲያዩት ስልባቦት እንደሚመስለው ገላው አይደለም ወይም እንደሴታሴት አኳኋኑ። ስለዚህ ሴታዊ ፍላጎቴን ለማግኘት የማላውቀው ሰው ጋር ከምሄድ ጥሩ ቅብብሎሽ ነበር። አንዳንዴ ምንችክ ሲልብኝ እዘጋዋለሁ። ደግሞ መልሰን እንጀምራለን። ስለእውነቱ ግንኙነታችን ምን እንደሆነ ወይም ወዴት እንደሚሄድ እንኳን ውልም ስምም የለውም ነበር። እንኳን እጄን ስሞኝ የስሜቴ የመጨረሻ ጡዘት ጠርዝ ላይ እንኳን እንዲህ ዛሬ ጎንጥ እጄን ሲስመኝ እንደተሰማኝ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም!! ኸረ እንኳን ሊሰማኝ መኖሩንም አላውቅም!! ፊልም ላይ እንኳን ትኩረታቸው ከንፈር እንጂ እጅ እና ከንፈር ሲገናኝ እንዲህ አስማታዊ ስሜት እንዳለው መች ይነግሩናል?
ቃሊቲ በሩ ላይ እንደደረስኩ ዘበኛው ሲያየኝ እንደተለመደው በወዳጅነት  «ቁርጠትዬ እስቲ ዛሬ ደህና ጊቢልኝ ታውቂ የለ ሚስትየው ስታላምጠኝ ነው የምትከርመው?» አለኝ።

«ይገባልሃል! ሂድ ባርችን ጥራልኝ!! እዚህ ስትቅለሰለስ እኮ እኔን አማክረህ አራት የወለድክ ነው የምትመስለው!»

«እሱማ ይጠራልሻል!! ግን ሰሞኑን ምርጫ ደርሷል ብለው የሌለ ህግ እያጠበቁ ነው!!»

«በቃ እሱ ታሳቢ ተደርጎ ይገባልሃል! መርዶ ሊነገራት ነው …. ወንድሟ ራሱን አጥፍቶ ነው …. መዓተኛ አይደለህ? አንዱን ቀባጥርና ጥራልኝ» ብዬ ከኪሴ ብር አውጥቼ አቀበልኩት። እሱ ወደ ውስጥ ሲገባ እየሆነ ያለውን ባላየ ዝም ብሎ የተቀመጠውን ሌላ ጠባቂ ብር በያዘ እጄ ጨበጥኩት። እየወተወተ አመሰገነኝ!!

«ያልጠየቅሽኝን እያካካስሽ ነው በየቀኑ?» አለች እሙ ገና ከመድረሷ «ጎንጤ ጥጋቡስ ዛሬ የለም?»

« ሁሉንም ነገር ላስረዳሽ ጊዜ አይበቃኝም!! እርዳታሽን ፈልጌ ነው የመጣሁት!! ከዛ ደግሞ በአጭሩ ትናንት ላይሽ የመጣሁ ጊዜ የማውቀው ታሪክ አልነበረም። የተመታሁ ጊዜ ሚሞሪዬን እንዳለ አጥቼ ነበር።»

«እና አሁን?» ብላ ግራ ገብቷት ከላይ እስከታች አስተዋለችኝ።