Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አንድ) (ሜሪ ፈለቀ) « | ወግ ብቻ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አንድ)
(ሜሪ ፈለቀ)

« የበፊቷን ሴት መሆን አልፈልግም!!!» አልኩት ኪዳንን እንዴት እንደምናስወጣው የሚያቀርበው አማራጭ ሁሉ የሆነን ሰው ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሲሆንብኝ

«ይሆንልሻል ?» አለ ማደንዘዣው እየለቀቀው የቁስሉ ህመም እየተሰማው ሲያወራም ጭምር እየተሰቃየ ።
«ውስጥ ያለህ ሰው ካሜራ መግጠም የሚያስችል ቅርበት አለው?»
«ይመስለኛል!! ምን አስበሽ ነው? ስልኬን ከኪሴ ውስጥ ወዲህ በይውማ እርግጡን ልንገርሽ! በቅድሚያ ግን ያሰብሽውን ልስማው?»

አመነታሁ! ከራሴ ውጪ ማንንም ሰው አምኜ የማውቅ ሰው አልነበርኩም! አለማመን በደሜ ውስጥ ያለ ነገር ነው። በሁለት ወር ከምናምን ጊዜ ሙልጭ ብሎ ሊጠራ አይችልም። የብዙ ዓመት ልምዴ ሁሌም ጀርባ እና ፊቴን ራሴው ስጠብቅ ፣ በመንገዴ የተደገፍኳቸው ሲንሸራተቱብኝ ፣ ከጎኔ ናቸው ያልኳቸው ጎኔን ሲወጉኝ ….. ነው። አውቃለሁ እኮ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶልኛል። በማንም ሰው ሚዛን ከዚህ በላይ ከእኔ ጎን መሆኑን ሊያሳይለት የሚችል ምንም ማረጋገጫ አይኖርም። በቃ ግን የዛች ሜላት ልብ አመነታ። ለአፍታ ዝም ስል ገብቶታል።

«አሁንም እምነትሽን አላገኘሁም ማለት ነው?? እንዲያው ምን ባደርግልሽ ነው የምታምኝኝ ዓለሜ?» የጎንጥ ድምፅ አይመስልም። ሳላምነው እንኳን የሚቆጣኝ ድምፅ ሳይሆን ምንም ማድረግ የማይችል በጣም የተከፋ ድምፅ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ <ዓለሜ> ብሎ እንደጠራኝ ያላስተዋልኩ መስዬ አለፍኩ።

«እሺ ይሁን!! ዝርዝሩን አትንገሪኝ!! እንዲሆን የምትፈልጊውን ብቻ ንገሪኝ!!» አለ በዛው በከፋው ድምፁ

«ውስጥ ያለህን ሰው ምን ያህል ታምነዋለህ?»
«በመድሃንያለም!! አንች የምታውቂያቸውን ሰዎች አላውቅም!! እኔ የማውቃቸው ግን እስከህይወት የሚታመኑኝ ሰዎች አሉኝ!!»

ለእኔ የማመን ትርጉም እርሱ ካለው ይለያል። አመኔታ ከሚታመነው ሰው ይልቅ የሚያምነው ሰው ላይ ይመስለኛል ጫናው። ማንንም ሰው <እገሌ በፍፁም አይከዳኝም! በፍፁም ፊቱን አያዞርብኝም!> ብሎ መቶ ፐርሰንት ሰውየው ላይ መዘርፈጥ የዋህነትም ጅልነትም ነው። ምክንያቱም ማንም ሰው በማይደራደረው ነገር ከመጡበት አሳልፎ ይሰጥሃል። እኔ እገሌን አምነዋለሁ ስል ፍፁም አይከዳኝም ማለቴ ሳይሆን ቢከዳኝ ወይ ፊቱን ቢያዞርብኝ እንኳን ያለበቂ ምክንያት አልከዳኝም ብሎ ምክንያቱን ለማወቅ ክፍት እስከመሆን የሚደርስ ልብ አለኝ ማለት ነው። ከበቀል በፊት <ለምን?> ብዬ መጠየቅ የምችልበት ልብ ካለኝ ያን ሰው አምኜዋለሁ ማለት ነው።

ሰዎች በፍቅር ለወደቁለት ሰው <አምንሃለሁ> ወይም <አምንሻለሁ> ብለው ልባቸውን ሲሰጡ ያን የወደዱትን ሰው <በፍፁም ልቤን እንደማትሰብረው አውቃለሁ!> እያሉት ነው እንዴ? እኔ አይመስለኝም። <ብትሰብረው እንኳን ልሰጥህ ዝግጁ ነኝ! ብትሰብረው እንኳን ህመሙን እስከመቀበል ድረስ ነው ፍቅሬ!> እያሉት እንጂ!


«አትፍረድብኝ! የመጣሁበት መንገድ ከሚታመኑት ይልቅ የማይታመኑት የበዙበት ነው! በዛ ላይ አንዲት ስህተት ብሰራ አደጋ ላይ ያለው ኪዳን ነው! በሱ ጉዳይ ማንም ላይ ባልታመን ተረዳኝ!! ደግሞም እኮ ጎንጥ ለልጅህ …… » ብዬ ነገሩን መጨረስ ይቅር ያላልኩት ያስመስልብኛል ብዬ ተውኩት

«ላውጋሽ ሁሉንም ከስር መሰረቱ አልኩሽ እኮ ዓለሜ? ስሚኝና ቅያሜሽን ያዥው ካሻሽ!»
«ቅያሜ አይደለምኮ! ግን እረስቼዋለሁ ብልህ ውሸቴን ነው!»

እውነታው ይቅርታ ማድረግ እና መርሳት ይለያያል።  ይቅር ብዬዋለሁ ማለት ከዛ በኋላ ያደረገኝን ነገር ሳስታውስ ቁጣ ወይም በቀል ወይም ጥላቻ ሳይሰማኝ አልፈዋለሁ ማለት ነው እንጂ ድርጊቱን ረስቼዋለሁ ማለት አይደለም!! ይቅር ብያለሁ ማለት የበደለኝን ሰው ሳየው ለቡጢ የሚዘረጋው እጄ ለማቀፍ መዘርጋት ይችላል ማለት እንጂ ያ ሰው በዛው ወጥመድ እንደማይጥለኝ አምኜ (መጃጃል ብለው ይቀለኛል) መጠንቀቅ እተዋለሁ ማለት አይደለም!! በኔ ልምድና ፍቺ ይቅርታ ይህ ይመስለኛል። ሀይማኖተኛም ባልሆን ከሰማኋቸው ጥቂት የመፅሃፍ ቅዱስ ስብከቶች በመነሳት እራሱ እግዚአብሄርም ይቅር ብዬሃለሁ ሲል በጥፋትህ አልቀጣህም ምህረት አጊንተህበታል ማለቱ እንጂ ስራህን ረስቸዋለሁ ማለቱ አይመስለኝም። ቢሆን ኖሮ እስራኤሎችን አንድ ሺህ አንድ ጊዜ ይቅር ካላቸው በኋላ አንድ ሺህ ሁለተኛ ጊዜ ባዕድ ሲያመልኩ ከግብፅ ካወጣቸው ጀምሮ የበደሉትን ባልዘረዘረላቸው ነበር።
ጎንጥ እኔጋ መስራት ከጀመረ ከተወሰነ ወር በኋላ ልጁ ታማበት ነበር። ለሳምንት አስፈቅዶኝ ጠፍቶ ተመልሶ ሲመጣ ልቡ ተሰብሮ ልጁ ኩላሊቷ መቀየር እንዳለበት እና የሱ ኩላሊት ማች እንዳላደረገ ሲነግረኝ ምክንያቴ ለሷ ማዘን ይሆን ለሱ ወይም በደም የጨቀየ ህይወቴን በደል መቀነስ ለማላውቃት ህፃን ኩላሊቴን ልሰጥለት ፈቃደኛ ነበርኩ። ሄጄ ምርመራውን አድርጌላት ነበር።

የዛን ቀን ለእመቤት ይገርማታል ብዬ ለጎንጥ ልጅ ላደርግ ያሰብኩትን ስነግራት እሷ ግን በሚያሳዝን አይን እያየችኝ
«ሜልዬ? የመረጥሽውን ህይወት ድጋሚ የማስተካከል እድል ቢኖርሽ ምርጫሽ ይለይ ነበር?» አለችኝ

«አላውቅም! አስቤው አላውቅም! ምናልባት እንደማንኛውም ሰው ዓይነት ህይወት ኖሮኝ ቢሆን ምን እንደምመርጥ አላውቅም!! ግን ማንኛዋም ህፃን እኔ ያለፍኩበትን መንገድ አላለፈችም!! ማንኛዋም ህፃን እኔ ያየሁትን አላየችም!!»

«እኔ ግን ሲመስለኝ እንደማንኛዋም ሴት ሚስት መሆን እናት መሆን ….. ስስ መሆን …. ማፍቀር …. ባፈቀሩት ሰው ልብ መሰበር ….. ማለቃቀስ ….. እነዚህን ሁሉ የማድረግ ፍላጎት  ልትሰሚው ስለማትፈልጊ እንጂ የሆነ ልብሽ ጥግ ተደብቆ ያለ ይመስለኛል።» አለችኝ። ጋዜጠኛ አይደለች? ወሬ ማዳመቅ ትችልበታለች።

«ሌላውስ ይሁን ልብ ተሰብሮ ማልቀስ መፈለግ የጤና ነው?» አልኳት ወሬው ሲኮሳተር ራሴን እፈልግ ይሆን አልፈልግ መጠየቅ ሽሽት። አፍቅሬ አላውቅም ወይም ፍቅር ይሉት ነገር በእኔ የህይወት ጉዞ ገደቡን ያለፈ ቅብጠት ነው። ከቅፅበት ስጋዊ መንደድ አልፎ አቅሉን ስቶ በፍቅሬ የነሆለለ ወንድም አላስታውስም!! ጭራሹኑ ከልብሴ ስር የሴት ገላ መኖሩ ትዝ የሚለው ወንድ ልብሴን አውልቄ ያየኝ ብቻ ይመስለኛል።

«እሱ ራሱ ጣዕም እንዳለው ብታውቂ? አፍቅረሽ ጧ ብለሽ! ከሌላ ሴት ጋር አየሁት ብለሽ ግንባርሽ ላይ ሻሽ ሸብ አድርገሽ ትኩስ ነገር የሞላው ኩባያ ይዘሽ ለጓደኛሽ ማውራት ……. »

«በይ እናቴ ያንቺ የጤና ፍቅር አይደለም! ታየኝኮ ማግ ይዤ ለወንድ ስንሰቀሰቅ!» ብያት ስቄ ከደንኩት። 

የጎንጥን ልጅ ሆስፒታል ሄጄ ሳያት ተስፋ ባዘሉ የልጅነት ዓይኖቿ ውስጥ የራሴን ልጅነት አየሁት። ኩላሊቴ ሊያድናት እንደሚችል  ሲነገረኝ የነበረኝን የደስታ ስሜት የዛሬን ያህል አስታውሰዋለሁ። ከዛን ቀን በፊት ሆስፒታል የመተኛት ከፍተኛ ፍርሃት ነበረብኝ። በተለይ ማደንዘዣ የሚያስወስድ ነገር ከሆነ። ራሴን ባላወቅኩበት ቅፅበት የሆነ ሰው የሆነ ነገር ያደርገኛል ብዬ እፈራለሁ። በጥይት ተመትቼ ሀኪም አምኜ ሆስፒታል የማልተኛ ሴት በገዛ ፈቃዴ ቅደዱና ኩላሊቴን አውጡ ብዬ የሆስፒታል አልጋ ላይ ልተኛ ዝግጁ ነበርኩ። ማንም ምንም ቢያደርገኝ ይሁን ከዛች ህፃን አይበልጥም ራሴን አስቱኝ ብዬ ፍርሃቴን ልውጥ ዝግጁ ነበርኩ። መኪናዋን ጊቢ እስካስገባ እንኳን አቅበጥብጦኝ

«እንኳን ደስ አለህ!!» ስለው ፊቱን ወደሌላ ቦታ አዙሮ እየተገማሸረ