Get Mystery Box with random crypto!

አንዲት ትንሽዬ የጭቃ ቤት በአስጠኚው በኩል አጊንተን ተከራየን!! የምንተኛበት እና የምናበስልበት | ወግ ብቻ

አንዲት ትንሽዬ የጭቃ ቤት በአስጠኚው በኩል አጊንተን ተከራየን!! የምንተኛበት እና የምናበስልበት ዕቃ ገዛን!! ኑሮ ተጀመረ!! መጀመሪያ አካባቢ መኪና ማጠብ ስራ አገኘሁ። አምስት መኪና በነፃ ካጠብኩ በኋላ ነው የቀጠሩኝ። ሰፈሩን መውጫ መግቢያ ተሽሎክሉኬ አወቅኩት። የሆነ ቀን ጠዋት ከኪዳን ጋር ዳቦ በሻያችንን በልተን ከቤት ልወጣ ስል
«ሜል?»
«ወዬ»
«እንዳትቆጭኝ! አልቆጣህም አባባ ይሙት በይ!» አለኝ ከዓመታት በኋላም የሞተውን አባቴን እየገደልን ነው የምንምለው።
«አባባ ይሙት አልቆጣህም ምንድነው?»
«እኔምኮ ትልቅ ልጅ ሆኛለሁ!! ስራ ፈልጌ የማልሰራው ለምንድነው?» አለኝ እንዳልቆጣው እየተሳቀቀ
«አባባ ይሙት እቆጣሃለሁ!! ሁለተኛ እንዲህ እንዳትለኝ!! አንተ አርፈህ ተቀመጥ ከወር በኋላ ትምህርት ሲጀመር ትምህርትህን ወጥረህ ትማራለህ!! ስራህ ትምህርትህ ነው!! ተግባባን?» ብዬ እንደፈራውም ጮህኩበት
«አዎ» ሲለኝ ስቅቅ ብሎ አሳዘነኝ እና አቀፍኩት።
«ላንተ ብዬኮ ነው!! ታውቅ የለ እንደምወድህ? አንተ ተምረህ ስራ ስትይዝ ያኔ አንተ ትሰራለህ እኔ እቤት እቀመጣለሁ!! አሁን ግን እኔ ታላቅህ አይደለሁ? እኔ እሰራለሁ አንተ ትማራለህ!!» ስለው ጭንቅላቱን ነቀነቀ። እናት መሆን ፣ ልጅ ማሳደግ ምኑም በቅጡ ሳይገባኝ ለካ እናትም የመሆን ሀላፊነትን ወስጃለሁ።
የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አንዱ በጉልቤነቱ የሚፈሩት ጥጋበኛ ሴት ሆኜ ከወንዶቹጋ መኪና ማጠቤን ሊያፌዝበት ሞከረ። ያልፈጠረብኝን አይ አለመተዋወቅ ብዬ ታገስኩት። በሌላኛው ቀን መጥቶ ግን ከኋላ ቂጤን ሲመታኝ መታገስ የምችልበት ልብ አጣሁ እና አፍንጫውን አልኩት። በቦታው የነበረው ሁሉ ደንግጦ ብድግ አለ። ልጁ ያልጠበቀው ቡጢ ስለጠጣ መጀመሪያ ተደናግጦ የደማ አፍንጫውን መጠራረግ ጀመረ። ቀጥሎ ግን ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ ሊገለግሉት የያዙትን ሁሉ እየተወራጨ ደነፋ!! እኔ በናታችሁ ልቀቁት ስል ፣ እሱ ከወድያ ልቀቁኝ ሲል …. አንድ በአንድ ሰው እየተሰበሰበ የፈሪ ድብድብ ሆነ። ድንገት ለቀቁት እና እኔና እሱ ተያይዝን። ለካስ ሲገላግሉ የነበሩት ልጆች የሸሹት ፖሊሶች መምጣታቸውን አይተው ነው። ፖሊሶቹ ማናችንንም ምንም የጠየቁትም ያጣሩትም የለም! አፋፍሰው ብቻ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን።

<እባካችሁ ትንሽ ወንድሜ ብቻውን ነው> ብል ማን ይስማኝ? ጀርባዬ ላይ ካሳረፈው ጥቁር ዱላ ህመም በላይ የተሰማኝ የኪዳን ብቻውን በፍርሃት መራድ ነው። ትቼው የጠፋሁ ይመስለዋል? ሊፈልገኝ ወጥቶ መንገድ ይጠፋበት እና የማያውቀው መንደር መንገድ ላይ ሲያለቅስ ታየኝ። ብዙ ክፉ ነገር ታየኝ። ተንዘፈዘፍኩ። ደቂቃ ባለፈ ቁጥር ፍርሃት ከአንጀቴ ይተራመሳል። ሰዓቱ አይሄድም!! ማልቀስ እፈልጋለሁ ግን እንባ አይወጣኝም።

<ጥጋባቸው በርዶላቸዋል> ብለው በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ሲለቁን እግሬ መሮጥ አቅቶት ተንቀጠቀጠ። የቤቱን በር አልፌ ስገባ ኪዳን ባይኖር የት ብዬ ነው የምፈልገው? ራሴን ረገምኩ! ደህና ተደላድሎ ከሚኖርበት ቤት ይዤው የወጣውበትን ቀን ረገምኩ። ሰውነቴ እየተንቀጠቀጠ በሩን ከፍቼ ስገባ ኪዳን ኩርምት ብሎ ፍራሹ ላይ ተቀምጧል። ሲያየን ዘሎ እላዬ ላይ ተሰቅሎ እንደህፃን ድምፅ አውጥቶ ማልቀስ ጀመረ። የሱ መርበትበት ይብስ አርበተበተኝ እና አብሬው እዬዬ ማለት ጀመርኩ። እህል ሳይበላ ከአሁን አሁን መጣች ብሎ ኩርምት ብሎ በር በሩን ሲያይ ነው ያደርኩት።

ፈሪ ሆንኩ! ለኪዳን ስል ፈሪ ሆንኩ!! ለእሱ ስል ብቻዬን ብሆን የማልውጠውን ብዙ መናቅ ዋጥኩ። ለእሱ ስል የማላልፈውን ውርደት አለፍኩ። አንገቴን ደፋሁለት!!! ከብዙ ስራ ቅየራ በኋላ …… ኪዳንም ትምህርቱን ብዙ ቀን ከተማረ በኋላ ….. ብዙ ጥጋበኛ አንገቴን ደፍቼ ካሳለፍኩ በኋላ …..….. በራሴው ሰውንም ከተማውንም መልመድ ከጀመርኩ በኋላ…….  የከተማ ሚኒባስ ወያላ ሆኜ እቁብ መጣል ከጀመርኩ በኋላ …… አንድ ቀን ተሰብስበን ተራ የምንጠብቅበት ቦታ ኪዳን መጥቶ ሲፈልገኝ በእድሜ በጣም ከሚበልጠው ልጅ ጋር ነገር ተፈላለጉና ኪዳንን በቁመቱ አንስቶ በጠረባ ጣለው። ደርሼ ልጁን ሳንጠለጥለው ከሚፈላው ደሜ ውጪ የሚሰማኝ ነገር አልነበረም። ምን እንዳደረግኩ አላውቅም!
«ሜል!» ብሎ ኪዳን ሲለምነኝ ነው ጆሮዬ ድምፅ መስማት የቻለው። ፖሊስ ከመቼ መጥቶ ብዬ ስሳቀቅ ግርግሩ ሰክኖ የሆነ ሰውዬ ተጠጋኝ እና
«ስራ ልስጥሽ! እዚህ ከተሳፋሪ ፍራንክ እየለቃቀምሽ ፀሃይ እና ዝናብ እየተፈራረቀብሽ ከምታገኝው እልፍ እጥፍ ደመወዝ የሚከፈልሽ ስራ ላስቀጥርሽ! » አለኝ
«እንዴ ምንድነው ስራው ?» አልኩት
«ደውዪልኝ» ብሎ ስልኩ ያለበት ቢዝነስ ካርድ ሰጥቶኝ ሄደ። ተሰብስቦ የነበረውን ወሬኛ አላስተዋልኩትም ነበር።
«ኸረ በለው! በአንድ ቦክስኮ ስሙን ሁሉ ነው ያስረሳሽው!! መሬት ሲደርስ ኦልሬዲ ቤተሰቡን ዘንግቷል!!» እያሉ ትከሻዬን አቅፈው ማውራት ጀመሩ። ሊያዋራኝ ይኮራ የነበረ ሁላ ጓደኛዬ ሊሆን ሰበብ ይፈልግ ጀመር።

አልጨረስንም!!!

@wegoch
@wegoch
@paappii