Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ) (ሜሪ ፈለቀ) እነዛ ጫ | ወግ ብቻ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ)
(ሜሪ ፈለቀ)

እነዛ ጫማ ያልለበሱ እግሮቻቸው ፣ የከብት ሽታ የሚሸት አዳፋ ልብሳቸው ፣ ያለፉበት መከራ የተፃፈበት የግንባራቸው መስመር ፣ ዘመናቸው ድሎት እንዳልጎበኘው የሚያሳብቁት ሻካራ እጆቻቸው ፣ ብራቸውን ስወስድባቸው እንድራራላቸው የሚለማመጡ ከርታታ ዓየኖቻቸው …….. ከአጠገባቸው ርቄ እንኳን አልራቀኝም!! የስንት ቀን የልጆቻቸው ምሳና እራት ይሆን? ምናልባት የሚያፈስ ቤታቸውን ሊያድሱ ይሆናል! ምናልባት የሚከፍሉት እዳ ይኖርባቸዋል! …… ብዙ ርቄያቸው ከሄድኩ በኋላ በጉልበቴ መሬቱ ላይ ዘጭ አልኩ!! አባቴ <ጀግና አያለቅስም!> ብሎ ቢያሳድገኝም ዛሬ መጀገን አቃተኝ! ለአፍታ ተመልሼ ሄጄ ብሩን ሰጥቻቸው የመምጣት ሀሳብ ሁላ ሽው ብሎብኝ ነበር። ይሄ ምስላቸው ለዓመታት ስቃዬ ነበር። ከበደሉኝ ሰዎች እኩል የበደልኳቸው ሰዎች ፊት እንቅልፍ የማያስተኛ ቅዠቴ ነበር። ለደቂቃዎች እዛው በጉልበቴ ከተንበረከኩበት የመጨረሻዋን አውቶቡስ ተሳፍረን አሁኑኑ ካልወጣን ፖሊሶቹ እኛ ቤት ለመድረስ ምንም የምርመራ ሂደት አይፈጅባቸውም!!

እንባዬን ጠራርጌ ሮጥኩ!! ያገኘሁትን የእኔን እና የኪዳንን ልብስ በፔስታል ጨመርኩ። ያለችንን አንድ ለእናቱ ጫማ ተጫምተን ወደመነሃሪያ እጁን ይዤ መሮጥ ጀመርኩ። መነሃርያው አካባቢ ስንደርስ ከኋላዬ ሁለት በእድሜ ጠና ያሉ የኛ አካባቢ የማይመስሉ ሰዎች ሲያወሩ ወሬያቸው ጆሮዬን ጠለፈው።
«የወዲያ ቀዬ ሰዎችን ዛሬ ሽፍታ ዘረፋቸው የሚሉትን ወሬ ሰማህ?»
«ኸረ አልሰማሁም!! ወደየት ግድም?»
«ከገበያው ጫፍ ትንሽ ቢርቁ ነው አሉ!! አንደኛው ይሄ በሬ ሻጩ አያልነህን አታውቀውም?»
«አያልነህ? አያልነህ?»
«ይሄ ሲያወራ ምራቁን እንትፍ የሚለው? ይህ እንኳን ወንድ ወልዳለሁ ብሎ ሲተኛ ስድስት ሴት ያሳደገው? በመጨረሻ ሚስቱ ወንድ ልጅ ሰጥታው እንዴየውም ደግሶ ያበላ ጊዜ አቅልህን እስክትስት ጠጥተሃልይ!!»
«እንዴ? እንዴ? አያልነህ በሬ ሻጩ?»
«ኤድያ እንዴት ያለው እምከፍ ነው? ምን እያልኩት ምን ይላል?»

ፍጥነቴን አቀዝቅዤ ወሬያቸውን ከሰማሁ በኋላ ድጋሚ መፍጠን ጀመርኩ። <አያልነህ> የሚለው ስም ጭንቅላቴ ውስጥ ልክ እንደዛ የአባቴን ሬሳ ተራምዶት እንዳለፈው ሰውዬ ኮቴ ታተመ።
«ሜል? ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሽው?» ብሎ ኪዳን ዓይን ዓይኔን እያየ ሲቁለጨለጭ ነው እንባዬ እየወረደ መሆኑን ያወቅኩት።
«ምንም አልሆንኩም!!»
«ምንም ሳትሆኚ ታዲያ እንባሽ ይፈሳል? እኔ ይዘሽኝ ካልሄድሽ ብዬ ስላስጨነቅኩሽ ነው?»
«ይሄ ደግሞ! ለምን አርፈህ አትሄድም? እኔ አስጨንቀኸኛል አልኩህ?» እየተነጫነጭኩ እንባዬን ጠርጌ ትኬታችንን ቆርጠን አውቶብስ ውስጥ ገባን!! ከከተማዋ እየወጣሁ በአውቶብሱ መስኮት ወደኋላዬ የሚያልፈውን ተወልጄ ያደግኩበት መንደር ሸኘሁት። ድብልቅልቁ የወጣ ስሜት ተሰማኝ። ትቼው ስሄድ ሀዘን ካጠላበት ጊዜያቶች ይልቅ የታሰበኝ

የአባቴ ትከሻ ላይ እንኮኮ ተደርጌ ከጫካው እስከ ጠላ ቤት ግርግሩ ስዞር ጠላ ቤት እግሩ ላይ አስቀምጦኝ  በሰዓቱ የማይገቡኝን ወሬዎች እየቀደደ ጠላውን ሲጠጣ እናቴ ከሩቅ እየተራገመች መጥታ «ልጅቱን ጭራሽ አምቡላችሁ መሃል ይዘሃት ትመጣ?» ብላ ከእግሩ አንስታኝ የምትሄደው

አባቴ ገበያ መሃል ጠብመንጃውን እንዳነገተ ሲያልፍ አላፊ አግዳሚ ከአንገቱ ጎንበስ ብሎ ከልብ በሆነ አክብሮት ሰላምታ ሲያቀርብለት ትከሻው ላይ ሆኜ የተቆነንኩት
ከወዳጆቹጋ ሰብሰብ ብሎ ዳማ ከሚጫወትበት አብሬያቸው ሳነግስ እማዬ ትመጣና <ልጄን በቃ ወንዲላ አድርገህ ባልም ልታሳጣብኝ ነው!> ብላ ገና በ10 እና በ11 ዓመቴ ሀሳብ የሚገባት የነበረው
አንድ ቀን አባቴ ሽጉጡን አስይዞኝ ስታይ ለቅሶ እንደተረዳች ጭንቅላቷን ይዛ እሪሪሪሪሪሪ ብላ ጮሃ ጎረቤት አሰብስባ «ይሄን ሰው አንድ በሉኝ» እያለች ወገቧን ይዛ የተንጎራደደችው
እናቴ ከምትሸጠው ፍራፍሬ ላይ ከገበያ ስትመለስ ለምድረማቲ ትሰጥና እኛ ቤት ደጅ ላይ የተሰጠንን እየበላን የምንዘለው
ከትምህርት ቤት ስንመለስ ከቤተሰብ ተደብቀን ወንዝ ወርደን እየተንቦጫረቅን ባልተገረዘው ልጅ ወ*ላ ንፍር ብለን የምንስቀው
ክረምት ላይ እማዬ ቡና እያፈላች የተቀቀለ በቆሎ እየጋጥን እጣኑን ስትሞጅረው <አስካል ጥይት ያልገደለኝን ጀግና በጭስ ልትገይኝ ነው ሀሳብሽ?> ሲላት ከተናገረው ውጪ እሷ ምን እንደገባት ሳይገባን እንደመሽኮርመም እያደረጋት <እንደው ወሬ ስታሳምር ቅም!> እያለች ጭሱን በተን በተን ስታደርግለት የነገሩ ውል ምን እንደሆነ ባይገባንም እኔና ኪዳንም አብረናቸው የምንሽኮረመመው
<አስካል ነይ እስኪ ጀርባዬን ዳበስ ዳበስ አድርጊኝ በሞቴ!!> ሁሌም መምጣቷ ላይቀር ጓዳ ሆና <እስኪ ስራ አታስፈታኝ አንተ ሰውዬ> ስትል <ተይዋ ነይማ አምሳሌ!> ይለኛል እንደመጥቀስ እያደረገኝ። እጇን እያደራረቀች እያጉረመረመች መጥታ ትከሻውን ጀርባውን ታሸዋለች።

እንዲህ እንዲህ ዓይነቱን ቀን ነው ያስታወስኩት! አስታውሼም በአውቶብሱ መስኮት የሸኘሁት!! አባቴ የሞተ ቀን ይሄ ሁሉ አብሮ ከአባቴ ጋር የተቀበረ ሳይሆን ልቤ ያን ንፁህ የልጅነት ጊዜም ልብም ዳግም ላላገኘው ልክ የዛን እለት የተሰናበትኩት ያህል አንሰፈሰፈው ……. ሁሉም ነገር ልክ የዛን ቀን የተሰናበትኩት ያህል….. የሚገጥመው አቀበት ታውቆት ነበር መሰለኝ! የአብቶብሱ መቀመጫ ላይ አጠገቤ የተቀመጠውን ኪዳን ጭምቅ አድርጌ አቅፌ

«አንተ አብረኸኝ ስላለህ ደስ ነው ያለኝ!! የማለቅሰው አጎቴ ስለሚናፍቀኝ ነው!! ሰፈሩ ስለሚናፍቀኝ ነው!! ባንተ አይደለም እሺ!!» እያልኩት ተደጋግፈን እንቅልፍ ወሰደን!!
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ <እንኳን ደህና መጣችሁ!> ብላ አልተቀበለችንም!! አውቶብስ ተራ እንደወረድኩ ነው ይሄ ከእኔ ዓለም በምንም የማይገጣጠም ውቅያኖስ እንደሆነ የገባኝ!! አዲስ አበቤዎች ሲያወሩ እንኳን የሚደማመጡ አይመስሉም። ሁሉም ያወራል፣ ሁሉም ይራወጣል፣ የተረጋጋ የለም! የት ሊሄዱ እንደሚቸኩሉ እንጃ ቸኩለው እያወሩ ቸኩለው እየተገጫጩ ይተላለፋሉ። ከራሱ መንገድ ውጪ ማንም በአካባቢው ያለውን አያስተውልም። በጩኸቱ ጆሮዬ ዛለ። ኪዳንን በአንድ እጄ ጥፍንግ አድርጌ ይዤ በሌላ እጄ ልብሳችን ያለበትን ፔስታል ይዤ <አልጋ> የሚሉ ልጆችን ተከትዬ የዛን ቀን የትኋን እራት ሆነን አደርን!! አዲስአበባ ቀማኛው ብዙ ነው ሲሉ ስለሰማሁ ምግብ ልንበላ በገባንበት ሁሉ የማየውን በጥንቃቄ እከታተላለሁ። በሀገሬ ባለፍኩ ባገደምኩበት ሰው የሚጎነበስልኝ ፣ ሁሉ የሚያውቀኝ ….. እዚህ ባዳነት ተሰማኝ። እዚህ ማንም ነኝ!! ከኪዳን ውጪ የሚያነጋግረኝ እንኳን የሌለ ማንም ነኝ!!
በበነጋታው ስልክ መደወያ ቦታ ፈልጌ አሰልጣኙጋ ስልክ ደወልኩ እና ያለንበት መጣ!!! የምንከራየው ቤት እስካገኝ እቤቱ ይወስደኛል መቼም የእግዜር እንግዳ ዝም አይባልም ብዬ ስጠብቅ እሱ እቴ!! የዛኑ ቀን በእጁ በያዛት ስልክ ለደላሎች ደውሎ ቤት እንዲፈልጉ ነግሮልኝ የማላውቅበት ምድረ ገበያ ህዝብ የሚተራመስበት ሰፈር አልጋ አስይዞን ሄደ። አሁን ብቻዬን እንደሆንኩ አወቅኩ!! አባት እና እናቴ የሉም! አጎቴ የለም! አሁን ለኪዳን እነሱን መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ ለካ!!