Get Mystery Box with random crypto!

ከሁሉም አይኔን የሳበችው ግን አንድ ጊዜ ‹እማዬ› አንድ ጊዜ ደግሞ ‹አባዬ› እያለች የምትጣራ እና | ወግ ብቻ

ከሁሉም አይኔን የሳበችው ግን አንድ ጊዜ ‹እማዬ› አንድ ጊዜ ደግሞ ‹አባዬ› እያለች የምትጣራ እና ሙልቅቅ ብላ አባዬን አላንቀሳቅስና ከሰው አላስወራ የምትለው ሕጻን ልጅ ነበረች፡፡ ሕጻኗን የ3 ዓመት ልጅ ገደማ መሆኗን መገመት ከባድ አልነበረም። የሚገርመው ግን ከ10 ቀን በኋላ ልክ 3 ዓመት የሚሞላት ልጅ መሆኗ ነበር፡፡ እሷ ማለት ደግሞ ያቺው ከላይ የተረኩላችሁ ተዓምረ-እግዚአብሔር ናት… "ሚጡ" እንበላት ለወጋችን ያክል፡፡ አባዬ እናቴ በምትጠራኝ ስም ‹በልዬ› እያለች ነው የምትጠራኝ፡፡ ሌላኛዋ አክስቴ ደግሞ ‹ጥላሁን› ነው የምትለኝ፡፡ በውስጤ ጥያቄ እንዳለ የገባት የመሰላት አባዬ ከምሳ በኋላ ቡና እየጠጣን በጨዋታ መሃል…‹‹ይኸውልህ በልዬ በስተርጅና ይቺን የመሰለች ልጅ ወለድኩ…›› ብላ ወሬ ከመጀመሯ ተዓምሪቷ ሚጡ አሁንም አላስወራ አለቻትና ከወሬው አናጠበቻት፡፡ ወዲያውም ደግሞ ለጠየቃትም ላልጠየቃትም ስሟን እስከ አያቷ ድረስ ደጋግማ መጥራት ትይዛለች፡፡
‹‹ማነው ስምሽ አንቺ…›› ሲሏት…‹‹እኔ… ሚጡ… አቡሽ… አባባ…›› ትላለች አሁንም አሁንም የራሷንም፣ የአባቷንም፣ የአያቷንም ስም ሳታዛንፍ በልጅ አፍ በትንሹ ኩልትፍ እያለችና ፊደላቱን እየጠራች፡፡ በአባትነት የምትጠራው አቡሽ በጥቂት ዓመት የሚበልጠኝን የአባዬ የመጨረሻ ወንድ ልጅ ነው፣ በአያትነት ደግሞ የአባዬን ባል (የአቡሽን አባት)…! ግራ መጋባቴ ቀጥሏል፡፡ አቡሽ የሚኖረው አሜሪካ እንደሆነና ይቺ ልጅ ከመወለዷ ብዙ ዓመት በፊት አግብቶ ልጆች
እንደወለደም አውቃለሁ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ አባዬ ወደ ጓዳ ሄድ ስትል… እህቴ ላይ የጥያቄ ፊት ዘረገፍኩባት፡፡ ይህን ያወጋኋችሁን ታሪክ እህቴ ከሌላኛዋ አክስቴ ልጅ ጋር ሆነው ፈጠን ፈጠን እያሉ ተጋግዘው በአጭሩ ነገሩኝ፡፡ ግፋ ቢል ከአምስት ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ አጠናቀቁት፡፡
‹ይህንንማ ከራሷ ከአባዬ ሙሉ ዝርዝሩን ካልሰማሁ በቀር አይሆንም…› አልኩና ለምሽት የእራት ላይ ጨዋታ አቆየሁት፡፡ አላስቻለኝምና እራት ገና እራት መብላት እንደጀመርን አነሳሁላት…‹‹አባዬ… ምንድን ነው ቅድም እኮ ስለዚህች ሕጻን ልጅ እንዲህ እንዲህ አሉኝ… ኧረ
እንደው ሙሉውን ንገሪኝ አባይዬ…›› ብዬ ጀመርኩ፡፡ ‹‹አይ በልዬ… የሷ ነገርማ ተዓምር ነው፡፡ ይሄ እናንተ በምታነቡት መፅሐፍ ውስጥ ራሱ ቢፈለግ አይገኝም…!›› አለችና ጀመረች፡፡ ‹ይሄ የምታነቡት መፅሐፍ ውስጥ አይገኝም›
ማለቷ በልብ-ወለድ እንኳን የማይታሰብ ነው ለማለት ነው፡፡ የንጽጽሯ ጥልቀት የገባኝ ታሪኩን ከጨረሰችልኝ በኋላ ነበር፡፡ Stranger than fiction የሚልና በጣም ወድጄ የተመለከትኩትን አንድ የሆሊዉድ ፊልም አስታወሰኝ አገላለጿ፡፡ ድንቅ ነበር ንጽጽሩ…!ለታሪኩ ስክት ብሎ የሚገባ ጠቅላይ ዐረፍተ ነገር…!ከዚያም ቀስ እያለች እስከላይ ድረስ የነገርኳችሁን ተረከችልኝ፡፡ የሰሙት ሁሉ እንደ አዲስ አደመጡ፡፡ አንዳንዴም በየመሃሉ እየገቡ ጨማመሩበት፡፡ ባለቤቴ በተፈጥሮ ያላት ቦጅቧጃ ስብዕና ላይ እናትነት ተጨምሮበት ፊቷን ለመግለጽ በሚከብድ ስሜት አብራኝ አባዬ አፍ ላይ ተተክላለች፡፡ እኔም በየመሃሉ ለማመን የሚከብደኝን ነገር በጥያቄ ማጣደፌ አልቀረም፡፡ ደጋግሜ የምጠይቃት ግን እንዴት ከሌቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እንደዚያ ሆና በሕይወት ተረፈች…? እንዴትስ እስከ ማታ 11፡00 ድረስ ጡት ሳትጠባ ልትተርፍ ቻለች…? እንዴትስ
እትብቷ በዚያ መልክ ተበጥሶ እና ሳይታሰር ተረፈች…? እናትየውስ እንዴት ተረፈች…? ማለቂያ አልነበረውም ጥያቄዬ፡፡ ‹‹አይ በልዬ እንደሚሉትማ እትብት በ30 ደቂቃ ወይም ቶሎ ተቆርጦ ካልተቋጠረ ልጅ ይሞታል ይባላል፡፡ በዚያ ላይ ብርዱ፣ ዝናቡ፣ ጡት አለመጥባቱ፣ እንደዛ በጭቃ እያድበለበለች ስትጫወትባት አድራ በሕይወት መትረፏ ሌላ ምን መልስ አለው በልዬ…የፈጣሪ ስራ ነው እንጂ! የእመቤቴ ማርያም ስራ ነው እንጂ! የባለወልድ ተዓምር ነው እንጂ በልዬ! የሚገድልም የሚያድንም አንድ ፈጣሪ እንጂ እንደ ሰው ግምትማ መች ትተርፍ ነበር…!» የሚል ነበር መልሷ። አባዬ ይህን ስትለኝ በወቅቱ አንቀጹ ትዝ ባይለኝም ድሮ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብኩት አንድ ጥቅስ ትዝ አለኝ፡፡
‹‹አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።›› ዘዳግም ምዕ.32፣ ቁ.39፡፡ እውነትም ይህን ጥቅስ ከማመን ውጪ ሌላ ሰውኛ ማብራሪያ ለመስጠት ከባድ ነውና
እኔም በፈጣሪ የማያልቅ ተዓምር ተደምሜአለሁ፡፡ እኔ በማምነው መንገድ በፈጣሪ ላይ ያለኝን እምነቴንም ይበልጥ አጠናክሮታል፡፡ አባዬ ብዙ ካለችኝ በኋላ ታሪኩን እያጠቃለለች ነው፡፡ ‹‹እናልህ በልዬ… እቤት ከመጣን በኋላ አቡሽዬ ሲደውል ነገርኩት፡፡ ‹አቡሽዬ… ይኸውልህ
በስተርጅና ሴት ልጅ ወለድኩ› አልኩትና ታሪኩን ስነግረው እጅግ ተደስቶ ለየዘመዱ እየደወለ ‹አባዬ ልጅ ወልዳለችና እንኳን ማርያም ማረሽ በሏት…› እያለ ሰዉን ሁሉ ግራ አጋባው፡፡ ወዲያውም የሚያስፈልጋትን በሙሉ እሱ እንደሚያሟላ እና የአባትነት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቃል ገብቶ ይኸውልህ ሚጡም በሱ ስም ትጠራለች… እሷም አባትሽ ማነው ስትባል አቡሽ ትላለች…›› አለችና ተነስታ ከፎቶ ማህደሯ ውስጥ ከልጅነቷ ከምሮ ያስነሳቻትን ፎቶዎች አምጥታ ሰጠችኝ፡፡ እየተቻኮልን እና እየተቀማማን ተመለከትነው፡፡ ገና የወር ዕድሜ ሳይሆናት ጀምሮ በየጊዜው የተነሳቻቸው ፎቶዎች ልዩ ናቸው፡፡ የአንድ ዓመት እና የሁለት ዓመት ልደቷ ሲከበር ድል ያለ ድግስ እንደነበረው መመስከር ይቻላል፡፡ ሁለት ፎቶዎች ትርፍ ቅጂ ስለነበራቸው አባዬን ለምኜ ፈቀደችልኝና ወሰድኳቸው፡፡ ከሁሉም ግን የልደት ፎቶዎቿ ይለያሉ…‹‹ይገርማል፣ በተለይ ለልደቶቿ ትልቅ ድግስ ነው ያደረግሽላት አባዬ…›› አልኩ፡፡ ‹‹እኔ አይደለሁም በልዬ… የሚገርምህ ልጅቷ ከዚህ ሁሉ ታሪኳ ቀጥሎ የሚገርመኝ በብዙ ነገር ዕድለኛ ነች፡፡›› አለችና በሁለቱ ልደቶቿ ወቅት ድግሱ እንዴት ሊያምርላት እንደቻለ የተከሰቱትን ድንገቴዎች አወራችኝ፡፡ ‹‹ይኸው አሁን ደግሞ ሶስተኛ ዓመት ልደቷ መጪው ባለወልድ ነው ከ11 ቀናት በኋላ፡፡ ነገር ግን ሚሚ መጪው ማክሰኞ ወደ አዲስ አበባ ስለምትሄድ ልደቷን ቀድመን እናክብር ብለን ነገ ልናከብርላት ወስነን ነበር፡፡ እኔም ቤት ባፈራው የሆነውን አደርጋለሁ ብዬ እንጂ በግ አርዳለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ይኸው ዕድለኛ ነች ብዬህ አልነበር… አምላክ ደግሞ ምንም የማታውቀውን አንተን በግ አስገዝቶ ላከላት… ታዲያ ከዚህ በላይ ዕድለኝነት
አለ…? ኧረ የሷስ ድንቅ ነው በልዬ…›› አለች፡፡
እንዳለችውም እኔ እጅ መንሻ ብዬ የወሰድኩላቸው በግ በነጋታው ዕለተ እሁድ ታርዶ፣ የልደት ግብዓቶች ሁሉ ተሟልተው ትልቅ ድግስ ሆኖ የሚጡ 3ኛ ዓመት ልደት በድምቀት
ተከበረ፡፡ ድንቅ እኛም እሁድን አድረን ሰኞ ወደ አዲስ አበባ ተመለስን…! ማክሰኞ ማታም ይህንን ታሪክ ማካፈል ጀመርን…!እነሆ ዛሬ ዕለተ ረቡዕም ለመደምደም እየተንደረደርን ነው…!
***
መውጪያ…
(እስቲ ደግሞ ጥቂት አብረን እንናደድ) እብዷን የደፈራት ሰው በአደባባይ የሚታወቅ ጤነኛ ሰው ነው መባሉን ስሰማ በመጀመሪያ የተሰማኝ ስሜት "ምናለ ፈጣሪ ያን የሚደፍራትን ሰው እጅ ከፍንጅ ቢያሲይዘኝ…" የሚል ነበር፡፡