Get Mystery Box with random crypto!

እውነት እብዱ ማነው? ክፍል - ሁለት (የመጨረሻ ክፍል) አባዬ፣ አለወትሮዋ የጠዋቱ ብርድ እና | ወግ ብቻ

እውነት እብዱ ማነው?
ክፍል - ሁለት
(የመጨረሻ ክፍል)

አባዬ፣ አለወትሮዋ የጠዋቱ ብርድ እና ዝናብ ከአልጋ አላላቅቅ ብሏት ተኝታለች። ሰዓቱን
ስትመለከት ሶስት ሰዓት ገደማ ስለሆነ እንደምንም ብላ ተነስታ ወደ ማርያም ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ሳያልቅ ለመድረስ ተጣድፋለች። በዚያ ላይ ከልጆቿ መካከል አራቱን የወለደችው በባለወልድ ቀን ስለሆነ ለባለወልድ የተለየ ስሜት አላት። "አዬ የኔ ጉድ፣ ለዛውም በባለወልድ ቀን እንዲህ ላርፍድ?" እያለች ነጠላዋን ተከናንባ ከወጣቷ ልጇ ሚሚ ጋር አውራ መንገዱን ተሻግረው ወደ ማርያም የሚያስገባውን መንገድ ሲጀምሩ ከአንድ ግቢ ውስጥ የሚጮኹ፣ የሚንጫጩ፣ የሚተራመሱ ሰዎች ሲመለከቱ በድንጋጤ እየተጣደፉ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሁለቱም በአይናቸው ያዩትን ማመን አልቻሉም…በግቢው ውስጥ ያለው አብዛኛው ሰው ፈራ-ተባ ባለበት ወቅት አባዬ አለፍ ብላ የማትናገር የማትንቀሳቀሰዋን ሕጻን አንስታ በሕይወት ትኑር ትሙት ለማወቅ ትንፋሿን ለማዳመጥ ሞከረች። ከሌቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ ሶስት ሰዓት ድረስ ለዘለቁት ሰባት ወይም ስምንት ሰዓታት ገደማ በዚያ አይነት ሁኔታ የቆየችው አራስ ልጅ አሁንም እስትንፋሷ አለ፡፡ በምን እንደተቆረጠ የማይታወቀው ቁራጭ እትብቷ አሁንም ሳይታሰር ጠልጠል እንዳለ ነው፡፡ አባዬ ሕጻኗን ለሚሚ ሰጥታ እየሮጠች ወደ ቤቷ ተመልሳ መጠራረጊያ እና ማቀፊያ የሚሆኑ ልብሶች ይዛ መጣች፡፡ ልጅቷን ሲጠራርጓት በጣም የገረማቸው ነገር ከጭቃ በቀረ ምንም አይነት ደም የቀላቀለ ነበር አልነበረባትም፡፡ ምናልባትም እናትየው ከወለደቻት በኋላ በዝናቡ ውስጥ መንገድ ላይ ዘለግ ላለ ጊዜ ይዛት ስለቆመች ዝናቡ አጥቧትም ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ጭቃዋ ሲጠራረግ ልቅም ያለች ቀይ ልጅ ብቅ አለች፡፡ ‹‹ፀጉሯ ግንባሯ ድረስ ድፍት ብሎ ቻይና ነበር እኮ የምትመስለው…›› ትላለች አባዬ ለኔ ባወራችኝ ጊዜ እንኳን ሶስት ዓመት ወደ ኋላ ተመልሳ በትዝታ፡፡ የግቢው ባለቤት፣ አባዬ እና ሚሚ ልጅቷን ከበው ምን እንደሚያደርጉ ለአፍታ መምከር ጀመሩ፡፡ ‹‹ለመንግስት እንስጣት ይሆን እንዴ…? ምን ይሻላል…? ምንስ እናድርግ…?›› ይላሉ
የግቢው ባለቤት፡፡ ‹‹አዪ ለመንግስት ብንሰጥስ ምን ይበጃታል ብለሽ ነው…? መጀመሪያ ግን ወደ ጤና ጣቢያ መውሰድ አለብን… ሌላውን በኋላ እናያለን…›› አሉ አባዬ ልባቸው የሚነግራቸው ሌላ መፍትሄ እንደሆነ በውስጣቸው እርግጠኛ ሆነው፡፡ መጀመሪያ ግን የልጅቷን ሕይወት ማትረፍ እንደሆነ ስለገባቸው ወደ ጤና ጣቢያ ለመውሰድ እየተሰናዱ፡፡ አባዬ በቃል አያውጡት እንጂ በልባቸው ያለውን አሳብ ምንም ሳይዘገይ ነበር ሚሚ ያቀበለችው፡፡ ይህ ሲሆን ሚሚ ነበረች የተጠራረገችውን ልጅ በማቀፊያ ይዛ የነበረችው፡፡ ‹‹አባዬ ይቺን ልጅማ ለማንም አንሰጥም… እኛው እናሳድጋታለን…›› አለች ፍጹም ፍርጥም ባለ እርግጠኝነት እና ስስት በእቅፏ ያለችውን አራስ ቁልቁል ትክ ብላ እያየች…‹‹ይሁን እኔም እንደሱ ነበር እያሰብኩ የነበረው… በይ ወደ ጤና ጣቢያ እንውሰዳት መጀመሪያ… በጣም ደክማለች…›› ብለው እየተጣደፉ ወደ ጤና ጣቢያ ሄዱ፡፡ ጤና ጣቢያ ደረሱ፡፡ ቁራጭ እትብቷም ተቋጠረ፡፡ ሙቀቷ 27 ዲግሪ ስለነበር በወቅቱ የነበረችው ሐኪም ወደ ማሞቂያ ክፍል እንድትገባ አደረገቻት፡፡ ሕጻኗ እየቆየች የበለጠ
ነፍስ እየዘራች ብትሄድም አንድም ጊዜ ስላልጠባች ጉዳት እየገጠማት ስለሆነ እነ አባዬ እብዷ ወዳለችበት ተመልሰው መጥተው እንዴት አድርገው እናትየውን አግባብተው በመውሰድ ልጅቷን እንድታጠባ ለማድረግ ከሰፈሩ ሰዎች ጋር ይመክራሉ፣ ይህ ሲሆን ተሲያት ሆኗል፡፡ የሚሚ ስልክ አቃጨለ፡፡ ሐኪሟ ነበረች… ‹‹ሐሎ አለች ሚሚ…›› ምናልባትም መጥፎ ዜና ልትነግራት የደወለች መስሏት እንደመደንገጥ ብላለች፡፡
‹‹ሐሎ… ምንድን ነው በዚያው የጠፋችሁት…እዚህ አምጥታችሁ ጥላችሁ የሄዳችሁትን
መጥታችሁ ውሰዱ እንጂ… ማን ላይ ጥላችሁ ለመሄድ አስባችሁ ነው…›› እያለች
አበሻቀጠቻት፡፡ ‹‹ስሚ የኔ እህት… እዚያ ጥለን የሄድነው ዕቃ አይደለም… የሰው ልጅ ነች እሺ…!?
እንዲህማ ልትናገሪ አትችዪም እሺ…! ለማንኛውም አሁን እንመጣለን ሌላ ትርፍ ነገር
አትናገሪ…›› ብላ እሷም አስታጠቀቻትና ወደ ጤና ጣቢያው ተመለሱ፡፡ እብዷም በዚህም በዚያም ተወስዳ ልጅቷን ባታጠባም ቢያንስ ኤች.አይ.ቪ እንድትመረመር ተደረገ፡፡ የፈጣሪ መልካምነት ማለቂያ አልነበረውምና እናትየው ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን ሲያውቁ ለሁሉም ትልቅ እረፍት ነበር፡፡ ልጅቷን የማጥባቱ ነገር ግን የሚሆን ስላልሆነ
ከአመሻሹ 11፡00 ገደማ የፎርሙላ ዱቄት ወተት ተገዝቶና በጡጦ ተበጥብጦ ልጅት አፍ ላይ ሲደረግ በርሃብ ስትናጥ የነበረችው ሕጻን ወዲያው መጥባት ጀመረች፡፡ አባዬ ትልቅ
እረፍት እና ደስታ ተሰማት፡፡ የሚገባውን ጊዜ ወስደው፣ ልጅቷ በሙሉ ጤንነትና ጥንካሬ ላይ ስትሆን አባዬና ሚሚ ልጃቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ ለአባዬ ትልቅ ትዝብት የነበረው ነገር እና እስካሁን ስታወራው እጅግ እየከነከናት ያለው ነገር አንዳንድ ሰዎች፣ የጤና ጣቢያዋን ሐኪም ጨምሮ የተናገሩት ነገር ተመሳሳይ እና እጅግ ኢሰብዓዊ የመሆኑ ነገር ነበር፡፡ ‹‹እንዲህ አይነቱ ልጅ ሲገኝስ ወስዶ ማሳደግ ነበር…! ግን ምን ዋጋ አለው… ሴት ሆነች እንጂ…! ወንድ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ቤት ይጠብቃል… ወይም ጥሩ እረኛ ይሆን ነበር… እያሉኝ እኔ ግን ልጄን ይዤ ስመጣ በጣም ነበር ደስ ያለኝ…›› ትላለች አባዬ አሁንም በጥልቅ ትዝብት የሰዎቹን ክፋት እየታዘበችና ወደኋላ እየተመለሰች፡፡ "ልጄ" ብላ ነው የምትጠራት። አባዬን ላስተዋውቃችሁ…?
አባዬ አክስቴ ነች… የእናቴ ታናሽ እህት… ከመንታ የማትተናነስ ቁርጥ እናቴን መሳይ…ከቁመና እስከ ፊት መልክ… ከድምጽ እስከ ውስጠ ስብዕና…! ላለፉት 14 ዓመታት አባዬን ባየሁ ቁጥር ስሜቱን ለማስተናገድ እጅግ ከባድ ነበር ለኔ፡፡ እናቴ ከሙታን ዓለም መጥታ የምታናግረኝ እስኪመስለኝ ድረስ ነበር መመሳሰላቸው… ድምጻቸው… ስብዕናቸው…እርጋታቸው… ጥርሳቸው… ጣቶቻቸው… ምኑ ቅጡ…!እናም አባዬን ለመጨረሻ ጊዜ ያየኋት ሌላኛዋ አክስቴ በሞተች ወቅት ለቀብር እዚያች ከተማ በሄድኩበት ጊዜ ነበር፡፡ እሱ ደግሞ ጊዜው ዘለግ እያለ ስለመጣ የሆነ ቀን ታላቅ እህቴን አብረን ሄደን እንደምንጠይቃት እንደዋዛ ቃል ገባሁላት፡፡ እህቴም የዋዛ አልነበረችም አውቃ ቀን አስቆረጠችኝ፡፡ እኔም ተስማማሁ፡፡ ቀኑ ደረሰና ከመጓዛችን በፊት ባለቤቴም የጉዞው ተሳታፊ እንደምትሆን አሳውቃን እጅግ ደስ የሚል ጉዞ አደረግን፡፡ አባዬን እና ሌላኛዋን አክስቴን እንዲሁም ዘመድ አዝማድን ከማየት እና ከመጠየቅ በዘለለ እንዲህ አይነት ተዓምረ ክስተት እመሰክራለሁ ብዬ ፍፁም አላሰብኩምም አልገመትኩምም ነበር፡፡ ቅዳሜ ተሲያት በኋላ ነበር የደረስነው፡፡ መምጣታችንን ቀድመን አሳውቀን ስለነበር ምንም ነገር ሳይጎድል ሁሉ ሙሉ ሆኖ ነበር የጠበቀን፡፡ ደስታው ልዩ ነበር፡፡ የአክስቶቼ ስስት የሚዘገን የሚታፈስ ነበር፡፡ እናቴን እያስታወሱ ለማለቃቀስ ሞከር አድርጓቸውም ነበር እኔ ኮምጨጭ ብዬ መለስኳቸው እንጂ፡፡ እነሱ እንደሁ እናቴን አንስተው ለማልቀስ ጥንጥዬ ነገር በቂያቸው ነች፡፡ በዛውም እንደ ወናፍ እስክወጠር ድረስ ‹ዘመድ ጠያቂና ቁምነገረኛ› መሆኔ ተደጋግሞ
ሲነገረኝ፣ ስመሰገን፣ አሁንም አሁንም ስመረቅ እንደ መነፋፋትም ቢጤ ሞክሮኝ ጎምለል ማለቴ አልቀረም፡፡ ቤቱ ውስጥ የአክሰቶቼ ልጆች፣ ጎረቤት፣ ተጨማሪ ዘመድ አዝማድ ውር ውር ይላል፡፡