Get Mystery Box with random crypto!

አሜሪካዊቷ Elinor Ostrom (ሊን) በ2009 በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ኖቤል ሽልማት ያገኘች የመጀመ | The Ethiopian Economist View

አሜሪካዊቷ Elinor Ostrom (ሊን) በ2009 በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ኖቤል ሽልማት ያገኘች የመጀመሪያዋ ሴት የፖለቲካ ሳይንቲስት ነች:: በርግጥ ከኢኮኖሚስቱ Oliver Williamson ጋር በጋራ ነው የተቀበሉት (ከሷ በመቀጠል በ2019 ድህነት ቅነሳ ላይ በሰራችው ስራ በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ኖቤል የወሰደችው ሁለተኛዋ ሴት የ46 ዓመት ሴት ፈረንሳዊቷ Esther Duflo ስትሆን በMIT መምህር ናት)::

ነገር ግን በ#Economic_Governance ማለትም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ሃብቶችን ስለማስተዳደር በሰራችው ጥናት ዓለም የሚያከብራት ታላቅ ኢኮኖሚስት Elinor Ostrom ለዓለም ያስተዋወቀችው ዋናው ሃሳብ በማህበረሰብ ውስጥ የጋራ የምንላቸው መገልገያዎች እንዳሉ ይታወቃል::

ኦስትሮም እንደምትለው የጋራ መገልገያዎችን ሰዎች በፍታዊነት እንዲጠቀሙበት ከተፈቀደ (ከማንም ጣልቃ ገብነት ውጪ ማለቷ ነው) የማስተዳደሪያ ህጎችን አውጥተው በመጠቀም በገቢም ተጠቃሚ ሆነው አካባቢያቸውንም በዘላቂነት እንዲንከባከቡ ያግዛል ትላለች::


#ለምሳሌ:- ወንዞች፤ የግጦሽ መሬት እንዲሁም ደኖች የወል/የጋራ (Common Resources) መገልገያ እንደሚባሉ ይታወቃል:: ነገር ግን እነዚህን የጋራ መገልገያዎች እንዴት በጋራ በፍታዊነት መጠቀም እንደሚቻል የሚያስረዳ ታላቅ ሃሳብ ነው፡፡

ለዚህ አካሄድ ያዋጣል ያለችውን 8 መንገዶች አስተዋውቃለች፡፡ እነሱም….

1.የጋራ ሃብቶችን በአግባቡ መከለል እና ተጠቃሚዎችን መለየት፤

2.አካባቢያዊ የአጠቃቀም ደንቦች እና ህጎች ማውጣት፤

3.ሁሉንም አካላት ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ ማድረግ፤

4.የአጠቃቀምን ፍታዊነት የመከታተል እና የመቆጣጠር ስራ መስራት፤

5.ህጎችን የሚጥሱ አካላትን ማስጠንቀቅ እና መቅጣት፤

6.በባህላዊ መንገድ ግጭቶች ሲከሰቱ በአፋጣኝ መፍታት፤

7.የበላይ አለቆች ባህላዊውን አስተዳደር እውቅና መስጠት አለባቸው እና

8.አጎራባች ክልሎችን የሚነኩ ሃብቶችን በጋራ ከክልሎች ጋር በመወያየት መጠቀም የሚሉ ናቸው።


በሀገራችን የጋራ የሆኑ ሀብቶችን በመጠቀም ዙሪያ መልካም ማህበራዊ አስተዳደር ቢኖርም የተፈጥሮ ሀብቶች እየገጠማቸው በመጣው እጥረት ምክንያት ሀብቶችን በጋራ በመጠቀም ዙሪያ በርካታ ግጭቶች ይፈጠራሉ (የሚነሱት የጥቅም ይገባኛል ግጭቶች፦ ነዋሪዎች የሚሞቱባቸው፤ ሀብቶች የሚወድምባቸው እንዲሁም  ሰዎች የሚፈናቀሉባቸው ናቸው)።


የክልል አወቃቀር ባለበት የሀገራችን የመንግስት አስተዳደር በክልሎች መካከል፤ በዞኖች መካከል፤ በወረዳዎች መካከል፤ በቀበሌዎች መካከል፤ በጎጦች እና በመንደሮች መካከል በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የጋራ ሀብቶች እንዳሉ ይታወቃል!(ጎረቤት ሀገራት ደግሞ እንደ ሀገር ከሀገራችን ጋር የሚጋሩት የአባይ ወንዝ ምሳሌ መሆን ይችላል!)።

የጋራ ሀብቶችን በእኩል ተጠቃሚነት እና ባለቤትነት ስርዓት ለማስተዳደር መቸገር፣ ሀብቱ መስጠት የሚገባውን ጥቅም ለማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዳይሰጥ ምክንያት ይሆናል!


ይህ የሊን አስተሳሰብ ከሚነሱበት ትችቶች መካከል ስብጥር ማህበረሰብ ባለበት አካባቢ በአንድ መጠቀሚያ ሃብተ ላይ ስለፍታዊነት ለመስማማት እና ህብረት ለመፍጠር መቻላቸው አስቸጋሪ ስለመሆኑ እና የጥቅም ግጭት ሲፈጠር ሁኔታውን ለማስተካከል ምን ማድረግ እንዳለባቸው አስገዳጅ መፍትሄ አልጠቆመችም ይሏታል።


በ2013 በካንሰር ህመም ምክንያት ህይወቷ አልፏል።