Get Mystery Box with random crypto!

400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ዋለ ሐምሌ 17/2015 | AddisWalta - AW

400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ዋለ

ሐምሌ 17/2015 (ዋልታ) መነሻውን ከጅቡቲ ወደብ አድርጎ መዳረሻውን ወረታ ከተማ ለማድረግ የተንቀሳቀሰው 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የጫነ ተሳቢ ተሽከርካሪ ከታሰበው ቦታ ሳይደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።

ህገ ወጥ ድርጊቱ የተፈፀመው በባህርዳር ከተማ ሰባታሚት ቀበሌ ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ሲሆን ከሌሊቱ 6 ሰዓት የአፈር ማዳበሪያ በህገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች ሲያከፋፍል በህብረተሰቡ ጥቆማ መያዙን የሰባታሚት ቀበሌ ፖሊስ ኦፊሰር ኮንስታብል ዮሐንስ ጥላሁን ተናግረዋል።

አብዛኛው ማዳበሪያ ሳይራገፍ ከነተሽከርካሪው መያዝ ቢቻልም ከ140 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ መሰራጨቱን ፖሊስ ባደረገው ክትትል ደርሶበታል።

ፖሊስ ባደረገው ቤተ ለቤት ፍተሻ ከተሽከርካሪው ተራግፎ በግለሰቦች ቤት የተከማቸ በርካታ የአፈር ማዳበሪያ አግኝቷል።

89 ኩንታል ማዳበሪያ በአንድ ግለሰብ ቤት ተከማችቶ የተገኘ ሲሆን 24 ኩንታል ማዳበሪያ ደግሞ በአንድ ግለሰብ ቤት በአልጋ ስር እና በኩሽና ተከዝኖ መገኘቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አሽከርካሪው ግለሰብ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ፖሊስ የገለፀ ሲሆን ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ህገ ወጥ ተግባርን እንዲያወግዝም ጠይቋል።