Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ምሳሌ የሚሆን ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ተጠቆመ ሰኔ 28/2015 | AddisWalta - AW

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ምሳሌ የሚሆን ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ተጠቆመ

ሰኔ 28/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ለቀጣናው ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ሲሉ የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።

የኢትዮ ጅቡቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ ትራንስፖርት፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተሳሰሩ ሀገራት ናቸው ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ታሪካዊ እና በጠንካራ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የጅቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረ እንደሆነም አመልክተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ተወካይ የምስራች ብናልፈው በበኩላቸው ኢጋድ በህብረቱ አባል ሀገራት መካከል ያለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ያበረታታል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ዘርፈ ብዙ የሚያስተሳስራቸው ነገር እንዳለ ጠቅሰው ኢትዮ ጅቡቱ የባቡር ትራንስፖርት ቀዳሚው መሆኑን አንስተዋል።

112 አባላትን የያዘ የጅቡቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

በመስከረም ቸርነት