Get Mystery Box with random crypto!

የሌማት ትሩፋት ትግበራ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ስለሚኖረው ፋይዳ ላይ የፓናል ውይይት እየተካሄደ | AddisWalta - AW

የሌማት ትሩፋት ትግበራ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ስለሚኖረው ፋይዳ ላይ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው

ግንቦት 3/2013 (ዋልታ) የሌማት ትሩፋትን በመተግበር ምግብ ዋስትናን እናረጋግጣለን በሚል መሪ ቃል የግብርና ሚኒስቴር ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው::

በፓናል ወይይቱ ላይ ከአለም አቀፍ እና ከልማት አጋር ድርጅቶች የመጡ ተገባዥ እንግዶች ፣ ከምርምር ተቋማት እና ከዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ እንግዶች ተሳትፈዋል ::

የፓናል ውይይቱን በይፋ የከፈቱት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ ግዙፍ የአሳ እርባታን ጨምሮ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ልማት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ይህንን ሀብት ባለፉት ዓመታት ሳንጠቀም መቆየቱን አስታዉሰዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በሌማት ትሩፋት በምግብ ራስን ለመቻል እየተሰራ ያለዉ ስራ አመርቂ ውጤት የታየበት ነው ብለዋል ::

አፈ ጉባኤው አክለውም በአረንጓዴ አሻራ እና በስንዴ ልማት ያስመዘገብነውን ውጤት በሌማት ትሩፋት ልንደግም ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የሌማት ትሩፋት በሁሉም ክልሎች ይፋ ተደርጐ ወደ ስራ ከተገባ ወዲህ በአርብቶ አደሩ እና አርሶ አደሩ ዘንድ ልዩ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል::

የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ዘጠነኛው ወሩ ሲሆን ከ34 ሚሊዮን በላይ ጫጩቶች፣ 1.2 ሚሊዮን የንብ ማነቢያ ቀፎዎች እና 1.2 ሚሊዮን ላሞች አቅርቦት መደረጉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በዋናነት ከውጭ የሚገቡ የሌማት ትሩፋቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል ::


በሜሮን መስፍን