Get Mystery Box with random crypto!

የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ | AddisWalta - AW

የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

ግንቦት 03/2015 (ዋለታ) ኢትዮጵያ የረጅም ግዜ የአነስተኛ ካርቦን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ይፋ አደረገች ፡፡

ስትራቴጂው ይፋ የተደረገው ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች፣ ሚኒስትሮች፣ አምባባሳደሮቾ እና ሌሎች በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው።

የኢትዮጵያ የረጅም ግዜ ዝቅተኛ ካርበን ልቀት ልማት ስትራቴጂ የተዘጋጀው በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሲሆን ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ ተግባር ላይ ይውላል ተብሏል።

ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአየር ንብረት ለውጥ ባለፉት አመታት ሀገራችን ላይ አሉታዊ ተጽኖ ማሳደሩን አስታውሰው የምንፈልገውን ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ዘርፈ ብዙ የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያም ባለፉት ግዚያት የተለያዩ የፖሊሲ ማእቀፎች አዘጋጅታ ሰራ ላይ ስታውል መቆየቷን አንስተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ምንም እንኳን አሁን ላይ አማቂ ጋዝን ወደ አየር በመልቀቅ ትልቅ ደርሻ ባይኖራትም፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከልማት እቅዶች ጋር አስተሳስሮ መጎዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መንግስት ይህን በመገንዘብ በአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን እንደ አንድ ምሰሶ አድርጎ ማካተቱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በመስከረም ቸርነት