Get Mystery Box with random crypto!

በዛሬው የበጎ ፈቃድ ቀን በየካቲት 12 ሆስፒታል የደም ልገሳ መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ተገለጸ ጳ | Walta

በዛሬው የበጎ ፈቃድ ቀን በየካቲት 12 ሆስፒታል የደም ልገሳ መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ተገለጸ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) በዛሬው የበጎ ፈቃድ ቀን በየካቲት 12 ሆስፒታል የደም ልገሳ መርኃ ግብር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አስታወቀ።

ዕለቱን በማስመልከት በየካቲት 12 ሆስፒታል በዋናነት ከተዘጋጀው መርኃ ግብር በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አደባባዮች ማህበረሰቡ በነቂስ ወጥቶ የደም ልገሳ ተግባር እንዲያከናውን ዝግጅት መጠናቀቁን የባንኩ ምክትል ዳይሬክተር ሃብታሙ ታዬ ገልፀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ቀንን በማስመልከት ይተገበራሉ ተብለው ሰፊ ዝግጀት ከተደረገባቸው ተግባራት መካከል የደም ልገሳ መርኃ ግብር አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የደም ባንኮች እና የጤና ቢሮዎች ለስራው መሳካት ዝግጅት መጨረሳቸውን ገልጸዋል።

ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ከጤና ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተውጣጡ አካላት በዕለቱ የሚካሄዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርኃ ግብሮችን በዋናነት እንደሚያስተባብሩም ኃላፊው ተናግረዋል።

የበጎ ቀን ሲባል ትልቁ በጎነት የደም ልገሳ ነው የሚሉት ኃላፊው በደም እጥረት ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ሰዎችን በበጎ ፈቃድ ደም በመለገስ መታደግ እንደሚቻል ገልፀዋል።

በክረምቱ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ድንኳኖችን በመትከል በጎ ፈቃደኞች ደም እንዲለግሱ በተከናወነው ስራ ከ3 ሺሕ በላይ ዩኒት ደም በክምችት ደረጃ መኖሩንም ኃላፊው ገልፀዋል።

ይሁንና አሁን ባለው ተጨባጭ የሃገራችን ሁኔታ የሚያስፈልገው የደም ከምችት ከፍተኛ እጥረት የሚታይበት መሆኑን ተናግረዋል።

ለፈጣን መረጃዎች:-
ቴሌግራም https://t.me/WALTA_TV_Eth