Get Mystery Box with random crypto!

ኡማህ ነውን? በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። 16፥120 ኢብራሂ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ኡማህ ነውን?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

16፥120 ኢብራሂም ለአሏህ ታዛዥ ወደ ቀጥተኛ ሃይማኖት ተዘንባይ ሕዝብ ነበር፡፡ ከአጋሪዎቹም አልነበረም፡፡ إِنَّ إِبْرَاهِيمَ كَانَ أُمَّةً قَانِتًا لِّلَّهِ حَنِيفًا وَلَمْ يَكُ مِنَ الْمُشْرِكِينَ

አልምጥ እና አልግጥ የሆኑ ሚሽነሪዎች፦ "ኡማህ" أُمَّة የሚለው ቃል ቁርኣን ላይ ያለ አግባብ ሁለት ቦታ ገብቷል፥ አንደኛው እንስሳትን ሕዝብ ሲል ሁለተኛው ደግሞ ኢብራሂምን ሕዝብ ይላል" እያሉ ያለ ዕውቀት ሲቦተረፉ ግርም ይላል። ሐቅን አጥልቆ እና ታጥቆ ለተነሳ ሙሥሊም ይህ አንኮላ እና እንኩቶ ትችት ከመጤፉ ነው፥ ለዚህ ቅሪላ እና አለሌ ትችት መልስ እንስጥ!
"ኡማህ" أُمَّة የሚለው ቃል "አመመ" أَمَّمَ ማለትም "ሐዘበ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ሕዝብ" ማለት ነው፥ የኡማህ ብዙ ቁጥር ደግሞ "ኡመም" أُمَم ሲሆን "ሕዝቦች" ማለት ነው፦
6፥38 ከተንቀሳቃሽም በምድር የሚኼድ በሁለት ክንፎቹ የሚበርም በራሪ መሰሎቻችሁ ሕዝቦች እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡ وَمَا مِن دَابَّةٍ فِي الْأَرْضِ وَلَا طَائِرٍ يَطِيرُ بِجَنَاحَيْهِ إِلَّا أُمَمٌ أَمْثَالُكُم

"ዳባህ" دَابَّة ማለት "እንስሳ" ማለት ነው፥ እንስሳት የየራሳቸው ስብስብ ስላላቸው "ሕዝቦች" ናቸው። ይህ ትችት መልስ በባይብል መሳ ለመሳ ስናየው "ሕዝብ" የሚለው የግዕዝ ቃል "ሐዘበ" ማለትም "ሰበሰበ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ስብስብ" ማለት ነው፥ እንስሳት እኮ "ስብስብ" አላቸው፦
ምሳሌ 30፥25 ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው "ሕዝቦች" ናቸው። הַ֭נְּמָלִים עַ֣ם לֹא־עָ֑ז וַיָּכִ֖ינוּ בַקַּ֣יִץ לַחְמָֽם׃
ምሳሌ 30፥25 ሽኮኮዎች ያልበረቱ "ሕዝቦች ናቸው። פַנִּים עַ֣ם לֹא־עָצ֑וּם וַיָּשִׂ֖ימוּ בַסֶּ֣לַע בֵּיתָֽם׃

ሁለቱም አናቅጽ ላይ "አም" עַ֣ם ማለት "ሕዝብ" ማለት ሲሆን ገብረ ጕንዳን እና ሽኮኮዎች "ሕዝብ" መባላቸው ስታነቡ ምን ይውጣችሁ ይሆን? ሁለተኛውን ትችት እስቲ እንመልከት፦
16፥120 ኢብራሂም ለአላህ ታዛዥ ወደ ቀጥተኛ ሃይማኖት ተዘንባይ "ሕዝብ" ነበር፡፡ ከአጋሪዎቹም አልነበረም፡፡ إِنَّ إِبْرَاهِيمَ كَانَ أُمَّةً قَانِتًا لِّلَّهِ حَنِيفًا وَلَمْ يَكُ مِنَ الْمُشْرِكِينَ

እዚህ አንቀጽ ላይ ኢብራሂም "ሕዝብ" የተባለው በመውለድ እና በመክበድ አባት፣ አያት፣ ቅድመ አያት፣ ቅም አያት፣ ቅማንት፣ ሽማት፣ ምንዥላት፣ እንጅላት፣ ፍናጅ እና ቅናጅ በመሆን መባዛቱን የሚያሳይ ነው። ይህ ትችት መልስ በባይብል መሳ ለመሳ ስናየው አብርሃም "ሕዝብ" እንደሚሆን ይናገራል፦
ዘፍጥረት 17፥6 እጅግም አበዛሃለሁ፥ "ሕዝብ" አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። וְהִפְרֵתִ֤י אֹֽתְךָ֙ בִּמְאֹ֣ד מְאֹ֔ד וּנְתַתִּ֖יךָ לְגֹויִ֑ם וּמְלָכִ֖ים מִמְּךָ֥ יֵצֵֽאוּ׃

አብርሃም ሲወልድ እና ሲዋለድ በመብዛት ሕዝብ መሆኑን ካየን ዘንዳ ሕዝብ ከሆነ በኃላ አምላካችን አሏህ ቁርኣን ላይ "ኢብራሂም "ሕዝብ" ነበር" ቢለን እንዴት ያለ ዕውቀት ለትችት ትሮጣላችሁ? አሏህ የህዲኩም ወዩሠቢትና! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም